የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w08 8/1 ገጽ 6-8
  • በቅርቡ ምድር ገነት ትሆናለች!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቅርቡ ምድር ገነት ትሆናለች!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እውን መስተዳድር
  • ‘ምድርን የሚያጠፏትን ማጥፋት’
  • ገነት ዳግመኛ ትቋቋማለች
  • አሳማኝ ምክንያቶች
  • የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን አስተምሯል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • የአምላክን መንግሥት በተመለከተ እውነቱ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2020
  • የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
w08 8/1 ገጽ 6-8

በቅርቡ ምድር ገነት ትሆናለች!

“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።” —ማቴዎስ 6:9, 10

በብዙዎች ዘንድ “አባታችን ሆይ” ወይም “አቡነ ዘበሰማያት” ተብሎ የሚታወቀው ይህ ጸሎት ለሰው ዘር ተስፋ ይፈነጥቃል። እንዴት?

ይህ ጸሎት የአምላክ መንግሥት፣ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንዲፈጸም እንዳደረገ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም እንደሚያደርግ ማረጋገጫ ይሰጣል። የአምላክ ፈቃድ ደግሞ ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥ ነው። (ራእይ 21:1-5) የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ምድርን ወደ ገነትነት የሚለውጠውስ እንዴት ነው?

እውን መስተዳድር

የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር ነው። አንድ መንግሥት ገዥዎች፣ ሕግጋትና ተገዥዎች ሊኖሩት ይገባል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት እነዚህን ብቃቶች ያሟላል? መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ተመልከት:-

የአምላክ መንግሥት ገዥዎች እነማን ናቸው? (ኢሳይያስ 33:22) ይሖዋ አምላክ፣ መንግሥቱን በበላይነት እንዲቆጣጠር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሾሞታል። (ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስ ደግሞ በይሖዋ አመራር ሥር ሆኖ ከእሱ ጋር ‘በምድር ላይ የሚነግሡ’ የተወሰኑ ሰዎችን ‘ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከወገንና ከሕዝብ’ መርጧል።—ራእይ 5:9, 10

የአምላክ መንግሥት ተገዥዎቹ እንዲታዘዙት የሚጠብቅባቸው ምን ሕጎች አሉት? አንዳንዶቹ ሕጎች እርምጃ መውሰድን የሚጠይቁ ናቸው። ኢየሱስ ከእነዚህ ሕግጋት መካከል ዋነኛ የሆኑትን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው።”—ማቴዎስ 22:37-39

የአምላክ መንግሥት ዜጎች ሊጠብቋቸው የሚገቡ ሌሎቹ ሕጎች ደግሞ ከአንዳንድ ድርጊቶች መራቅን የሚጠይቁ ናቸው። ለአብነት ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ግልጽ መመሪያ ይዟል:- “በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

የአምላክ መንግሥት ዜጎች እነማን ናቸው? ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ዜጎች በበግ መስሏቸዋል። እንዲህ ብሏል:- “እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ።” (ዮሐንስ 10:16) አንድ ሰው የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ከፈለገ የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ተከታይ መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን እሱ የሚያዘውንም መፈጸም ይኖርበታል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም።”—ማቴዎስ 7:21

በመሆኑም የአምላክ መንግሥት ዜጎች ኢየሱስ እንዳደረገው ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም ይጠቀማሉ፤ እንዲሁም ለስሙ አክብሮት አላቸው። (ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለሰዎች እንዲያስተምሩ የሰጣቸውን ትእዛዝ ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በተጨማሪም እርስ በርሳቸው ከልብ ይዋደዳሉ።—ዮሐንስ 13:35

‘ምድርን የሚያጠፏትን ማጥፋት’

በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በምድር ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ናቸው። ይህንን እንዴት እናውቃለን? ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ‘የአምላክ መንግሥት መቅረቡን’ ስለሚጠቁም የተለያዩ ገጽታዎች ስላሉት አንድ ምልክት ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 21:31) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው የዚህ ምልክት ገጽታዎች በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ በግልጽ እየታዩ ናቸው።

ከዚያስ በኋላ ምን ይከናወናል? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “በዚያን ጊዜ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:21) ይህ ሰው ሠራሽ ጥፋት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፏትን ለማጥፋት’ የሚወስደው እርምጃ ነው። (ራእይ 11:18 የ1954 ትርጉም) ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ምድርን ሊያጠፏት የተቃረቡ ክፉ ሰዎች “ከምድሪቱ ይወገዳሉ።” አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ የሚያገለግሉ ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች ግን “በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22

ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን ጥብቅ እርምጃ የሚወስድበት በቂ ምክንያት አለው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት። የምታከራያቸው የተወሰኑ ቤቶች አሉህ እንበል። አንዳንዶቹ ተከራዮች ጥሩ ባሕርይ ያላቸውና አሳቢ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ኪራዩን በወቅቱ የሚከፍሉ ሲሆኑ ቤቱንም በጥሩ ሁኔታ ይይዛሉ። ሌሎቹ ተከራዮች ግን ሥርዓት የሌላቸውና ራስ ወዳድ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ኪራይ ለመክፈል ፈቃደኞች አይደሉም፤ እንዲሁም ቤቱን በጣም አበላሽተውታል። በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ብትሰጣቸውም ለመስተካከል ፈቃደኞች አይደሉም። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? የቤቱ ባለቤት እንደመሆንህ መጠን እነዚህን መጥፎ ተከራዮች ከቤትህ እንደምታስወጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ ምድርንም ሆነ በእሷ ላይ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው እሱ በመሆኑ በፕላኔቷ ላይ ማን መኖር እንዳለበትና እንደሌለበት የመወሰን መብት አለው። (ራእይ 4:11) ይሖዋ ትእዛዙን ችላ የሚሉና የሌሎችን መብት የሚጋፉ ክፉ ሰዎችን ከምድር ላይ እንደሚያጠፋቸው ገልጿል።—መዝሙር 37:9-11

ገነት ዳግመኛ ትቋቋማለች

በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ምድርን መግዛት ይጀምራል። ኢየሱስ ይህንን አዲስ ጅምር “ሁሉም ነገር የሚታደስበት ጊዜ” በማለት ጠርቶታል። (ማቴዎስ 19:28 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) በዚያን ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታዎች ይኖራሉ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የሚከተሉትን ተስፋዎች ተመልከት:-

መዝሙር 46:9 “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል።”

ኢሳይያስ 35:1 “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።”

ኢሳይያስ 65:21-23 “እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል። ድካማቸው በከንቱ አይቀርም፤ ዕድለ ቢስ ልጆችም አይወልዱም።”

ዮሐንስ 5:28, 29 “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል።”

ራእይ 21:4 “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።”

አሳማኝ ምክንያቶች

የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ታምናለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብዙ ሰዎች እነዚህ ተስፋዎች ይፈጸማሉ ብለው እንደማያምኑ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ ‘“እመጣለሁ” ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ።” (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች እጅግ ተሳስተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ይፈጸማሉ ብለን እንድናምን ከሚያደርጉን ምክንያቶች መካከል እስቲ አራቱን እንመልከት:-

(1) አምላክ ከዚህ በፊት ምድር ላይ በሚኖሩ ክፉ ሰዎች ላይ እርምጃ ወስዷል። የኖኅ የጥፋት ውኃ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆነናል።—2 ጴጥሮስ 3:5-7

(2) የአምላክ ቃል በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚታዩትን ሁኔታዎች በትክክል ተንብዮአል።

(3) ሁሉም ነገር “ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ” ባለበት እየቀጠለ አይደለም። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፕላኔታችን ለማኅበራዊ፣ ለሥነ ምግባራዊና ለአካባቢያዊ ቀውስ ተዳርጋለች።

(4) የአምላክ “መንግሥት ወንጌል” በምድር ዙሪያ እየተሰበከ ሲሆን ይህም በቅርቡ ‘መጨረሻው እንደሚመጣ’ ያሳያል።—ማቴዎስ 24:14

የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ይጋብዙሃል። እንዲህ ማድረግህ በአምላክ መንግሥት ሥር ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይበልጥ እንድታውቅ ይረዳሃል። (ዮሐንስ 17:3) አዎ፣ የሰው ልጆች አስደናቂ የወደፊት ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣል! አንተስ በዚያን ጊዜ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ለመሆን ትበቃ ይሆን?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሁሉም ነገር ባለበት ይቀጥላል የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች እጅግ ተሳስተዋል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚያን ጊዜ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ለመሆን ትበቃ ይሆን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