ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለተሳካ ትዳር ቁልፍ ነው
በ1778 ሮበርት ባሮን በአንድ ጊዜ ሁለት ቁልፎች በመጠቀም የሚከፈት ቁልፍ ፈለሰፈ። ይህ ዛሬ ላሉት ቁልፎች መሠረት ጥሏል። የእርሱ ፈጠራ የቁልፉን ሁለት መቀተሪያዎች በአንድ ጊዜ ለመመለስ የሚችል አንድ ቁልፍ መጠቀምን የሚጠይቅ ነበር።
በተመሳሳይም ትዳርን ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው ባልና ሚስት በአንድነት ተባብረው ሲሠሩ ነው። የተሳካ ትዳርን በር ለመክፈትና ከፍተኛ ደስታ ለማግኘት አንዱ አስፈላጊ ነገር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ነው።
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ምን ነገሮችን ይጨምራል? አንድ መዝገበ ቃላት የሐሳብ ግንኙነትን “በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በምልክት ሐሳብን፣ አስተያየትን ወይም መረጃን ማስተላለፍ ወይም መለዋወጥ” ሲል ይፈታዋል። ስለዚህ የሐሳብ ግንኙነት ስሜትንና ሐሳብን ማካፈልን ይጨምራል። ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ደግሞ የሚያንጹ፣ መንፈስን የሚያድሱ፣ በጎ፣ ጥሩና የሚያጽናኑ ነገሮችን መናገርን ያጠቃልላል።—ኤፌሶን 4:29-32፤ ፊልጵስዩስ 4:8
መተማመንና የጋራ መግባባት ካለ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ያሉት ባሕርያት የሚመጡት ጋብቻን የእድሜ ልክ ዝምድና አድርገው ሲመለከቱትና የተሳካ እንዲሆንም ልባዊ ጥረት ሲኖር ነው። የ18ኛው መቶ ዘመን ደራሲ የሆኑት ጆሴፍ አዲሰን ይህን ዓይነቱን ግንኙነት በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሁለት ሰዎች እርስ በርስ ለመጽናናትና ደስታቸውን ለመጋራት በትዳር መቆራኘታቸው አንዳቸው የሌላውን ድክመትና ጠንካራ ጎን ግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ተጫዋች፣ ተወዳጅ፣ አስተዋይ፣ ይቅር ባይ፣ ታጋሽና ደስተኛ ለመሆን መጣመራቸውን ያሳያል።” እንዲህ ያለው ጥምረት እንዴት ደስታ የሰፈነበት ነው! በጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አማካኝነት እነዚህን እንቁ መሳይ ባሕርያት የራሳችሁ በማድረግ ትዳራችሁን ማራኪ ልታደርጉት ትችላላችሁ።
ለጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ዕንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች
ብዙዎቹ ተጋቢዎች ወደ ትዳር ዓለም የሚገቡት በደስታና ብሩህ አመለካከት በመያዝ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎች የነበራቸው ብሩህ አመለካከትም ሆነ ደስታ ወዲያው እንደ ጉም በኖ ሲጠፋ ይመለከታሉ። ቀደም ሲል ትዳራቸው አስደሳች እንደሚሆን የነበራቸው ጠንካራ እምነት ጠፍቶ በምትኩ ተስፋ መቁረጥ፣ ብስጭት፣ አለመግባባት አልፎ ተርፎም የከረረ ጥላቻ ሊነግሥ ይችላል። በዚህ ጊዜ ጋብቻው ‘ሞት እስኪለያቸው ድረስ’ ከፍተኛ ጽናትን የሚጠይቅ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ለተሳካ ትዳር አስፈላጊ የሆነውን ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማሻሻል ወይም ጠብቆ ለማቆየት አንዳንድ ዕንቅፋቶች መወገድ ይኖርባቸዋል።
ለጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ዕንቅፋት የሆነው ዋነኛው ነገር ለትዳር ጓደኛዬ አንዳንድ ነገሮችን ብነግረው ወይም የምፈልገውን ነገር ብገልጽለት መጥፎ ምላሽ ሊሰጠኝ ይችላል የሚል ፍርሃት ነው። ለምሳሌ ያህል አንዱ የትዳር ጓደኛ ከባድ ወደሆነ የአካል ጉዳት እያመራ እንዳለ ካወቀ የትዳር ጓደኛዬ ለእኔ ያለው አመለካከት ይለወጣል የሚል ፍርሃት ሊያድርበት ይችላል። አንድ ሰው ወደፊት መልኩን ወይም የመሥራት ችሎታውን ሊያበላሽ የሚችል ሁኔታ ዛሬ ቢያጋጥመው ጉዳዩን ለትዳር ጓደኛው የሚገልጸው እንዴት ነው? እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ምንም ሳይደባበቁ መነጋገርና ስለ ወደፊቱ ጊዜ የታሰበበት ዕቅድ ማውጣቱ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በየጊዜው ፍቅርን በቃላትና በድርጊት መግለጽ አንዱ ለሌላው ያለውን ስሜት ስለሚያሳይ ትዳርን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ይረዳል። “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” የሚለው ምሳሌ በትዳር ውስጥ ሊሠራ ይገባዋል።—ምሳሌ 17:17
