በረሃብ ለተጠቁ ሰዎች የተላከ እርዳታ!
‘ምን ዓይነት ረሃብ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የመንፈሳዊ ምግብ ረሃብ ነው! በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ዕብራዊ ነቢይ “እነሆ፣ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም” በማለት ይህን ረሃብ በተመለከተ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (አሞጽ 8:11) ኒው ዮርክ ፓተርሰን በሚገኘው ጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ112ኛው ክፍል 48 ተማሪዎች በመንፈሳዊው ረሃብ የተጠቁ ሰዎችን ለመርዳት በ5 አህጉሮችና የባሕር ደሴቶች ላይ ወደሚገኙ 19 አገሮች ለመሄድ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ተማሪዎቹ ወደተመደቡበት ቦታ የሚሄዱት ቃል በቃል ስንዴና ዘይት ይዘው ሳይሆን ያገኙትን እውቀት፣ ተሞክሮና ስልጠና ሰንቀው ነው። በባዕድ አገር በሚስዮናዊነት ለማገልገል የሚያስችላቸውን እምነት ለመገንባት ለአምስት ወራት ያህል ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል። መጋቢት 9, 2002 በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት 5, 554 ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙን በደስታ ተከታትለዋል።
ፕሮግራሙን ሞቅ ባለ ስሜት የከፈተው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ የሚያገለግለው ስቴፈን ሌት ነበር። በመጀመሪያ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡት በርካታ እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሞቅ ያለ ሰላምታ አቀረበ። ከዚያ በመቀጠል “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ከአዲሶቹ ሚስዮናውያን ሥራ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ተናገረ። (ማቴዎስ 5:14) ‘በተመደባችሁባቸው ቦታዎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ታላቅ አምላክ የሆነውን ይሖዋንና ዓላማዎቹን እንዲያደንቁና ድንቅ ሥራዎቹን እንዲያስተውሉ የመርዳት አጋጣሚ ይኖራችኋል’ ሲል ገለጸ። ወንድም ሌት ሚስዮናውያኑ በአምላክ ቃል ብርሃን አማካኝነት የሐሰት ትምህርቶችን በማጋለጥ እውነትን የሚፈልጉ ሰዎችን እንዲረዱ ማበረታቻ ሰጣቸው።
ስኬታማ ለመሆን ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ወሳኝ ነው
ከሊቀ መንበሩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ባልታሳር ፔርላ ተመራቂዎቹ ስኬታማ ሚስዮናውያን እንዲሆኑ ለማበረታታት ከተዘጋጁት ተከታታይ ንግግሮች መካከል የመጀመሪያውን አቀረበ። የንግግሩ ጭብጥ “በርቱ፤ ጠንክሩ፤ ሥራውንም ፈጽሙ” የሚል ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:20 አ.መ.ት ) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ከዚህ በፊት ሠርቶ የማያውቀውን ሥራ ማለትም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የመገንባት ከባድ ኃላፊነት ተረክቦ ነበር። ሰሎሞን ሥራውን ከመጀመሩም በላይ የቤተ መቅደሱ ግንባታ በይሖዋ ድጋፍ ሊጠናቀቅ ችሏል። ወንድም ፔርላ ይህ ለተማሪዎቹ ምን ትምህርት እንደያዘ ሲገልጽ ‘ሚስዮናዊ ሆኖ የማገልገል አዲስ ሥራ ተሰጥቷችኋል። ስለሆነም ብርቱና ጠንካራ መሆን ይገባችኋል’ አለ። ተማሪዎቹ ይሖዋን የሙጥኝ ብለው እስከያዙ ድረስ አምላክ ፈጽሞ እንደማይተዋቸው የተሰጣቸው ማበረታቻ በእርግጥ አጽናንቷቸዋል። ወንድም ፔርላ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ‘በሚስዮናዊ አገልግሎታችሁ ብዙ መልካም ውጤቶች ማግኘት ትችላላችሁ። ለእኛ ቤተሰብ እውነትን የነገሩን ሚስዮናውያን ነበሩ!’ በማለት የጠቀሰው የራሱ ተሞክሮ የአድማጮችን ስሜት ቀስቅሷል።
የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ሳሙኤል ኸርድ “ስኬታማ ለመሆን በይሖዋ ተመኩ” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። ተማሪዎቹ ሚስዮናዊነትን ሞያቸው አድርገው ሊያያዙት ነው። በዚህ ገረድ የሚያገኙት ስኬት በአመዛኙ ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ የተመካ ነው። ወንድም ኸርድ እንዲህ ሲል መከራቸው:- ‘ከጊልያድ ባገኛችሁት ትምህርት አማካኝነት ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አካብታችኋል። በደስታ ስትቀበሉ ቆይታችኋል። ከዚህ በኋላ ግን እውነተኛ ስኬት ለማግኘት ያወቃችሁትን ነገር መስጠት መጀመር ይኖርባችኋል።’ (ሥራ 20:35) ሚስዮናውያኑ ለሌሎች ጥቅም ‘ራሳቸውን ሲያፈስሱ’ ሰጪ የሚሆኑበት በርካታ አጋጣሚ ያገኛሉ።—ፊልጵስዩስ 2:17
አስተማሪዎቹ ለተማሪዎቹ የሚሰጡት የመሰነባበቻ ምክር ምን ይሆን? የማርክ ኑሜር ንግግር የተመሠረተው በሩት 3:18 ላይ (አ.መ.ት ) ሲሆን ጭብጡ “ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ታገሡ” የሚል ነበር። ተናጋሪው በኑኃሚንና በሩት ምሳሌ ላይ በመንተራስ ተመራቂዎቹ በአምላክ ምድራዊ ድርጅት ዝግጅቶች ላይ ሙሉ ትምክህት እንዲጥሉና ከአምላክ ለተገኘ ሥልጣን አክብሮት እንዲያሳዩ አበረታታቸው። ወንድም ኑሜር እንዲህ ሲል የተማሪዎቹን ልብ የሚነካ ሐሳብ ተናገረ:- ‘የተሰጣችሁን ውሳኔ ለመቀበል የምትቸገሩበት ወይም አንድ ነገር እናንተ ባሰባችሁት መንገድ ሳይሠራ በመቅረቱ ቅር የምትሰኙበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? ቸኩላችሁ ነገሮችን በራሳችሁ መንገድ ማከናወን ትጀምራላችሁ? ወይስ አምላክ ሁኔታውን የፈቀደው በጎ ውጤት ቢኖረው ነው በሚል ትምክህት “ታግሣችሁ” እሱን ትጠብቃላችሁ።’ (ሮሜ 8:28) አዲሶቹ ሚስዮናውያን በባዕድ አገር አገልግሎታቸውን ሲያከናውኑ ‘በግለሰቦች ባሕርይ ላይ ሳይሆን የይሖዋ ድርጅት እያከናወነ ባለው ሥራ ላይ ትኩረት በማድረግ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስቀደም እንዲጣጣሩ’ የተሰጣቸው ምክር በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
በተከታታይ ከቀረቡት የመክፈቻ ንግግሮች መካከል የመጨረሻውን ያቀረበው ሚስዮናዊ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ዋላስ ሊቨራንስ ሲሆን የንግግሩ ጭብጥ “በይሖዋ ዓላማ ላይ በማተኮር በአገልግሎታችሁ ጽኑ” የሚል ነበር። ተናጋሪው፣ ነቢዩ ዳንኤል የባቢሎንን ውድቀት በማየትና ኤርምያስ ከተናገረው ትንቢት በመነሳት እስራኤላውያን ከምርኮ ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን እንዳስተዋለ ገለጸ። (ኤርምያስ 25:11፤ ዳንኤል 9:2) ዳንኤል ይሖዋ ጊዜውን ጠብቆ ደረጃ በደረጃ የሚያከናውናቸውን ነገሮች በንቃት ይከታተል ነበር። ይህም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። በአንጻሩ በነቢዩ ሐጌ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን “ዘመኑ አልደረሰም” ብለዋል። (ሐጌ 1:2) በወቅቱ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባ የነበረውን ጉዳይ ዘንግተው በራሳቸው ምቾትና ፍላጎት ላይ በማተኮራቸው ከባቢሎን ነፃ የወጡበትን ዓላማ ይኸውም ቤተ መቅደሱን መልሶ የመገንባቱን ሥራ ችላ አሉ። ወንድም ሊቨራንስ “ስለዚህ ምንጊዜም የይሖዋን ዓላማ በአእምሯችሁ በመያዝ ነቅታችሁ ኑሩ” በማለት ንግግሩን ደመደመ።
የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን “ይሖዋ ሕያው በሆነው ቃል የሚጠቀሙትን ይባርካቸዋል” የሚል ጭብጥ ያለውን ክፍል በቃለ ምልልስ መልክ አቀረበ። (ዕብራውያን 4:12) ይህ ክፍል ተማሪዎቹ በመስክ አገልግሎት ባገኟቸው ተሞክሮዎች ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይሖዋ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀሙትን እንዴት እንደሚባርካቸው የሚያጎላ ነበር። ወንድም ቦወን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ አገልጋዮች ሁሉ ግሩም ምሳሌ መተዉን ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል:- ‘ኢየሱስ፣ ትምህርቱ የመነጨው ከአምላክ ቃል ላይ እንጂ ከራሱ እንዳልሆነ በሐቀኝነት መናገር ችሏል።’ ልበ ቅን ሰዎች እውነትን ተገንዝበው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። (ዮሐንስ 7:16, 17) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
