መልካም ባሕርይ ጥሩ ፍሬ ያፈራል
ከደቡብ ጃፓን ባሕር ዳርቻ ብዙም በማትርቅ ደሴት ውስጥ አንዲት እናትና ሦስት ልጆቿ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በዚህች ገለልተኛና ወግ አጥባቂ በሆነች ትንሽ ደሴት ላይ የሚኖሩት ሰዎች እናትየዋን ፊት ይነሷት ጀመር። “ፊት ስለነሱኝ ብዙም አልከፋኝም፤ ይበልጥ ያሳዘነኝ ባለቤቴንና ልጆቼን ማኩረፋቸው ነበር” ስትል ተናግራለች። ያም ሆኖ ለልጆቿ “የአካባቢያችንን ሰዎች ለይሖዋ ስንል ሰላም ልንላቸው ይገባል” ትላቸው ነበር።—ማቴዎስ 5:47, 48
ሰዎች ጥሩ ምላሽ ባይሰጧቸውም እንኳ እነርሱ ሥርዓታማ መሆን እንዳለባቸው ልጆቿን ቤት ውስጥ ታሠለጥናቸዋለች። በአካባቢያቸው ወደሚገኘው ፍልውሃ መታጠቢያ ቤት በየጊዜው ሲሄዱ ለሰዎች የሚያቀርቡትን ሰላምታ መኪና ውስጥ ይለማመዱ ነበር። ሁሌም ወደ ሕንጻው ሲገቡ “ኮኒቺዋ!” ማለትም “መልካም ቀን!” እያሉ በፈገግታ ሰላምታ ይሰጡ ነበር። ሰዎቹ ኮስተር እያሉባቸውም እንኳ ያገኙትን ሰው ሁሉ በትዕግሥት ሰላም ማለታቸውን ቀጠሉ። በመሆኑም ሰዎቹ፣ ልጆቹ መልካም ባሕርይ እንዳላቸው አስተዋሉ።
ከጊዜ በኋላ የአካባቢው ሰው ቀስ በቀስ “ኮኒቺዋ” በማለት ምላሽ መስጠት ጀመረ። ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ የከተማው ሰው በሙሉ ማለት ይቻላል ከቤተሰቡ ጋር ሰላም ይባባል ነበር። እንዲያውም ሰዎቹ እርስ በርስ ሰላምታ መሰጣጣትና የበለጠ መግባባት ጀመሩ። ምክትል ከንቲባው ልጆቹ ይህን ለውጥ በማምጣት ረገድ ለተጫወቱት ሚና ሽልማት ሊሰጧቸው ፈልገው ነበር። ሆኖም እናታቸው ልጆቿ ክርስቲያኖች ስለሆኑ ማድረግ የሚገባቸውን እንዳደረጉ ነገረቻቸው። ከጊዜ በኋላ በደሴቲቱ ውስጥ በተካሄደ የንግግር ውድድር ላይ አንደኛው ልጅ የሰዎች ምላሽ ጥሩ ባይሆንም እንኳ ሰላምታ ሊሰጡ እንደሚገባ እናቱ ቤተሰቡን እንዴት እንዳሠለጠነች ተናገረ። ልጁ በዚህ ንግግር አንደኛ ወጥቶ የተሸለመ ሲሆን ንግግሩ ደግሞ በከተማው በሚታተም ጋዜጣ ላይ ሊወጣ ችሏል። ይህ ቤተሰብ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተከትሎ እንዲህ ያሉ መልካም ውጤቶችን በማግኘቱ ደስተኛ ነው። ተግባቢ ለሆኑ ሰዎች መልካሙን ምሥራች ማካፈል ይበልጥ ቀላል ነው።