የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 10/1 ገጽ 6-8
  • ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአእምሮ ሰላም።
  • በመከራ ጊዜ መጽናኛና ብርታት ማግኘት።
  • ከአምላክ የሚገኝ ጥበብ።
  • መጸለይህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
  • ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ምን ብለን እንጸልይ?—ጸሎት የሚባለው አቡነ ዘበሰማያት ብቻ ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 10/1 ገጽ 6-8
አንዲት ሴት ታማሚ ስለሆኑት እናቷ እያሰበች ስትጸልይ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጸለይ የሚያስገኘው ጥቅም አለ?

ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?

አንድ አዲስ ሥራ ከመጀመርህ በፊት ‘ምን ጥቅም አገኝበታለሁ?’ ብለህ ማሰብህ ያለ ነገር ነው። ይሁንና ጸሎትን በተመለከተ እንዲህ ብለህ መጠየቅህ ራስ ወዳድነት ይሆናል? በፍጹም። ጸሎት ይጠቅመን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ መፈለጋችን ምንም ስህተት የለውም። ጥሩ ሰው የነበረው ኢዮብ እንኳ “ብጠራው ይመልስልኛል?” ብሎ የጠየቀበት ወቅት ነበር።—ኢዮብ 9:16

ከዚህ በፊት ባሉት ርዕሶች ላይ ጸሎት አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም የአእምሮ ሕክምና ከመሆን ያለፈ ጥቅም እንዳለው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። እውነተኛው አምላክ በእርግጥ ጸሎት ሰሚ ነው። ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት በተገቢው መንገድ የምንጸልይ ከሆነ ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጠናል። እንዲያውም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያበረታታናል። (ያዕቆብ 4:8) ታዲያ ጸሎት የሕይወታችን ክፍል እንዲሆን ካደረግን ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን? እስቲ አንዳንዶቹን ጥቅሞች እንመልከት።

የአእምሮ ሰላም።

በሕይወትህ ውስጥ ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ በጭንቀት ትዋጣለህ? እንደዚህ ባሉት ጊዜያት ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ እና ‘ልመናችንን ለአምላክ እንድናቀርብ’ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ፊልጵስዩስ 4:6) በጸሎት ወደ አምላክ የምንቀርብ ከሆነ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅልን’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 4:7) በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ያስጨነቁንን ነገሮች በምንገልጽበት ጊዜ በተወሰነ መጠን ስሜታችን ይረጋጋል። እንዲያውም አምላክ በመዝሙር 55:22 ላይ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” በማለት ማበረታቻ ሰጥቶናል።

“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።”—መዝሙር 55:22

በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በጣም ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሰላም አግኝተዋል። በደቡብ ኮሪያ የምትኖረው ሂ ራን እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ ችግሮች ቢኖሩብኝም እንኳ ችግሮቼን ጠቅሼ ከጸለይኩ በኋላ ሸክም እንደቀለለኝ የሚሰማኝ ከመሆኑም ሌላ ለመጽናት የሚያስፈልገኝን አቅም እንዳገኘሁ ይሰማኛል።” በፊሊፒንስ የምትኖረው ሴሲልያ እንዲህ ብላለች፦ “እናት እንደመሆኔ መጠን የሴቶች ልጆቼና የእናቴ ነገር በጣም ያስጨንቀኛል፤ በአሁኑ ሰዓት እናቴ አታውቀኝም። ይሁንና ጸሎት ስለ ብዙ ነገር ሳልጨነቅ የዕለት ተዕለት ሕይወቴን እንድገፋ አስችሎኛል። ይሖዋ እነሱን መንከባከብ እንድችል እንደሚረዳኝ አውቃለሁ።”

በመከራ ጊዜ መጽናኛና ብርታት ማግኘት።

ከባድ ጭንቀት ውስጥ ነህ? አልፎ ተርፎም ለሕይወት የሚያሰጉ ወይም እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ሁኔታዎች አጋጥመውሃል? “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ወደሆነው አካል መጸለይህ ትልቅ እፎይታ ሊያመጣልህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እጅግ ከመጨነቁ የተነሳ “ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ።” ከዚያስ ምን ሆነ? “አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።” (ሉቃስ 22:41, 43) ሌላው ታማኝ ሰው ደግሞ ነህምያ ነው፤ አምላክ የሰጠውን ሥራ ለማስቆም በክፉ ዓላማ የተነሳሱ ሰዎች ዛቻ ሰንዝረውበት ነበር። ነህምያ “በዚህ ጊዜ እጆቼን አበርታልኝ ብዬ ጸለይኩ” ብሏል። ከዚህ በኋላ የተከናወኑት ነገሮች አምላክ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍና ሥራውን ዳር እንዲያደርስ በእርግጥ እንደረዳው ያሳያሉ። (ነህምያ 6:9-16) ጋና ውስጥ የሚኖረው ሬጀነልድ ከጸሎት ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በተለይ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውኝ በምጸልይበት ጊዜ እኔን መርዳት ለሚችልና ያን ያህል የምደናገጥበት ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ ለሚያጽናናኝ አካል ችግሬን እንደነገርኩ ሆኖ ይሰማኛል።” አዎን፣ አምላክ ወደ እሱ ከጸለይን ሊያጽናናን ይችላል።

