የጥናት ርዕስ 41
የምናገለግለው አምላክ “ምሕረቱ ብዙ ነው”
“ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው፤ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል።”—መዝ. 145:9
መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት
ማስተዋወቂያa
1. መሐሪ ሰው ሲባል ወደ አእምሯችን የሚመጣው ምን ሊሆን ይችላል?
መሐሪ ሰው ሲባል ወደ አእምሯችን የሚመጣው ደግ፣ አሳቢ፣ ሩኅሩኅና ለጋስ የሆነ ሰው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ እናስታውስ ይሆናል። ከሌላ አገር የመጣው ይህ ሰው በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው አይሁዳዊ “ምሕረት በማሳየት” ረድቶታል። ሳምራዊው ለቆሰለው አይሁዳዊ ‘በጣም ስላዘነለት’ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ረድቶታል። (ሉቃስ 10:29-37) ይህ ምሳሌ የአምላካችን ግሩም ባሕርይ ስለሆነው ስለ ምሕረት ያስተምረናል። ምሕረት የአምላክ ፍቅር አንዱ መገለጫ ነው፤ ይሖዋ በየዕለቱ በተለያዩ መንገዶች ምሕረት ያሳየናል።
2. ምሕረት የሚገለጽበት ሌላ መንገድ ምንድን ነው?
2 ምሕረት የሚገለጽበት ሌላም መንገድ አለ። ምሕረት፣ ቅጣት የሚገባው ሰው ይቅርታ እንዲደረግለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ቅጣቱ እንዲቀርለት ማድረግንም ያመለክታል። ይሖዋ በዚህ መንገድ ምሕረት እንዳሳየን በሕይወታችን በግልጽ ተመልክተናል። መዝሙራዊው “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም” ብሏል። (መዝ. 103:10) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ኃጢአት ለሠራ ግለሰብ ጠንከር ያለ ተግሣጽ የሚሰጥበት ጊዜ አለ።
3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ጥያቄዎችን እንመልሳለን። ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለምንድን ነው? ጠንከር ባለ ተግሣጽና በምሕረት መካከል ግንኙነት አለ? በተጨማሪም ምሕረት እንድናሳይ ምን ሊረዳን ይችላል? የአምላክ ቃል ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለምንድን ነው?
4. ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ ምሕረት ማሳየት ይወዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ የነበረው አምላክ ፍጹማን ላልሆኑት ቅቡዓን አገልጋዮቹ ሰማያዊ ተስፋ በመስጠት ስላሳያቸው ምሕረት ነው። (ኤፌ. 2:4-7) ሆኖም የይሖዋ ምሕረት የተገለጸው በዚህ መንገድ ብቻ አይደለም። መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው፤ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 145:9) ይሖዋ ሰዎችን ስለሚወድ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት ባለበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያደርጋል።
5. ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ምሕረት ያወቀው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምሕረት ማሳየት ምን ያህል እንደሚወድ ከማንም በላይ ያውቃል። እሱና አባቱ የሰው ልጆች በምድር ላይ በኖሩባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ሁሉ በሰማይ ላይ አብረው ኖረዋል። (ምሳሌ 8:30, 31) ኢየሱስ፣ ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ምሕረት ሲያሳይ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። (መዝ. 78:37-42) ኢየሱስ ማራኪ የሆነውን ይህን የአባቱን ባሕርይ በትምህርቶቹ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል።
አባትየው ዓምፆ የነበረውን ልጁን አላዋረደውም፤ ከዚህ ይልቅ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጎለታል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)c
6. ኢየሱስ ስለ አባቱ ምሕረት ለማስተማር የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?
