የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w08 9/15 ገጽ 3-7
  • ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ታዳጊዬ አንተ ነህ’
  • ከተቃዋሚዎች አድኖታል
  • ሲታመም ተንከባክቦታል
  • የዕለት ምግቡን ሰጥቶታል
  • ይሖዋ ሕዝቡን ‘እንዴት እንደሚያድናቸው ያውቃል’
  • “ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
w08 9/15 ገጽ 3-7

ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’

“አምላክ ሆይ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤ ረዳቴም፣ ታዳጊዬም አንተ ነህ።” —መዝ. 70:5

1, 2. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች የእሱን እርዳታ እንዲጠይቁ የሚያደርጓቸው የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው? (ለ) ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄ ይነሳል? መልሱንስ ከየት ማግኘት እንችላለን?

ያገባች ልጅ ያለቻቸው አንድ ባልና ሚስት ለመዝናናት ወጣ ብለው እያለ ልጃቸው እንደጠፋች ሰሙ። ይህች የ23 ዓመት ወጣት የጠፋችበት ሁኔታ ግራ የሚያጋባ ሲሆን ምናልባትም ወንጀል ተፈጽሞባት ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ነበር። እነዚህ ወላጆች ይህንን እንደሰሙ ወዲያውኑ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ በጉዞው ወቅት ልጃቸውን አስመልክተው ወደ ይሖዋ አጥብቀው ይጸልዩ ነበር። የ20 ዓመት ወጣት የሆነ ሌላ የይሖዋ ምሥክር ደግሞ ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ሽባ የሚያደርግ በሽታ እንዳለበት ተነገረው። ወንድም ይህንን እንደሰማ ወዲያው ወደ ይሖዋ ጸለየ። ሥራ ለማግኘት ላይ ታች የምትል አንዲት ነጠላ እናት ለራሷም ሆነ ለ12 ዓመት ሴት ልጇ ምግብ ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አልነበራትም። ይህች እናትም ለይሖዋ የልቧን አውጥታ ነገረችው። በእርግጥም፣ የአምላክ አገልጋዮች ከባድ ፈተናዎች ወይም ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይሖዋ እንዲረዳቸው መለመናቸው የተለመደ ነገር ነው። አንተስ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞህ ወደ ይሖዋ ምልጃ አቅርበህ ታውቃለህ?

2 እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ይነሳል:- ይሖዋ፣ እንዲረዳን ለምናቀርበው ጸሎት ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? መዝሙር 70 እምነታችንን የሚያጠናክር መልስ ይሰጠናል። ይህን ልብ የሚነካ መዝሙር የጻፈው ዳዊት ሲሆን ይህ ታማኝ የይሖዋ አምላኪ በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር። ይህ መዝሙራዊ፣ ይሖዋን “አምላክ ሆይ፤ . . . ረዳቴም፣ ታዳጊዬም አንተ ነህ” ብሎታል። (መዝ. 70:5) መዝሙር 70⁠ን መመርመራችን እኛም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ የምንችለው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ‘ታዳጊያችን’ እንደሚሆን ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችልበትን ምክንያት ለመገንዘብ ይረዳናል።

‘ታዳጊዬ አንተ ነህ’

3. (ሀ) መዝሙር 70 የአምላክን እርዳታ በአፋጣኝ ለማግኘት የቀረቡትን የትኞቹን ልመናዎች ይዟል? (ለ) በ70ኛው መዝሙር ላይ የሚገኘው ሐሳብ ዳዊት ምን ጠንካራ እምነት እንዳለው ያሳያል?

