የአንባብያን ጥያቄዎች
የይሖዋ ፍትሕ በምሕረቱ ይለዝባል ብሎ መናገር ትክክል ነውን?
ምንም እንኳን በዚህ ሐረግ ስንጠቀም የቆየን ቢሆንም ፍትሑ ለርኅራኄ ቦታ የማይሰጥ ሆኖ ምሕረቱ ከፍትሑ የተሻለ ይመስል የይሖዋ ምሕረት ፍትሑን ያለዝበዋል ወይም ይገራዋል የሚል መልእክት ስለሚያስተላልፍ በዚህ መግለጫ አለመጠቀሙ የተሻለ ነው። ምሕረቱን ከፍትሑ ማበላለጥ ትክክል አይደለም።
“ፍትሕ” ለማለት የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፍርድ” ማለትም ሊሆን ይችላል። ፍትሕ ከጽድቅ ጋር በቅርብ ይዛመዳል። ይሁን እንጂ ፍትሕ አብዛኛውን ጊዜ ሕጋዊ አንደምታ አለው። ጽድቅ ግን ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት የለውም። የይሖዋ ፍትሕ ተገቢ ቅጣት መስጠትን ሊያካትት የሚችል መሆኑ እውነት ቢሆንም ለሚገባቸው ሰዎች መዳንን መስጠትንም ሊያጠቃልል ይችላል። (ዘፍጥረት 18:20-32፤ ኢሳይያስ 56:1፤ ሚልክያስ 4:2) ስለሆነም የይሖዋ ፍትሕ ለርኅራኄ ቦታ የማይሰጥ ወይም መለዘብ የሚያስፈልገው ባሕርይ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም።
“ምሕረት” ለማለት የገባው የዕብራይስጥ ቃል ፍርድ ከመስጠት መታቀብን ሊያመለክት ይችላል። እንዲሁም ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች እፎይታ የሚያስገኝ ተግባራዊ የርኅራኄ ስሜት ማሳየትን ሊያመለክት ይችላል።—ዘዳግም 10:18፤ ሉቃስ 10:29-37
ይሖዋ የፍትሕም የምሕረትም አምላክ ነው። (ዘጸአት 34:6, 7፤ ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 145:9) ፍትሑም ሆነ ምሕረቱ ፍጹም ሲሆኑ ሁለቱም ስምም ሆነው በአንድ ላይ የሚሠሩ ናቸው። (መዝሙር 116:5፤ ሆሴዕ 2:19) ሁለቱም ባሕርያት ፍጹም እኩል ወይም እርስ በርስ የሚደጋገፉ ናቸው። ስለሆነም የይሖዋ ፍትሕ በምሕረቱ ይለዝባል የምንል ከሆነ ምሕረቱም በፍትሑ ይለዝባል ማለት ሊኖርብን ነው።
ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 30:18 አ.መ.ት ) እዚህ ላይ ኢሳይያስ የይሖዋ ምሕረት ፍትሑን ያለዝበዋል ወይም ይገድበዋል ማለቱ ሳይሆን ፍትሑ የምሕረት እርምጃ እንዲወስድ ያንቀሳቅሰዋል ማለቱ ነው። ይሖዋ ፍትሐዊ በመሆኑ ምክንያት እንዲሁም አፍቃሪ በመሆኑ ምክንያት ምሕረት ያሳያል።
እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱሱ ጸሐፊ ያዕቆብ “ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 2:13ለ የ1980 ትርጉም ) ይሁን እንጂ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ያዕቆብ እየተናገረ ያለው ስለ ይሖዋ ሳይሆን ክርስቲያኖች ችግር ላይ ለወደቁና ለድሆች ስለሚያሳዩት ምሕረት ነበር። (ያዕቆብ 1:27፤ 2:1-9) እንዲህ ያለ ምሕረት የሚያሳዩ ሰዎች ወደ ፍርድ በሚመጡበት ጊዜ ይሖዋ ያሳዩትን ባሕርይ ግምት ውስጥ በማስገባት በልጁ መሥዋዕት አማካኝነት በምሕረት ይቅር ይላቸዋል። ስለሆነም መሐሪ በመሆን ያሳዩት ጠባይ በኃላፊነት እንዲጠየቁ የሚያደርጋቸውን ማንኛውንም ዓይነት ፍርድ ያሸንፋል።—ምሳሌ 14:21፤ ማቴዎስ 5:7፤ 6:12፤ 7:1, 2
በዚህ ምክንያት የይሖዋ ፍትሕ በምሕረቱ መለዘብ ያስፈልገዋል በሚል ስሜት ፍርዱ በምሕረቱ ይለዝባል ብሎ መናገር ትክክል አይደለም። በይሖዋ ዘንድ እነዚህ ሁለት ባሕርያት እኩል ሚዛን የሚደፉ ናቸው። ፍቅርንና ጥበብን ከመሳሰሉ ከሌሎቹ የይሖዋ ባሕርያት ጋር እኩል እንደሆኑትና በእነዚህም ባሕርያት አማካኝነት ሚዛናቸውን እንደሚጠብቁ ሁሉ እርስ በርሳቸውም እንዲሁ እኩል ናቸው።