6 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምሕረት ማድረግ ምን ያህል እንደሚወድ ለማሳየት ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተናግሯል። ልጁ ከቤቱ ወጥቶ “ልቅ የሆነ ሕይወት በመኖር ንብረቱን አባከነ።” (ሉቃስ 15:13) ከጊዜ በኋላ ይህ ወጣት ከኃጢአቱ ንስሐ ገባ፤ ራሱን አዋረደ እንዲሁም ወደ ቤቱ ተመለሰ። ታዲያ አባትየው ምን ያደርግ ይሆን? ወጣቱ ይህን ለማወቅ ብዙ መጠበቅ አላስፈለገውም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ልጁ] ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” አባትየው ልጁን አላዋረደውም። ከዚህ ይልቅ ልጁን በምሕረት ይቅር በማለት በድጋሚ የቤተሰቡ አባል እንዲሆን ፈቅዶለታል። አባካኙ ልጅ የፈጸመው ኃጢአት ከባድ ነው፤ ሆኖም ንስሐ በመግባቱ አባቱ ይቅር ብሎታል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው መሐሪ አባት ይሖዋን ይወክላል። ኢየሱስ ይህን ልብ የሚነካ ምሳሌ በመጠቀም፣ አባቱ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ አስተምሯል።—ሉቃስ 15:17-24
7. የይሖዋ ጥበብ ከምሕረቱ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ወደር የለሽ ጥበብ ስላለው ነው። ይሖዋ ጥበበኛ ነው ሲባል ከፍተኛ እውቀት ያለው ሆኖም ስሜት የሌለው አምላክ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት” እንደሆነ ይናገራል። (ያዕ. 3:17) ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ ይሖዋ፣ ምሕረት ማሳየቱ ልጆቹን እንደሚጠቅማቸው ያውቃል። (መዝ. 103:13፤ ኢሳ. 49:15) ይሖዋ ምሕረት የሚያሳይ መሆኑ ሰዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ስለዚህ ይሖዋ ወደር የለሽ ጥበብ ያለው በመሆኑ፣ ምሕረት ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት እስካለ ድረስ ምሕረት ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሕረት ፍጹም ሚዛናዊ ነው። ይሖዋ ጥበበኛ ነው፤ ስለዚህ መሐሪ መሆኑ ልል እንዲሆን አያደርገውም።
8. አንዳንድ ጊዜ የትኛውን እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል? ለምንስ?
8 አንድ የአምላክ አገልጋይ ሆን ብሎ የኃጢአት ጎዳና መከተል ጀመረ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ‘እንዲህ ካለው ሰው ጋር መግጠማችሁን ተዉ’ የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 5:11) ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤው ይወገዳሉ። ይህ እርምጃ መወሰዱ ታማኝ የሆኑት ወንድሞችና እህቶች ከጉዳት እንዲጠበቁ ከማድረጉም ሌላ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ለማስከበር ያስችላል። ይሁንና አንዳንዶች ውገዳን የይሖዋ ምሕረት መገለጫ አድርጎ መመልከት ሊከብዳቸው ይችላል። በእርግጥ ውገዳ የይሖዋ ምሕረት መገለጫ ነው? እስቲ እንመልከት።
ጠንከር ያለ ተግሣጽ የምሕረት መገለጫ ሊሆን ይችላል?
አንድ የታመመ በግ ከመንጋው ተለይቶ እንዲቆይ ሊደረግ ይችላል፤ በዚያ ወቅትም ግን እረኛው ይንከባከበዋል (ከአንቀጽ 9-11ን ተመልከት)
9-10. በዕብራውያን 12:5, 6 መሠረት ውገዳ ምሕረት የሚንጸባረቅበት ዝግጅት ነው የምንለው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
9 በጉባኤ ስብሰባ ላይ፣ የምናውቀውንና የምንወደውን አንድ ሰው በተመለከተ “እገሌ ከእንግዲህ የይሖዋ ምሥክር አይደለም” የሚል ማስታወቂያ ሲነገር በጣም እናዝናለን። ‘ይህን ሰው ማስወገድ በእርግጥ አስፈላጊ ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል። ይሁንና ውገዳ በእርግጥ ምሕረት የሚንጸባረቅበት እርምጃ ነው? አዎ። ተግሣጽ የሚያስፈልገውን ሰው ከመገሠጽ ወደኋላ ማለት ጥበብ፣ ምሕረትም ሆነ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርምጃ አይደለም። (ምሳሌ 13:24) ሆኖም ውገዳ፣ ንስሐ ያልገባው ኃጢአተኛ አካሄዱን እንዲያስተካክል ሊረዳው ይችላል? አዎ ይችላል። ከባድ ኃጢአት ፈጽመው የነበሩ ብዙዎች፣ ሽማግሌዎች የወሰዱት ጥብቅ እርምጃ እንዲነቁና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ፣ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ እንዲሁም ወደ ይሖዋ እቅፍ እንዲመለሱ እንደረዳቸው ተናግረዋል።—ዕብራውያን 12:5, 6ን አንብብ።
10 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ እረኛ ከበጎቹ አንዱ እንደታመመ አስተዋለ። እረኛው ለታመመው በግ ሕክምና ለመስጠት በጉን ከመንጋው ለይቶ ማቆየት እንደሚያስፈልግ ያውቃል። ሆኖም በጎች ከመንጋቸው መለየት አይፈልጉም፤ ብቻቸውን ከተገለሉ ሊረበሹ ይችላሉ። ታዲያ እረኛው እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ጨካኝ ያስብለዋል? በጭራሽ አያስብለውም። እረኛው የታመመው በግ ከመንጋው ጋር እንዲቀላቀል ቢያደርግ በሽታው እንደሚዛመት ያውቃል። የታመመውን በግ ለይቶ በማቆየት መንጋው በሙሉ ከበሽታ እንዲጠበቅ ያደርጋል።—ከዘሌዋውያን 13:3, 4 ጋር አወዳድር።
11. (ሀ) የተወገደ ሰው ከታመመ በግ ጋር የሚመሳሰለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) የተወገዱ ሰዎች እርዳታ ማግኘት የሚችሉባቸው ምን ዝግጅቶች አሉ?