3 መዝሙር 70 የሚጀምረውም ሆነ የሚደመድመው የአምላክን እርዳታ በአፋጣኝ ለማግኘት በቀረበ ልመና ነው። (መዝሙር 70:1-5⁠ን አንብብ።) ዳዊት፣ ‘ፈጥኖ’ እንዲያድነው ይሖዋን ተማጽኖታል። ከቁጥር 2 እስከ 4 ላይ ዳዊት የሚመኛቸውን ነገሮች የሚገልጹ አምስት ልመናዎችን አቅርቧል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ሊገድሉት ይሞክሩ የነበሩትን ሰዎች የሚመለከቱ ናቸው። ዳዊት እነዚህን ጠላቶቹን ይሖዋ እንዲያሸንፋቸውና በክፋታቸው እንዲያፍሩ እንዲያደርጋቸው ልመና አቅርቧል። በቁጥር 4 ላይ የሚገኙት ሁለት ልመናዎች ደግሞ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የተያያዙ ናቸው። ዳዊት፣ ይሖዋን የሚሹ ሁሉ በእሱ እንዲደሰቱና እሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንዲነሳሱ ጸልዮአል። ይህ የአምላክ አገልጋይ መዝሙሩን ሲደመድም ይሖዋን “ረዳቴም፣ ታዳጊዬም አንተ ነህ” ብሎታል። ዳዊት ‘ረዳቴና ታዳጊዬ ሁንልኝ’ በማለት ልመና ከማቅረብ ይልቅ “ረዳቴም፣ ታዳጊዬም አንተ ነህ” በማለት በይሖዋ እንደሚተማመን መግለጹን ልብ በል። አዎን፣ ዳዊት መለኮታዊ እርዳታ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበር።

4, 5. መዝሙር 70 ስለ ዳዊት ምን ይጠቁመናል? ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን መተማመን እንችላለን?

4 መዝሙር 70 ስለ ዳዊት ምን ይጠቁመናል? ዳዊት ሕይወቱን ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ ጠላቶች ባጋጠሙት ወቅት ችግሩን በራሱ ለመፍታት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ በወሰነው ጊዜና በራሱ መንገድ በእነዚህ ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ተማምኖ ነበር። (1 ሳሙ. 26:10) ይሖዋ እሱን የሚሹ ሰዎችን እንደሚረዳቸውና እንደሚያድናቸው ዳዊት ቅንጣት ያህል አልተጠራጠረም። (ዕብ. 11:6) ዳዊት እንደነዚህ ያሉት እውነተኛ አምላኪዎች ስለ ይሖዋ ታላቅነት ለሌሎች በመናገር ለመደሰትና እሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳላቸው ያምን ነበር።—መዝ. 5:11፤ 35:27

5 እኛም እንደ ዳዊት ይሖዋ፣ ረዳታችንና ‘ታዳጊያችን’ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። በመሆኑም ከባድ መከራ ሲደርስብን ወይም እርዳታ በጣም እንደሚያስፈልገን ሲሰማን ይሖዋ ፈጥኖ እንዲረዳን መጸለያችን ተገቢ ነው። (መዝ. 71:12) ታዲያ ይሖዋ ለእርዳታ ላቀረብነው ጸሎት መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው? ይሖዋ እንዴት እንደሚረዳን ከማየታችን በፊት ዳዊት አፋጣኝ እርዳታ ባስፈለገው ወቅት ይሖዋ ታዳጊው መሆኑን ያሳየባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።

ከተቃዋሚዎች አድኖታል

6. ይሖዋ፣ ጻድቃንን እንደሚታደግ ዳዊት እንዲያስተውል የረዳው ምንድን ነው?

6 ዳዊት፣ ጻድቃን የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት በእሱ መታመን እንደሚችሉ በወቅቱ ከነበሩት ቅዱሳን መጻሕፍት አስተውሎ ነበር። ይሖዋ፣ ከአምላክ በራቀው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣበት ወቅት ኖኅንና ፈሪሃ አምላክ ያለውን ቤተሰቡን አድኗቸዋል። (ዘፍ. 7:23) ይሖዋ፣ በሰዶምና በገሞራ ይኖሩ በነበሩት ክፉ ሰዎች ላይ እሳትና ዲን ሲያዘንብ ጻድቁ ሎጥና ሁለት ሴት ልጆቹ በሕይወት እንዲተርፉ አድርጓል። (ዘፍ. 19:12-26) ይሖዋ፣ ትዕቢተኛውን ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ባጠፋበት ወቅት ለሕዝቦቹ ጥበቃ በማድረግ ከጥፋት ታድጓቸዋል። (ዘፀ. 14:19-28) ታዲያ ዳዊት በሌላው መዝሙሩ ላይ “አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው” በማለት ይሖዋን ማወደሱ ምን ያስገርማል?—መዝ. 68:20

7-9. (ሀ) ዳዊት በአምላክ የማዳን ኃይል እንዲታመን የሚያደርጉ ምን ምክንያቶች ነበሩት? (ለ) ዳዊት በሕይወት በመትረፉ ያመሰገነው ማንን ነበር?