በጊልያድ የሚሰጠው ሥልጠና ለመልካም ሥራ ሁሉ ያስታጥቃል
ቀጥሎ ለረጅም ዓመታት የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሆኑት ሪቻርድ ኤብራሃምሰን እና ፓትሪክ ላ ፍራንካ በአሁኑ ጊዜ በተለያየ ዘርፍ በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማርተው ለሚገኙ ስድስት የጊልያድ ምሩቃን ቃለ ምልልስ አደረጉ። የ112ኛው ክፍል ተመራቂዎች፣ እነዚህ ስድስት ወንድሞች አሁን ያሉበት የአገልግሎት ዘርፍ ምንም ይሁን ምን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ምርምር በማድረግና ከሰዎች ጋር ተግባብቶ በመኖር ረገድ በጊልያድ ያገኙት ስልጠና ከበርካታ ዓመታት በኋላም እየጠቀማቸው መሆኑን መስማታቸው አበረታቷቸዋል።
የፕሮግራሙን ዋና ንግግር ያቀረበው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ነበር። የንግግሩ ርዕስ “የሰይጣንን ጥላቻ በጽናት መቋቋም ምን ያስገኛል?” የሚል ነበር። ባለፉት አምስት ወራት ተማሪዎቹ አፍቃሪና መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ኖረዋል። ይሁን እንጂ ክፍል ውስጥ ይሰጣቸው በነበረው ትምህርት ላይ እንደተጠቀሰው የምንኖረው ጠላት በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ነው። በመላው ዓለም የይሖዋ ሕዝቦች ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል። (ማቴዎስ 24:9) ወንድም ጃራዝ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በማውሳት ‘የዲያብሎስ ዒላማ በተለይ በእኛ ላይ አነጣጥሯል። ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከርና ፈተናዎቹን ለመቋቋም ጠንክረን መነሳት ይኖርብናል’ ሲል ገለጸ። (ኢዮብ 1:8፤ ዳንኤል 6:4፤ ዮሐንስ 15:20፤ ራእይ 12:12, 17) ወንድም ጃራዝ የአምላክ ሕዝቦች የተጠሉ ቢሆኑም ‘ኢሳይያስ 54:17 እንደሚናገረው በእኛ ላይ የተሠራ መሣሪያ አይከናወንም። ይሖዋ በወሰነው ጊዜና መንገድ ነፃ እንድንወጣ ያደርገናል’ በማለት ንግግሩን ደመደመ።
የ112ኛው ክፍል የጊልያድ ተመራቂዎች የተሟላ ‘ዝግጅት’ ያደረጉ በመሆናቸው በሚያገለግሉባቸው አገሮች ውስጥ በመንፈሳዊ ረሃብ የተጠቁ ሰዎችን ለመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የተረጋገጠ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በእነዚህ አገሮች ውስጥ እምነት ገንቢ የሆነውን መልእክት ለሰዎች እንዴት እንዳዳረሱ የሚገልጽ ሪፖርት ለመስማት በጉጉት እንጠብቃለን።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 6
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 19
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
አማካይ ዕድሜ:- 33.2
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 15.7
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12.2
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 112ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ፓሮት ኤም፣ ሁከር ኢ፣ አናያ አር፣ ሬይኖልድስ ጄ፣ ጄዝዋልዲ ኬ፣ ጎንዛሌዝ ጄ (2) ሮቢንሰን ሲ፣ ፊሊፕስ ቢ፣ ሜይድመንት ኬ፣ ሙሬ አይ፣ ኖክስ ጄ፣ ባርኔት ኤስ (3) ስታይርስ ቲ፣ ፓልመር ቢ፣ ያንግ ሲ፣ ግሩትሂስ ኤስ፣ ግሮፔ ቲ፣ ባክ ሲ (4) አናያ አር፣ ሱከሬፍ ኢ፣ ስቲዋርት ኬ፣ ሲሞዝራግ ኤን፣ ሲሞቴል ሲ፣ ባክ ኢ (5) ስቲዋርት አር፣ ያንግ ኤች፣ ጊልፊዘር ኤ፣ ሃሪስ አር፣ ባርኔት ዲ፣ ፓሮት ኤስ (6) ሜይድመንት ኤ፣ ሙሬ ጄ፣ ግሩትሂስ ሲ፣ ጊልፊዘር ሲ፣ ኖክስ ኤስ፣ ስታይርስ ቲ (7) ጄዝዋልዲ ዲ፣ ግሮፔ ቲ፣ ሱከሬፍ ቢ፣ ፓልመር ጂ፣ ፊሊፕስ ኤን፣ ሲሞቴል ጄ (8) ሃሪስ ኤስ፣ ሁከር ፒ፣ ጎንዛሌዝ ጄ፣ ሲሞዝራግ ዲ፣ ሬይኖልድስ ዲ፣ ሮቢንሰን ኤም