11 የተወገደ ክርስቲያን ከታመመ በግ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ሰው በመንፈሳዊ ታሟል። (ያዕ. 5:14) እንደ አንዳንድ በሽታዎች ሁሉ መንፈሳዊ ሕመምም ወደ ሌሎች ሊተላለፍ ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ፣ በመንፈሳዊ የታመመ ሰው ከጉባኤው እንዲገለል ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ይህ ተግሣጽ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑት የመንጋው አባላት ያለውን ፍቅር ያሳያል፤ እንዲሁም ኃጢአተኛው ልቡ እንዲነካና ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል። ግለሰቡ፣ በተወገደበት ወቅትም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችላል። እዚያም በመንፈሳዊ መመገብና እምነቱን ማጠናከር ይችላል። በተጨማሪም ለግሉ የሚጠቀምባቸውን ጽሑፎች መውሰድና JW ብሮድካስቲንግ መመልከት ይችላል። ሽማግሌዎች ግለሰቡ የሚያደርገውን ለውጥ ሲያዩ እንደገና በመንፈሳዊ ጤናማ መሆንና ወደ ጉባኤው መመለስ እንዲችል አልፎ አልፎ በግሉ ምክርና መመሪያ ሊሰጡት ይችላሉ።b
12. ሽማግሌዎች ንስሐ ካልገባ ኃጢአተኛ ጋር በተያያዘ የትኛውን ፍቅርና ምሕረት የሚንጸባረቅበት እርምጃ ይወስዳሉ?
12 ከጉባኤ የሚወገዱት ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ብቻ እንደሆኑ ማስታወስ ያስፈልጋል። ሽማግሌዎች ይህ በቀላሉ ሊታይ የማይገባው ከባድ ውሳኔ እንደሆነ ያውቃሉ። ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጠው “በተገቢው መጠን” እንደሆነም ያውቃሉ። (ኤር. 30:11) ወንድሞቻቸውን ይወዷቸዋል፤ በመሆኑም በመንፈሳዊ ሊጎዳቸው የሚችል ምንም ነገር ማድረግ አይፈልጉም። አንዳንድ ጊዜ ግን ፍቅርና ምሕረት የሚንጸባረቅበት እርምጃ፣ ኃጢአተኛው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከጉባኤው እንዲወገድ ማድረግ ነው።
13. በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበረ አንድ ክርስቲያን ከጉባኤ መወገድ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ ንስሐ ካልገባ አንድ ኃጢአተኛ ጋር በተያያዘ ምን እንዳደረገ እንመልከት። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ከአባቱ ሚስት ጋር ብልግና የሚፈጽም አንድ ክርስቲያን ነበር። ይህ እንዴት ያለ ዘግናኝ ነገር ነው! ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ከአባቱ ሚስት ጋር የተኛ ሰው አባቱን ለኀፍረት ዳርጎታል። ሁለቱም ይገደሉ።” (ዘሌ. 20:11) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ሰውየው እንዲገደል ማዘዝ እንደማይችል የታወቀ ነው። ሆኖም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ይህን ሰው ከጉባኤ እንዲያስወግዱት አዟቸዋል። የዚህ ሰው ብልግና በሌሎቹ የጉባኤው አባላት ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ይህ አስጸያፊ ድርጊት የሚያሳፍር ነገር እንደሆነ አልተሰማቸውም።—1 ቆሮ. 5:1, 2, 13
14. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው የተወገደ ሰው ምሕረት ያሳየው እንዴት ነው? ለምንስ? (2 ቆሮንቶስ 2:5-8, 11)
14 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ይህ ሰው ትልቅ ለውጥ እንዳደረገ ተገነዘበ። ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ ገብቶ ነበር! ይህ ሰው በጉባኤው ላይ ውርደት ያመጣ ቢሆንም ጳውሎስ ከልክ በላይ ጥብቅ ሊሆንበት አልፈለገም። ለሽማግሌዎቹ “በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎቹ ይህን ማድረግ ያለባቸው “ይህ ሰው ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ” እንደሆነ ገልጿል። ጳውሎስ ንስሐ ለገባው ሰው አዝኖለታል። ግለሰቡ በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት በጣም ከመጸጸቱና ከልክ በላይ ከመደቆሱ የተነሳ ምሕረት ለማግኘት መሞከሩን ከናካቴው እንዳይተወው ጳውሎስ ሰግቶ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 2:5-8, 11ን አንብብ።
15. ሽማግሌዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጥብቅም መሐሪም መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
15 እንደ ይሖዋ ሁሉ ሽማግሌዎችም ምሕረት ማሳየት ይወዳሉ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ይሆናሉ፤ ሆኖም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያሳያሉ። ሽማግሌዎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግሣጽ የማይሰጡ ከሆነ ግን መሐሪ ሳይሆን ልል ይሆናሉ። ይሁንና ምሕረት ማሳየት የሚጠበቅባቸው ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው?
