የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አላችሁን?
1 ኢየሱስ ክርስቶስ ከራስ ወዳድነት ፈጽሞ ነፃ በሆነ መንገድ ለሰው ልጆች ላከናወነው ተግባር ያለን አድናቆት ችሎታችንን፣ ኃይላችንን እንዲሁም ጉልበታችንን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በመያዝ እንድንጠቀምበት ሊያነሳሳን ይገባል። ቅዱስ ጽሑፉ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ” በማለት ያሳስበናል። (ሮሜ 12:1) በየጊዜው ራሳችሁን መመርመራችሁ ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁን ያህል እንዲህ ያለውን መንፈስ በተሟላ መልኩ እያሳያችሁ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳችኋል።
2 የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማካበት:- ዘወትር የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለማድረግና ለማጥናት ጊዜ መድባችኋል? ያወጣችሁትንስ ኘሮግራም በጥብቅ ትከተላላችሁ? ለጉባኤ ስብሰባዎች በጥሩ ሁኔታ የመዘጋጀት ልማድ አላችሁ? የቤተሰብ ራስ ከሆናችሁ ከቤተሰባችሁ አባሎች ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ታደርጋላችሁ? እነዚህን ነገሮች ማድረግ ምናልባት በቴሌቪዥን፣ በኮምፒዩተር ወይም በሌሎች ነገሮች የምታጠፉትን ጊዜ መሥዋዕት እንድታደርጉ ይጠይቅባችሁ ይሆናል። ሆኖም የአምላክን ቃል በማጥናት የምታሳልፉት ጊዜ ወደ ዘላለም ሕይወት እንድታመሩ የሚረዳችሁ መሆኑን ስለምታውቁ የምትከፍሉት መሥዋዕትነት ከዚህ ጋር ሲወዳደር ከቁጥር የሚገባም አይደለም!—ዮሐ. 17:3
3 ልጆቻችሁን በማሠልጠን:- የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ለመኮትኮት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የልጅነት ወቅት ነው። ለጨዋታ ጊዜ ቢኖረውም ለሥራና ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችም ጊዜ መኖር እንዳለበት ልጆቻችሁን አስተምሯቸው። (ኤፌ. 6:4) በቤት ውስጥ የሚያከናውኑት አንድ ጠቃሚ ሥራ ስጧቸው። ከእነርሱ ጋር በአገልግሎት ለመካፈል ቋሚ ኘሮግራም አውጡ። እንዲሁም ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ ሆናችሁ በመገኘት የሰጣችሁትን መመሪያ አጠናክሩት።
4 በጉባኤ እንቅስቃሴዎች:- በጉባኤው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው ለሁሉም የሚጠቅም ተግባር ለማከናወን ሲል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑ ጉባኤውን ያጠነክረዋል። (ዕብ. 13:16) በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተጨማሪ ሰዓት ማሳለፍ ትችላላችሁ? የታመሙትን ወይም በዕድሜ የገፉትን ለመርዳት ምናልባትም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ይዛችኋቸው ለመሄድ በፈቃደኛነት ራሳችሁን ማቅረብ ትችላላችሁ?
5 ኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወቱን የላቀ ዋጋ ያለው መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ በፊት ደቀ መዛሙርቱን ዓይናቸው በመንግሥቱ ፍላጎቶች ላይ እንዲያተኩርና በሕይወታቸው ውስጥ ሌሎቹን ነገሮች በሁለተኛ ደረጃ እንዲያስቀምጡ መክሮአቸዋል። (ማቴ. 6:33) ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን እስከቀጠልን ድረስ እንዲህ ያለውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን ከፍተኛ ደስታ ያመጣልናል።