ከትዳር ጓደኛህ ጋር በግልጽ ለመነጋገር የሚረዱ ነጥቦች
‘እንዲህ ማለት አልነበረብኝም።’ ‘እንደዚያ ማለቴ እኮ አይደለም።’ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለመነጋገር ሞክረህ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? በግልጽ መነጋገር ሊዳብር የሚገባው ችሎታ ነው። አንዳንዶች በዚህ ረገድ የተዋጣላቸው ሲሆኑ ሌሎች ግን ይህን ችሎታ ማዳበር ይከብዳቸዋል። ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ከሚያስቸግራቸው ሰዎች መካከል ብትሆንም እንኳ ሐሳብህን በሚያስደስት መልኩ መግለጽን መማር ትችላለህ።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ በአካባቢያቸው ያለው ባሕል ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። በአንዳንድ ባሕሎች ወንዶች ‘ብዙ ማውራት የለባችሁም’ ይባሉ ይሆናል። ወሬ የሚወዱ ወንዶች ቁም ነገረኛ እንዳልሆኑ ተቆጥረው ሊናቁ ይችላሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . ይሁን” ይላል። (ያዕቆብ 1:19) ሆኖም ይህ ምክር ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የሚሠራ ሲሆን የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ከመናገር የበለጠ ነገርንም እንደሚጨምር ያሳያል። ሁለት ሰዎች ለረጅም ሰዓታት ሊያወሩ ይችላሉ፤ ሆኖም እርስ በርስ ባይደማመጡስ? በመካከላቸው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሊኖር አይችልም። ከላይ ያለው ጥቅስ እንደሚያሳየው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ከሁሉ የላቀው ነገር የማዳመጥ ችሎታ ነው።
ሳይነጋገሩ መግባባት
በአንዳንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ሚስቶች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ እንደሌለባቸው ይታሰባል። ባሎች ደግሞ በቤተሰብ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። እንደዚህ በመሰለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ባልና ሚስት የትዳር ጓደኛቸው ምን እንደሚፈልግ አያውቁም። አንዳንድ ሚስቶች የባሎቻቸውን ፍላጎት አስተውለው የሚያስፈልገውን ነገር ወዲያውኑ ማሟላት ይችላሉ። እንዲህ ባለው ባሕል ውስጥ ባልና ሚስቱ ሳይነጋገሩ ይግባባሉ። ሆኖም በእንዲህ ዓይነቱ የሐሳብ ግንኙነት ሐሳቡን የሚገልጸው አንደኛው ወገን ብቻ ይሆናል። ሚስትየዋ ባሏ ምን እንደሚያስብ ወይም ምን እንደሚሰማው መረዳትን ትለምድ ይሆናል፤ ባልየው ግን የሚስቱ ዓይነት ችሎታ በማዳበር ስሜቷን እንዲያስተውል አይጠበቅበትም።
እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ባሕሎች ወንዶች የሴቶችን ስሜታዊ ፍላጎት በመገንዘብ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ይጥሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእንዲህ ዓይነቱ ባሕል ውስጥም እንኳ ባለትዳሮች ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረጋቸው ይጠቅማቸዋል።
በግልጽ መነጋገር አስፈላጊ ነው
በግልጽ መነጋገር አለመግባባት እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ይጠብቃል። የጥንት እስራኤላውያን ታሪክ እንደሚያሳየው ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩት የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ “ግዙፍ መሠዊያ” ሠርተው ነበር። ሌሎቹ ነገዶች ድርጊታቸውን በተሳሳተ መንገድ ተረዱት። በምዕራቡ በኩል ያሉት ነገዶች፣ በዮርዳኖስ ማዶ ያሉት ወንድሞቻቸው የክህደት እርምጃ እንደወሰዱ በማሰብ “ዐመፀኞቹን” ለመውጋት ተዘጋጁ። ሆኖም ወደ ውጊያው ከመዝመታቸው በፊት በስተ ምሥራቅ በኩል የሚገኙትን ነገዶች ለማነጋገር ተወካዮችን ላኩ። ይህ እንዴት ያለ የጥበብ ድርጊት ነበር! መልእክተኞቹ መሠዊያው ከይሖዋ ሕግ ጋር የሚጋጭ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ የሚያገለግል አለመሆኑን ተገነዘቡ። ከዚህ ይልቅ በስተ ምሥራቅ ያሉት ነገዶች፣ ወደፊት ሌሎቹ ነገዶች “ከእግዚአብሔር ዘንድ ድርሻ የላችሁም” እንዳይሏቸው በመፍራት የሠሩት መሠዊያ ሲሆን ይህ ደግሞ እነርሱም የይሖዋ አምላኪዎች እንደሆኑ የሚያሳይ ምሥክር ነበር። (ኢያሱ 22:10-29) መሠዊያው፣ ይሖዋ ለእነሱ እውነተኛ አምላክ መሆኑን ስለሚያሳውቅ ምሥክር ብለው ጠሩት።—ኢያሱ 22:34
የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ያቀረቡት ምክንያት ሌሎቹን ነገዶች ስላሳመናቸው በእነርሱ ላይ ሊወስዱት ያሰቡትን እርምጃ ተዉት። በእርግጥም በግልጽ መነጋገራቸው ከመዋጋት ጠብቋቸዋል። ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ምሳሌያዊ ባላቸው በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ ባመጹ ጊዜ፣ እርሱ ምሕረት አድርጎላቸው ‘በፍቅር ቃል እንደሚያነጋግራቸው’ ተገልጿል። (ሆሴዕ 2:14) ለተጋቡ ሰዎች የሚሆን እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! የትዳር ጓደኛችሁ ስሜታችሁን እንዲረዳላችሁ ከፈለጋችሁ የልባችሁን አውጥታችሁ ተነጋገሩ። በተለይ ደግሞ ነገሩ ከስሜት ጋር የተያያዘ ከሆነ እንዲህ ማድረጋችሁ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ፓቲ ሚሃሊክ የተባለች ጋዜጠኛ እንዲህ ብላለች:- “ሰዎች ሐሳብን በንግግር መግለጽ ብዙም ጥረት እንደማይጠይቅ ይናገራሉ፤ ሆኖም ቃላት በገንዘብ ሊተመን የማይችል ዋጋ ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንዶች ስሜታቸውን መግለጽ ቢያስቸግራቸውም ውጤቱ ግን በባንክ ከተቀመጠ ገንዘብ የሚበልጥ ነው።”
በግልጽ የመነጋገር ችሎታ አዳብሩ
አንዳንዶች ‘ትዳራችን ገና ከጅምሩ ችግር ነበረው’ ይሉ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ‘ይህ ትዳር መፍረሱ አይቀርም’ የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። አንዳንድ ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ በግልጽ የመነጋገር ችሎታን ማሻሻል ፈጽሞ የማይቻል ነገር ሊመስላቸው ይችላል። ሆኖም የትዳር ጓደኛቸውን ቤተሰቦቻቸው የሚመርጡላቸውን ሰዎች አስብ። እንደዚህ ዓይነት ባሕል ባለበት አካባቢ የሚገኙ በርከት ያሉ ሰዎች በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ እያደር በግልጽ የመነጋገር ችሎታን ማዳበር ችለዋል።
በሩቅ ምሥራቅ በሚገኝ አገር ውስጥ ለሚኖር አንድ ሰው ሚስት ያመጡለት ቤተሰቦቹ ነበሩ። አንድ አገልጋይ ረጅም ጉዞ አድርጎ ለሰውየው ሚስት እንዲፈልግ ተልኮ ነበር። ያም ቢሆን ግን ከ4,000 ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩት እነዚህ ባልና ሚስት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ችሎታ አዳብረዋል። ይህ ሰው ማለትም ይስሐቅ፣ አገልጋዩንና የወደፊት ሚስቱን ያገኛቸው በሜዳ ነበር። አገልጋዩም “ያደረገውን ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው።” ይህን ጋብቻ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ይስሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባትም፤ ሚስት ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት።”—ዘፍጥረት 24:62-67
ይስሐቅ አገልጋዩን ካዳመጠ በኋላ ርብቃን ሚስቱ አድርጎ መውሰዱን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ አገልጋይ ታማኝና ይስሐቅ ያመልከው ለነበረው ለይሖዋ አምላክ ያደረ ሰው ነበር። ይስሐቅ ይህንን ሰው ለማመን አጥጋቢ ምክንያት ነበረው። ከዚያ በኋላ ይስሐቅ ሚስቱን ርብቃን “ወደዳት።”
ታዲያ ይስሐቅና ርብቃ በግልጽ የመነጋገር ልማድ ነበራቸው? ዔሳው የተባለው ልጃቸው ኬጢያውያን የሆኑ ሁለት ሴቶችን ካገባ በኋላ በቤተሰቡ ውስጥ ከባድ ችግር ተከሰተ። ርብቃ ይስሐቅን “‘ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም [ታናሹ ልጃቸው] . . . ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ’ አለችው።” (ዘፍጥረት 26:34፤ 27:46) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ርብቃ የሚያሳስባትን ሁሉ አንድም ሳይቀር በግልጽ ነግራዋለች።
ይስሐቅ የዔሳው መንትያ ለሆነው ለያዕቆብ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስት እንዳያገባ ነገረው። (ዘፍጥረት 28:1, 2) ርብቃ መልእክቷን አስተላልፋለች። እነዚህ ባልና ሚስት አሳሳቢ ስለነበረው የቤተሰብ ጉዳይ በግልጽ በመነጋገር ረገድ በዛሬ ጊዜ ላለነው ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛሞች በአንድ ጉዳይ ላይ ባይስማሙ ምን ማድረግ ይችላሉ?
አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ
በእናንተና በትዳር ጓደኛችሁ መካከል ከባድ አለመግባባት ሲፈጠር የትዳር ጓደኛችሁን አታኩርፉት። ካኮረፋችሁት ደስተኛ አለመሆናችሁንና የትዳር ጓደኛችሁም ደስተኛ እንዲሆን እንደማትፈልጉ የሚጠቁም ግልጽ የሆነ መልእክት እያስተላለፋችሁ ነው። እንደዚያም ሆኖ የትዳር ጓደኛችሁ ምን እንደምትፈልጉና ውስጣችሁ ምን እንደሚሰማችሁ ሙሉ በሙሉ ላይረዳላችሁ ይችላል።
ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ጉዳዩ የትዳር ጓደኛችሁን የሚያበሳጨው ከሆነ ለማረጋጋት ቀላል ላይሆን ይችላል። የይስሐቅ ወላጆች የሆኑት አብርሃምና ሣራ በአንድ ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ተደቅኖባቸው ነበር። ሣራ መካን ስለነበረች በዚያን ጊዜ የነበረውን ልማድ በመከተል ልጅ እንድትወልድለት አገልጋይዋን አጋርን ቁባት አድርጋ ለባሏ ሰጠችው። አጋር ለአብርሃም እስማኤል የተባለ ወንድ ልጅ ወለደችለት። ይሁን እንጂ ከዚያ ቆየት ብሎ ሣራ ያረገዘች ሲሆን ለአብርሃም ይስሐቅ የተባለ ወንድ ልጅ ወለደችለት። ይስሐቅ ጡት በሚጥልበት ጊዜ ሣራ፣ እስማኤል በልጅዋ ላይ ሲያፌዝበት ተመለከተች። በዚህም ምክንያት ሣራ ልጅዋ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደተጋረጠበት ስለተገነዘበች አገልጋይዋን አጋርንና እስማኤልን እንዲያባርራቸው ለአብርሃም ነገረችው። አዎን፣ ሣራ ምን እንደተሰማት በግልጽ ተናግራለች። ሆኖም የጠየቀችው ነገር አብርሃምን በጣም አሳዘነው።
ታዲያ አለመግባባቱ እንዴት ተፈታ? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ ‘ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ አሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ።’” አብርሃምም የይሖዋ አምላክን መመሪያ በመስማት ተገቢውን እርምጃ ወስዷል።—ዘፍጥረት 16:1-4፤ 21:1-14
‘እኛም፣ አምላክ ከሰማይ የሚናገረን ከሆነ በቀላሉ ልንስማማ እንችላለን!’ ትል ይሆናል። ይህ ደግሞ በትዳር ውስጥ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ወደሚረዳን ወደ ሌላኛው ነጥብ ይወስደናል። ባልና ሚስት አምላክን መስማት ይችላሉ። እንዴት? የአምላክን ቃል አንድ ላይ በማንበብና ያነበቡትንም ከአምላክ እንደተሰጣቸው መመሪያ አድርገው በመቀበል ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13
አንዲት የጎለመሰች ክርስቲያን ሚስት እንዲህ ትላለች:- “ብዙ ጊዜ አንዲት ወጣት ሴት ስለ ትዳሯ ምክር ለመጠየቅ ወደ እኔ ስትመጣ፣ እሷና ባሏ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ያነቡ እንደሆነ እጠይቃታለሁ። በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያለባቸው ብዙዎቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አብረው የማንበብ ልማድ የላቸውም።” (ቲቶ 2:3-5) ይህች እህት ከሰጠችው አስተያየት ሁላችንም መጠቀም እንችላለን። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ዘወትር የአምላክን ቃል አንብቡ። በዚህ መንገድ በሕይወታችሁ ውስጥ የሚያስፈልጋችሁን መመሪያ ከአምላክ ‘ትሰማላችሁ።’ (ኢሳይያስ 30:21) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን፣ የትዳር ጓደኛችሁ በሥራ አያውላቸውም ብላችሁ የምታስቧቸውን ጥቅሶች በተደጋጋሚ እያወጣችሁ ለመውቀስ አትጠቀሙበት። ከዚህ ይልቅ ሁለታችሁም ያነበባችሁትን በተግባር ለማዋል የምትችሉበትን መንገድ ፈልጉ።