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆነው ሌላው ነገር ቅሬታ ነው። ደስታ የሰፈነበት ትዳር የሁለት ጥሩ ይቅር ባዮች ጥምረት ውጤት ነው መባሉ ተገቢ ነው። ከዚህ አባባል ጋር ለመስማማት ተጋቢዎቹ ሐዋርያው ጳውሎስ “በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” ሲል የሰጠውን ተግባራዊ ምክር ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው። (ኤፌሶን 4:27) ቁጣን ወይም ቅሬታን በሆድ አምቆ ከመያዝ ይልቅ ይህን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል በትህትና መነጋገር ያስፈልጋል። ጥሩ ትዳር ያላቸው ሰዎች በትዳራቸው ውስጥ ንዴት፣ ጠብና ቂም እንዲኖር አይፈቅዱም። (ምሳሌ 30:33) ቂም የማይዘውን አምላክ ለመምሰል ይፈልጋሉ። (ኤርምያስ 3:12) እርስ በርስ ደግሞ ከልባቸው ይቅር ይባባላሉ።—ማቴዎስ 18:35
ለማንኛውም ዓይነት የሐሳብ ግንኙነት ግልጽ የሆነው ዕንቅፋት መኮራረፍ ነው። ይህም ምናልባት ፊትን ማጨፍገግን፣ መበሳጨትን፣ እየተነጫነጩ መሥራትንና የአንድ ወገን ኩርፊያን ይጨምር ይሆናል። እንዲህ የሚያደርግ የትዳር ጓደኛ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ እየገለጸ ነው። ነገር ግን ተኮራርፎ ዝም ከማለት ይልቅ ስሜትን አውጥቶ ግልጽና ማራኪ በሆነ ሁኔታ መነጋገር ትዳር እንዲሻሻል በእጅጉ ይረዳል።
በትዳር ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት የሚሆነው ሌላው ነገር የትዳር ጓደኛ በሚናገርበት ጊዜ በጥሞና አለማዳመጥ ወይም ጨርሶ ጆሮ አለመስጠት ነው። ሥራ በዝቶብን ወይም በጣም ደክሞን ከሆነ እርስ በርስ በጥሞና ለመደማመጥ በአእምሮም ሆነ በስሜት ዝግጁ ላንሆን እንችላለን። አንደኛው ወገን ከትዳር ጓደኛው ጋር በአንድ ጉዳይ ላይ በደንብ ተግባብተው እንደነበረ ሲያስብ ሌላኛው ወገን ግን ጉዳዩ ፈጽሞ አዲስ ሊሆንበት ይችላል። በዚህ ጊዜ ጭቅጭቅ ሊነሳ ይችላል። እንደዚህ ላሉት ችግሮች መንስኤው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት አለመኖር እንደሆነ ግልጽ ነው።
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማዳበር የሚቻልበት መንገድ
ፍቅር የሰፈነበት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ጊዜ መዋጀት በጣም አስፈላጊ ነው! አንዳንዶች በቴሌቪዥን ፊት ተደቅነው የሌሎች ሰዎችን ሕይወት በመመልከት ብዙ ጊዜ ስለሚያጠፉ ለራሳቸው ሕይወት ጊዜ የላቸውም። ስለዚህ ቴሌቪዥኑን መዝጋቱ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በር የሚከፍት አስፈላጊ እርምጃ ነው።
ለመናገር ትክክለኛ ጊዜ እንዳለው ሁሉ ዝም ለማለትም ጊዜ አለው። ጠቢቡ ሰው እንዲህ ብሏል: “ለሁሉ ዘመን አለው . . . ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው።” ደግሞም ለመናገር የምንመርጣቸው ተገቢ የሆኑ ቃላት ይኖራሉ። አንድ ምሳሌ “ቃልም በጊዜው [“በትክክለኛው ጊዜ፣” NW] ምንኛ መልካም ነው!” በማለት ያስገነዝባል። (መክብብ 3:1,7፤ ምሳሌ 15:23) ስለዚህ ልትናገረው የፈለግከውን ነጥብ ወይም የልብህን ጭንቀት ለመግለጽ በጣም ጥሩ የሆነውን ጊዜ ምረጥ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የትዳር ጓደኛዬ ደክሞታል ወይስ ዘና ባለ ሁኔታ ላይ ነው ያለው? ላነሳው የፈለግሁት ርዕስ የሚያስደነግጥ ነውን? በዚህ ጉዳይ ላይ በተነጋገርንበት ወቅት ባለቤቴ በቃላት አመራረጤ ረገድ ምን የተቃወመኝ ነገር ነበረ?’