ሁላችንም ምሕረት እንድናሳይ ምን ይረዳናል?
16. ምሳሌ 21:13 እንደሚለው ይሖዋ ምሕረት ለማያሳዩ ሰዎች ምን አያደርግላቸውም?
16 ሁሉም ክርስቲያኖች እንደ ይሖዋ ምሕረት ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ። ለምን? አንዱ ምክንያት ይሖዋ ምሕረት የማያሳዩ ሰዎችን ጸሎት የማይሰማ መሆኑ ነው። (ምሳሌ 21:13ን አንብብ።) ሁላችንም ብንሆን ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰማልን እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ምሕረት የለሽ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እየተሠቃየ ያለን ክርስቲያን ላለመስማት ጆሯችንን ከመድፈን ይልቅ “ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት” ለመስማት ምንጊዜም ፈጣን መሆን አለብን። በተጨማሪም የሚከተለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ማስታወስ ይኖርብናል፦ “ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታል።” (ያዕ. 2:13) ትሑቶች በመሆን፣ ምሕረት ምን ያህል እንደሚያስፈልገን የምናስታውስ ከሆነ እኛም ምሕረት ለማሳየት መነሳሳታችን አይቀርም። በተለይ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ወደ ጉባኤው ሲመለስ ምሕረት ማሳየት ይኖርብናል።
17. ንጉሥ ዳዊት ልባዊ ምሕረት ያሳየው እንዴት ነው?
17 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎች፣ ምሕረት የለሽ ከመሆን ይልቅ ምሕረት እንድናሳይ ይረዱናል። የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት በተደጋጋሚ ጊዜያት ልባዊ ምሕረት አሳይቷል። ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ዳዊት አምላክ ለቀባው ንጉሥ ምሕረት አሳይቶታል፤ ሊበቀለው ወይም ሊጎዳው አልፈለገም።—1 ሳሙ. 24:9-12, 18, 19
18-19. ዳዊት ምሕረት ያላሳየባቸው ሁለት አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
18 ይሁንና ዳዊት ምሕረት ያላሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኃይለኛ ሰው የነበረው ናባል ስለ ዳዊት በንቀት በተናገረበት ብሎም ለእሱና ለሰዎቹ ምግብ ለመስጠት እንቢ ባለበት ጊዜ ዳዊት በጣም ተበሳጭቶ ናባልንም ሆነ በቤቱ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል ተነስቶ ነበር። ሆኖም ደግና ትዕግሥተኛ የሆነችው የናባል ሚስት አቢጋኤል አፋጣኝ እርምጃ በመውሰዷ ዳዊት በራሱ ላይ የደም ዕዳ ከማምጣት ሊቆጠብ ችሏል።—1 ሳሙ. 25:9-22, 32-35
19 በሌላ ጊዜ ደግሞ ነቢዩ ናታን ለዳዊት ስለ አንድ ሀብታም ሰው ነግሮት ነበር፤ ይህ ሀብታም ሰው፣ ድሃ ከሆነው ጎረቤቱ የሚወዳትን በጉን ሰርቆበት ነበር። ዳዊት ይህን ሲሰማ በጣም ተቆጥቶ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!” አለ። (2 ሳሙ. 12:1-6) ዳዊት የሙሴን ሕግ በደንብ ያውቅ ነበር። በሙሴ ሕግ መሠረት በግ የሰረቀ ሌባ አራት እጥፍ ካሳ መክፈል ነበረበት። (ዘፀ. 22:1) ሆኖም ይህ ወንጀል የሞት ፍርድ የሚገባው አይደለም። በእርግጥም ዳዊት ያስተላለፈው ፍርድ ከልኩ ያለፈ ነበር። ናታን ይህን ምሳሌ የተናገረው ዳዊት የፈጸማቸውን እጅግ የከፉ ኃጢአቶች ለማጋለጥ ነበር! ዳዊት በናታን ምሳሌ ውስጥ ለተጠቀሰው በግ የሰረቀ ሰው ምሕረት ባያሳየውም ይሖዋ ግን ለዳዊት ምሕረት አሳይቶታል።—2 ሳሙ. 12:7-13
ንጉሥ ዳዊት በናታን ምሳሌ ላይ የተጠቀሰውን ሰው ያለምሕረት ፈርዶበታል (ከአንቀጽ 19-20ን ተመልከት)d
20. ከዳዊት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