7 ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ነገሮችም በይሖዋ የማዳን ኃይል ሙሉ በሙሉ እንዲታመን አድርገውታል። የይሖዋ ‘የዘላለም ክንዶች’ አገልጋዮቹን ማዳን እንደሚችሉ ዳዊት በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። (ዘዳ. 33:27) ይሖዋ፣ ዳዊትን ብዙ ጊዜ ‘ከጠላቶቹ’ አድኖታል። (መዝ. 18:17-19, 48) እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

8 የእስራኤል ሴቶች ዳዊትን በውጊያ ችሎታው ባወደሱት ወቅት ንጉሥ ሳኦል ቅናት ስላሳበደው ጦሩን ሁለት ጊዜ ዳዊት ላይ ወርውሮበት ነበር። (1 ሳሙ. 18:6-9) በሁለቱም ጊዜያት ዳዊት ምንም ጉዳት ሳይደርስበት አምልጧል። ዳዊት ሊያመልጥ የቻለው ጥሩ ችሎታ ያለው ቀልጣፋ ተዋጊ ስለነበር ነው? አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ‘እግዚአብሔር ከእሱ ጋር እንደነበረ’ ይገልጻል። (1 ሳሙኤል 18:11-14⁠ን አንብብ።) ቆየት ብሎም ሳኦል፣ ፍልስጥኤማውያን ዳዊትን እንዲገድሉት የጠነሰሰው ሴራ መክሸፉን ሲመለከት “እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ” ተገንዝቧል።—1 ሳሙ. 18:17-28

9 ዳዊት በሕይወት በመትረፉ ያመሰገነው ማንን ነበር? በመዝሙር 18 አናት ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ዳዊት ይህን መዝሙር ለይሖዋ የዘመረው “ከሳኦል . . . እጅ በታደገው ጊዜ” ነበር። ዳዊት “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ . . . ነው” በማለት ስሜቱን በመዝሙር ገልጿል። (መዝ. 18:2) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ማዳን የሚችል አምላክ መሆኑን ማወቅ እምነት የሚያጠናክር አይደለም?—መዝ. 35:10

ሲታመም ተንከባክቦታል

10, 11. ዳዊት በመዝሙር 41 ላይ የተጠቀሰው ሕመም ያጋጠመው መቼ ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ የሚረዳን ምንድን ነው?

10 ንጉሥ ዳዊት በአንድ ወቅት በጠና ታምሞ እንደነበር በመዝሙር 41 ላይ ተገልጿል። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ዳዊት ከአልጋው መውረድ አቅቶት ስለነበር አንዳንድ ጠላቶቹ ‘ከተኛበት እንደማይነሣ’ ተሰምቷቸው ነበር። (ቁጥር 7, 8) ዳዊት እንዲህ ያለ ከባድ ሕመም ያጋጠመው መቼ ነበር? በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች እንደሚጠቁሙት ዳዊት የታመመው ልጁ አቤሴሎም ንግሥናውን ለመንጠቅ ያደርግ የነበረው ጥረት ጭንቀት ላይ በጣለው ወቅት ሳይሆን አይቀርም።—2 ሳሙ. 15:6, 13, 14

11 ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት እንጀራውን ተካፍሎት የበላ የሚተማመንበት ወዳጁ እንደከዳው ገልጿል። (ቁጥር 9) ይህ ሐሳብ ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመውን አንድ ሁኔታ ያስታውሰናል። ታማኝ አማካሪው የነበረው አኪጦፌል፣ አቤሴሎም ባመፀበት ወቅት ከእሱ ጋር በማበር በንጉሡ ላይ ዓምፆ ነበር። (2 ሳሙ. 15:31፤ 16:15) በሕመም ምክንያት አቅም ያጣው ንጉሥ በአልጋው ላይ ሆኖ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ ንጉሡ የክፋት እቅዳቸውን መፈጸም እንዲችሉ የእሱን መሞት በሚመኙ ሴረኞች እንደተከበበ ያውቅ ነበር።—ቁጥር 5

12, 13. (ሀ) ዳዊት፣ በይሖዋ ላይ ምን እምነት እንዳለው ገልጿል? (ለ) አምላክ፣ ዳዊትን ያበረታው እንዴት ሊሆን ይችላል?