ከአምላክ የሚገኝ ጥበብ።

በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች በእኛም ሆነ በቅርብ የቤተሰባችን አባላት ላይ ዘላቂ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላል። ታዲያ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው [በተለይ ፈተናዎችን ለመወጣት] ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤ ይህም ሰው ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) ጥበብ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ጥበብ የታከለባቸው ውሳኔዎች እንድናደርግ ሊመራን ይችላል። እንዲያውም ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!” ስላለን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ለይተን መጠየቅ እንችላለን።—ሉቃስ 11:13

አንድ ሰው ሲጸልይ

“ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድችል መመሪያ እንዲሰጠኝ ያለማሰለስ ጸለይኩ።”—ክዋቤና፣ ጋና

ኢየሱስ እንኳ ከባድ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት አባቱ እንዲረዳው መጠየቅ እንዳለበት ተሰምቶታል። ኢየሱስ ሐዋርያት ሆነው የሚያገለግሉትን 12 ሰዎች መምረጥ በፈለገ ጊዜ “ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 6:12

እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎችም ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ ላቀረቧቸው ልመናዎች አምላክ እንዴት መልስ እንደሰጣቸው ሲመለከቱ ተበረታተዋል። በፊሊፒንስ የምትኖረው ሬጂና ልዩ ልዩ ፈተናዎች አጋጥመዋት እንደነበር ተናግራለች፤ ለምሳሌ ባሏ ከሞተ በኋላ ለራሷና ለቤተሰቧ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት፣ ሥራ ማጣት እንዲሁም ልጆች ማሳደግ ተፈታታኝ ሆኖባት ነበር። ታዲያ ጥበብ የታከለባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው? “ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ” ብላለች። በጋና የሚኖረው ክዋቤና ወደ አምላክ የጸለየበትን ምክንያት ሲገልጽ “ጥሩ ደመወዝ የማገኝበትን የግንባታ ሥራዬን አጣሁ” ብሏል። ከፊቱ የተደቀኑትን አማራጮች በተመለከተ “ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድችል መመሪያ እንዲሰጠኝ ያለማሰለስ ጸለይኩ” ሲል ተናግሯል። አክሎም “ይሖዋ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎቶቼን እንዳሟላ የሚያስችለኝን ሥራ እንድመርጥ እንደረዳኝ አምናለሁ” ብሏል። አንተም ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ሊነኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጸሎትህ በመጥቀስ የእሱን አመራር ማግኘት ትችላለህ።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ነጥቦች ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። (ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት “ጸሎት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁንና እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት በመጀመሪያ አምላክን እንዲሁም የእሱን ፈቃድ ማወቅ ያስፈልግሃል። ይህን የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።a እንዲህ ማድረግህ “ጸሎት ሰሚ” ወደሆነው አምላክ ለመቅረብ የምትወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል።—መዝሙር 65:2

a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም www.jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።

ጸሎት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

የአእምሮ ሰላም “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ከአምላክ የሚገኝ ማጽናኛ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ . . . እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ መመሪያ ማግኘት “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤ ይህም ሰው ይሰጠዋል።”—ያዕቆብ 1:5

ከፈተና እንድንርቅ እርዳታ ማግኘት “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ።”—ሉቃስ 22:40

የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት “በስሜ የተጠሩትም ሕዝቤ ራሳቸውን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢሹና ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ፣ ከሰማያት ሆኜ እሰማለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ።”—2 ዜና መዋዕል 7:14

ሌሎችን ለመርዳት “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።”—ያዕቆብ 5:16

ጸሎታችን መልስ በማግኘቱ የምናገኘው ማበረታቻ “ይሖዋም [ሰለሞንን] እንዲህ አለው፦ ‘በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት ያቀረብከውን ልመና ሰምቻለሁ።’”—1 ነገሥት 9:3

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