ሰዎች ከተጠየቁት ነገር ጋር መተባበራቸው ወይም የተጠየቁትን ነገር መፈጸማቸው እነሱን ራሳቸውን እንዴት እንደሚጠቅማቸው ከተገነዘቡ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ማስታወሱ ጥሩ ነው። በትዳር ጓደኛሞች መካከል የሆነ ቅራኔ ከተፈጠረ አንዳቸው እንዲህ ለማለት ይገፋፋ ይሆናል፣ “በመካከላችን አንድ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፤ ስለዚህ አሁኑኑ ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን!” እርግጥ ትክክለኛ የቃላት ምርጫ በሁኔታዎች ላይ ሊመካ ቢችልም እንዲህ ማለቱ ግን የበለጠ የተሻለ ሊሆን ይችላል፣ “የኔ ውድ ባለፈው ስለተነጋገርንበት ጉዳይና እንዴት ልንፈታው እንደምንችል ሳስብ ነበር።” የትዳር ጓደኛችሁ የትኛውን አቀራረብ የበለጠ ይመርጣል ብላችሁ ታስባላችሁ?
አዎን፣ አነጋገር ወሳኝነት አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል: “ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) የድምፃችሁ ቃና እና የቃላት ምርጫችሁ ለጆሮ የሚጥም እንዲሆን ጣሩ። ‘ያማረ ቃል እንደ ማር ወለላ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና’ እንደሆነ አስታውሱ።—ምሳሌ 16:24
አንዳንድ ባልና ሚስቶች በቤት ውስጥ የተወሰኑ ሥራዎችን አብረው መሥራታቸው የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር የሚያስችል ጥሩ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው ይችላል። እንዲህ መተባበሩ የሐሳብ ልውውጥን በማዳበር ለጥሩ ውይይት ጊዜ ያስገኛል። ለሌሎች ባለ ትዳሮች ደግሞ፣ ከሥራ አርፈው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል ለብቻቸው የሚሆኑበት ፀጥ ያለ ጊዜ ማግኘታቸው የተሻለ ነው።
ተስማምተው የሚኖሩ የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው እንዴት የሐሳብ ግንኙነት እንደሚያደርጉ በመመልከት ብዙ ነገር መማር ይቻላል። እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ያላቸው ስምምነትና በቀላሉ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ መቻላቸው ከግል ጥረታቸው፣ ከታጋሽነታቸውና ከፍቅራዊ አሳቢነታቸው የመነጨ እንደሆነ አያጠራጥርም። ጥሩ ትዳር ወዲያውኑ የሚገኝ ነገር ስላልሆነ እነርሱ ራሳቸው ብዙ የሚማሩት ነገር እንደነበር በግልጽ ማየት ይቻላል። እንዲህ ከሆነ የትዳር ጓደኛችሁን አስተያየት ከግምት ውስጥ ማስገባት፣ የሱን ወይም የሷን ፍላጎት መገንዘብና ሊጎዱ የሚችሉ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ትክክለኛ ቃላት ተጠቅሞ ማብረድ ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 16:23) ያገባችሁ ከሆናችሁ አብረዋችሁ ለመኖር የማትከብዱና በቀላሉ ይቅር የምትሉ ለመሆን ጣሩ። ይህ ደግሞ ትዳራችሁ በእርግጥ ጥሩ እንዲሆን ይረዳችኋል።
ይሖዋ አምላክ ሰዎች ደስታ የሰፈነበት ዘላቂ ትዳር እንዲኖራቸው ይፈልጋል። (ዘፍጥረት 2:18, 21) ነገር ግን ቁልፉ ያለው በጋብቻ በተጣመሩት ሰዎች እጅ ነው። ወደ ተሳካ ትዳር የሚያስገባውን በር ከፍቶ ለመግባት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የማድረግን ጥበብ የተካኑ በቅንጅት የሚሠሩ ሁለት የሚፋቀሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቴሌቪዥኑን መዝጋት የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ እንዲኖር ያደርጋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ዘላቂ በሆነ ፍቅር ለመጣመር ይረዳል