20 ዳዊት በተበሳጨበት ወቅት ‘ናባልና በቤቱ ያሉ ወንዶች በሙሉ ሞት ይገባቸዋል’ ብሎ እንደፈረደ ልብ እንበል። በኋላ ደግሞ ዳዊት በናታን ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ሰው ሞት እንደሚገባው ፈርዶበታል። ከዚህ ዘገባ ጋር በተያያዘ ‘እንደ ዳዊት ያለ ሩኅሩኅ ሰው እንዲህ ያለ ምሕረት የለሽ ፍርድ ያስተላለፈው ለምንድን ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ዳዊት በወቅቱ የነበረበትን ሁኔታ እንመልከት። በዚያ ወቅት ዳዊት ሕሊናው እየወቀሰው ነበር። አንድ ሰው ምሕረት የለሽ መሆኑና ለመፍረድ መቸኮሉ ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት እንደሌለው ያሳያል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ የሚል ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፦ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል።” (ማቴ. 7:1, 2) እንግዲያው ምሕረት የለሽ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፤ ከዚህ ይልቅ “ምሕረቱ ብዙ” የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል ጥረት እናድርግ።
21-22. ምሕረት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
21 ምሕረት ማሳየት ሲባል ለሌሎች ማዘን ማለት ብቻ አይደለም። እንዲያውም ምሕረት “በተግባር የተደገፈ ርኅራኄ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። እንግዲያው ሁላችንም በቤተሰባችን፣ በጉባኤያችን ወይም በአካባቢያችን ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይኖሩ እንደሆነ በንቃት መከታተል እንችላለን። ምሕረት ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው አለ? ምግብ ልንወስድለት ወይም በሌላ ተግባራዊ መንገድ ልንረዳው የምንችለው ሰው ይኖር ይሆን? ውገዳ የተነሳለትን ክርስቲያን ማበረታታትና አብረነው ጊዜ ማሳለፍ እንችል ይሆን? አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥራች ለሌሎች ማካፈልም እንችላለን። ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ምሕረት ማሳየት ከምንችልባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ ይህ ነው።—ኢዮብ 29:12, 13፤ ሮም 10:14, 15፤ ያዕ. 1:27
22 ንቁ ከሆንን ምሕረት ለማሳየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሁልጊዜ እናገኛለን። ምሕረት ስናሳይ “ምሕረቱ ብዙ” የሆነውን የሰማዩን አባታችንን በእጅጉ እናስደስተዋለን!
መዝሙር 43 የምስጋና ጸሎት
a ማራኪ ከሆኑት የይሖዋ ባሕርያት መካከል አንዱ ምሕረት ነው። ሁላችንም ይህን ባሕርይ ማዳበር ይኖርብናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለምን እንደሆነ፣ የይሖዋ ተግሣጽ ምሕረት የሚንጸባረቅበት ነው የምንለው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይህን ግሩም ባሕርይ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
b ውገዳ የተነሳላቸው ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ሽማግሌዎች እንዴት ሊረዷቸው እንደሚችሉ ለማወቅ በዚህ መጽሔት ውስጥ ያለውን “ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት አድስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ የአባካኙ ልጅ አባት የቤቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ ተመለከተው፤ ከዚያም እየሮጠ ሄዶ አቀፈው።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ የነበረው ንጉሥ ዳዊት፣ ናታን በነገረው ምሳሌ ላይ ያለው ሀብታም ሰው ሞት እንደሚገባው በንዴት ሲገልጽ።