ከባድ ችግር አጋጥሟችሁ ለመወጣት እየሞከራችሁ ከሆነ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫንa (እንግሊዝኛ) በመጠቀም የሚያሳስቧችሁን ጉዳዮች ለምን ከዚያ ላይ አትመለከቷቸውም? ምናልባት በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መንከባከብ በትዳራችሁ ውስጥ ውጥረት ፈጥሮባችሁ ይሆናል። የትዳር ጓደኛችሁ ማድረግ ስላለበትና ስለሌለበት ነገር አንስቶ ከመጨቃጨቅ ይልቅ ማውጫውን አንድ ላይ ሆናችሁ ለምን አትመለከቱትም? በመጀመሪያ “ወላጆች” የሚለውን ዋና ርዕስ አውጥታችሁ ተመልከቱ። “በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መንከባከብ” እንደሚለው ባሉት ንዑስ ርዕሶች ሥር በተጠቀሱት ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረግ ትችላላችሁ። ተመሳሳይ ትምህርቶችን ይዘው የወጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን አንድ ላይ ሆናችሁ አንብቧቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ሐሳብ ቅን ልብ ያላቸውን በርካታ ክርስቲያኖች እንደረዳ ሁሉ አንተንም ሆነ የትዳር ጓደኛህን ምን ያህል ሊጠቅማችሁ እንደሚችል ስትመለከት ትገረማለህ።
በማውጫው ላይ የተጠቀሱትን ጽሑፎች አውጥታችሁ አንድ ላይ ሆናችሁ ማንበባችሁ ችግሮቻችሁ ምን እንደሆኑ ለማገናዘብ ይረዳችኋል። የአምላክ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት ትችላላችሁ። ጥቅሶቹን እያወጣችሁ አንድ ላይ አንብቧቸው። እንዲህ በማድረግ እየተጋፈጣችሁ ስላላችሁት ችግር አምላክ ምን እንደሚል ትሰማላችሁ!
በግልጽ የመነጋገር ልማድ ይኑራችሁ
ለብዙ ጊዜያት ሳይከፈት የቆየን በር ለመክፈት ሞክረህ ታውቃለህ? በሩ ቀስ እያለ መከፈት ሲጀምር የዛጉት ማጠፊያዎች ሲጢጥ የሚል ድምፅ ያሰማሉ። ሆኖም በሩ ሁልጊዜ የሚከፈትና የሚዘጋ እንዲሁም ማጠፊያዎቹ ዘይት የሚቀቡ ቢሆንስ? በሩን መክፈት ቀላል ይሆን ነበር። በግልጽ መነጋገርን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በግልጽ የመነጋገር ልማድ ካላችሁና የበር ማጠፊያ ዘይት እንደሚቀባ ሁሉ ግንኙነታችሁ በክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲለሰልስ ካደረጋችሁት ከባድ አለመግባባት ቢኖርም እንኳ ሐሳባችሁን በቀላሉ መግለጽ ትችላላችሁ።
በግልጽ የመነጋገር ችሎታ ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው። ይህን ችሎታ ማዳበር ጥረት የሚጠይቅ ሊሆን ቢችልም ተስፋ አትቁረጡ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በቀላሉ ለመነጋገር ትችላላችሁ፤ ይህ ደግሞ ዘላቂ የሆነ መግባባት እንዲኖር ያስችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አለመግባባት ሲፈጠር የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ትጥራለህ?