12 ዳዊት ‘ታዳጊው’ በሆነው አምላክ ላይ ምንጊዜም ቢሆን ይተማመን ነበር። ዳዊት በሕመም ላይ ስላለ አንድ ጻድቅ የአምላክ አገልጋይ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር በክፉ ቀን ይታደገዋል። ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፤ በበሽታውም ጊዜ መኝታውን ያነጥፍለታል።” (መዝ. 41:1, 3) እዚህ ላይም ዳዊት “እግዚአብሔር ይንከባከበዋል” በማለት በአምላክ እንደሚተማመን መግለጹን ልብ በል። ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚታደገው እርግጠኛ ነበር። ታዲያ ይሖዋ የታደገው እንዴት ነበር?

13 ዳዊት፣ ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከበሽታ ያድነኛል ብሎ አልጠበቀም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘እንደሚንከባከበው’ ማለትም ታምሞ በተኛበት ወቅት የሚያስፈልገውን ድጋፍና ጥንካሬ እንደሚሰጠው ሙሉ በሙሉ ይተማመን ነበር። ደግሞም እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያስፈልገው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ንጉሡ፣ በሽታው አቅም ያሳጣው ከመሆኑም በላይ ስለ እሱ መጥፎ ነገር በሚናገሩ ጠላቶቹ ተከብቦ ነበር። (ቁጥር 5, 6) ይሖዋ፣ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን እንዲያስታውስ በመርዳት ዳዊትን አጠናክሮት ሊሆን ይችላል። ዳዊት “ስለ ታማኝነቴ ደግፈህ ይዘኸኛል” ብሏል። (ቁጥር 12 NW) ከዚህም በላይ ይህ ንጉሥ፣ የጤንነት ችግሩ አቅም ያሳጣውና ጠላቶቹ ስለ እሱ መጥፎ ነገር መናገራቸው የጎዳው ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እንደ ታማኝ ሰው አድርጎ እንደሚመለከተው ማወቁ ብርታት ሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ከሕመሙ አገግሟል። ይሖዋ፣ የታመሙ ሰዎችን እንደሚንከባከብ ማወቅ የሚያጽናና አይደለም?—2 ቆሮ. 1:3

የዕለት ምግቡን ሰጥቶታል

14, 15. ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ምግብ አጥተው የነበሩት መቼ ነው? ምን እርዳታስ አግኝተው ነበር?

14 ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ በኋላ ምርጥ የሆኑ ምግቦችን መመገብ እንዲሁም ያሰኘውን መጠጥ መጠጣት አልፎ ተርፎም ሌሎች ከገበታው እንዲመገቡ መጋበዝ ይችል ነበር። (2 ሳሙ. 9:10) ያም ሆኖ ዳዊት ማጣትንም ያውቅ ነበር። ልጁ አቤሴሎም ዓመፅ በማስነሳት ንግሥናውን ሊነጥቀው በሞከረ ጊዜ ዳዊት ከጥቂት ታማኝ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኘው ገለዓድ የተባለ አካባቢ ሸሸ። (2 ሳሙ. 17:22, 24) ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከአሳዳጆቻቸው ይሸሹ ስለነበር ምግብና መጠጥ ከማጣታቸውም በላይ እረፍት ያሻቸው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ሩቅ አካባቢ ሆነው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ከየት ማግኘት ይችላሉ?

