የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w04 2/15 ገጽ 8-9
  • መከራ ለደረሰባቸው የሚሆን ማጽናኛ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መከራ ለደረሰባቸው የሚሆን ማጽናኛ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘የሰላም አምላክ’ መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ያስባል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • 2 ቆሮንቶስ 12:9—“ጸጋዬ ይበቃሃል”
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
  • ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ይሖዋ መከራ የደረሰባቸውን ያድናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
w04 2/15 ገጽ 8-9

መከራ ለደረሰባቸው የሚሆን ማጽናኛ

ቀደም ባሉት ዘመናት መከራ ይደርስባቸው የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች አምላክ መመሪያ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ይጸልዩ ነበር። ይሁን እንጂ እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ የሚደርስባቸውን መከራ ለማቅለል አንዳንድ አስፈላጊ እርምጃዎችንም ይወስዱ ነበር። ለምሳሌ ያህል ይጨቁኗቸው ከነበሩ ሰዎች ለማምለጥ አንዳንድ ብልሃቶችን ተጠቅመዋል። ዳዊት በይሖዋ ላይ ከመታመኑ በተጨማሪ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዱ መከራውን ለመቋቋም ረድቶታል። እኛስ ዛሬ ምን ማድረግ እንችላለን?

አንድ ዓይነት መከራ ሲደርስብህ ችግሩን ለመፍታት አስፈላጊውን እርምጃ እንደምትወስድ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል ሥራ ባይኖርህ ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን ለማስተዳደር የሚያስችልህን ሥራ ለማግኘት ጥረት አታደርግም? (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ወይም ደግሞ የጤና እክል ቢገጥምህ ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት አትሞክርም? ሁሉንም ዓይነት በሽታዎች የመፈወስ ችሎታ የተሰጠው ኢየሱስ ‘ሕመምተኞች ባለ መድኃኒት’ እንደሚያስፈልጋቸው መናገሩን አስታውስ። (ማቴዎስ 9:12) ሆኖም አስፈላጊውን እርምጃ ወስደህም እንኳ ያለብህ ችግር ላይወገድ ስለሚችል ችለህ ለመኖር የምትገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ ችግርህን ለይሖዋ አምላክ ለምን በጸሎት አትነግረውም? ለምሳሌ ያህል ሥራ በምንፈልግበት ጊዜ ወደ አምላክ በመጸለይ እምነታችንን በእሱ ላይ የምንጥል ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ የሚያጓጓ ሥራ የመያዝ አጋጣሚ ቢፈጠር በዚህ ፈተና እንዳንሸነፍ ይረዳናል። በተጨማሪም በስግብግብነት መንፈስ ተነሳስተን ወይም በገንዘብ ፍቅር ተስበን ‘ከእምነት መንገድ ስተን እንዳንሄድ’ ይጠብቀናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:10 አ.መ.ት) በእርግጥም ሥራን፣ ቤተሰብን ወይም ጤናን የሚመለከቱ ከባድ ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚለውን የዳዊት ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን።—መዝሙር 55:22

በተጨማሪም ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን ስለችግራችን ብቻ በማሰብ ከልክ በላይ እንዳንጨነቅና ሚዛናችንን እንዳንስት ይረዳናል። ታማኝ ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ” ሲል ጽፏል። ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችን ሊያጽናናን የሚችለው እንዴት ነው? “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አምላክ የሚሰጠው ሰላም ከሰው ‘አእምሮ’ በላይ ነው። በመሆኑም በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንድንረጋጋ ሊያደርገን ይችላል። ‘ልባችንንና አሳባችንን ስለሚጠብቅልን’ በስሜት ተገፋፍተን ችግሩን ይበልጥ የሚያባብስ ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንዳንወስድ ይረዳናል።

ጸሎት የገጠመን ሁኔታ እንዲስተካከል በማድረግ ረገድም ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት የእምነት ባልደረቦቹ እንዲጸልዩለት ጠይቋል። ጳውሎስ እንዲጸልዩለት የጠየቀው ለምንድን ነው? “ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ” ሲል ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 13:19) በሌላ አባባል ጳውሎስ የእምነት ባልደረቦቹ ወደ ይሖዋ የማያቋርጥ ጸሎት ማቅረባቸው ቶሎ ከእስር እንዲፈታ ሊያደርገው እንደሚችል ያውቅ ነበር።—ፊልሞና 22

ጸሎት ለችግራችን መፍትሔ በማስገኘት ረገድ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? አዎን፣ ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እኛ በፈለግነው መንገድ ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ አለብን። ጳውሎስ የነበረበትን ‘የሥጋ መውጊያ’ (የጤና እክል ሊሆን ይችላል) በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ አምላክ ጸሎት አቅርቧል። ይሁን እንጂ አምላክ ችግሩን በማስወገድ ፋንታ “ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” አለው።—2 ቆሮንቶስ 12:7-9

ስለዚህ የገጠመን ችግር ወዲያውኑ ላይወገድ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ በሰማይ በሚኖረው አባታችን ላይ ምን ያህል እንደምንታመን ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:2-4) ይሖዋ አምላክ ችግራችንን ባያስወግድልን እንኳ ‘መታገሥ እንድንችል መውጫ መንገዱን እንደሚያዘጋጅልን’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ እንደሆነ አስታውስ። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) አምላክ መጽናት የሚያስችለንን ኃይል የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን።

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” ሲል ይገልጻል። (ራእይ 21:3, 4) መከራ የሌለበት ዓለም ይመጣል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው? ሕይወትህ በመከራና በችግር የተሞላ ከሆነ ይህን መቀበል ሊከብድህ ይችላል። ይሁንና ከስጋትና ከመከራ ነፃ የሆነ ዓለም እንደሚመጣ ቃል የገባው አምላክ ነው፤ የአምላክ ዓላማ ደግሞ ግቡን እንደሚመታ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳይያስ 55:10, 11

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እፎይታ ማግኘት ይቻላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