15 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከረጅም ጉዞ በኋላ መሃናይም ወደተባለችው ከተማ ደረሱ። በዚያም ሾቢ፣ ማኪር እና ቤርዜሊ ከተባሉ ሦስት ደፋር ሰዎች ጋር ተገናኙ። እነዚህ ሰዎች፣ አቤሴሎም ንግሥናውን ቢይዝ ዳዊትን የደገፉ ሰዎች ሁሉ ከባድ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ቢያውቁም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል በይሖዋ የተሾመውን ንጉሥ ለመርዳት ፈቃደኞች ነበሩ። እነዚህ ሦስት ታማኝ ሰዎች ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ያጋጠማቸውን ችግር በተረዱበት ወቅት መተኛ ምንጣፎችን እንዲሁም ስንዴ፣ ገብስ፣ የተጠበሰ እሸት፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ማር፣ ቅቤና በጎችን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አመጡላቸው። (2 ሳሙኤል 17:27-29⁠ን አንብብ።) እነዚህ ሦስት ሰዎች ባሳዩት ለየት ያለ የታማኝነትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ዳዊት ልቡ ተነክቶ መሆን አለበት። ደግሞስ ንጉሡ እነዚህ ሰዎች ያደረጉለትን ነገር እንዴት ሊረሳው ይችላል?

16. ዳዊትና ሰዎቹ ምግብ እንዲያገኙ የረዳቸው ማን ነበር?

16 ዳዊትና ሰዎቹ ምግብ እንዲያገኙ የረዳቸው ማን ነበር? ዳዊት፣ ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደሚያስብ እርግጠኛ ነበር። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ሲቸገሩ ሌሎች አምላኪዎቹ እነሱን ለመርዳት እንዲነሳሱ እንደሚያደርግ ጥርጥር አልነበረውም። ዳዊት በገለዓድ ምድር በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ መለስ ብሎ ሲያስብ፣ ሦስቱ ሰዎች ያሳዩትን ደግነት የይሖዋ ፍቅራዊ አሳቢነት መግለጫ አድርጎ እንደተመለከተው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ የአምላክ አገልጋይ ወደ ሕይወቱ ማብቂያ ሲቃረብ “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል [ዳዊትን ጨምሮ]፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” በማለት ጽፏል። (መዝ. 37:25) የይሖዋ እጅ አጭር አለመሆኑን ማወቅ የሚያጽናና አይደለም?—ምሳሌ 10:3

ይሖዋ ሕዝቡን ‘እንዴት እንደሚያድናቸው ያውቃል’

17. ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት ምን ዓይነት አምላክ መሆኑን አስመስክሯል?

17 ዳዊት፣ ይሖዋ በጥንት ዘመናት ከታደጋቸው በርካታ አምላኪዎቹ መካከል አንዱ ብቻ ነው። ከዳዊት ዘመን በኋላም ቢሆን አምላክ በተደጋጋሚ ጊዜያት ያከናወናቸው ነገሮች ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣሉ:- “ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸው . . . ያውቃል።” (2 ጴጥ. 2:9) እስቲ ሁለት ተጨማሪ ምሳሌዎችን እንመልከት።

18. ይሖዋ፣ በሕዝቅያስ ዘመን ሕዝቦቹን ያዳነው እንዴት ነበር?

18 በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ኃያሉ የአሦር ሠራዊት ይሁዳን በመውረር ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እየዛተ በነበረበት ወቅት ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ በማለት ጸልዮ ነበር:- “ይሖዋ አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ይሖዋ ብቸኛው አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ . . . አድነን።” (ኢሳ. 37:20 NW) ሕዝቅያስን በዋነኝነት ያሳሰበው በአምላክ ስም ላይ የሚመጣው ነቀፌታ ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቅያስ ላቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት ምላሽ ሰጥቶታል። አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት ብቻ 185,000 አሦራውያንን በመግደል ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን አድኗቸዋል።—ኢሳ. 37:32, 36

19. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከጥፋት መትረፍ የቻሉት የትኛውን ማስጠንቀቂያ በመስማታቸው ነበር?

19 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት፣ በይሁዳ የሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱን የሚጠቅም ትንቢት አዘል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። (ሉቃስ 21:20-22⁠ን አንብብ።) ማስጠንቀቂያው ከተሰጠ በኋላ የተወሰኑ አሥርተ ዓመታት አለፉ፤ በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ግን የሮም ሠራዊት የአይሁዳውያንን ዓመፅ ለማስቆም በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ። በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው ሠራዊት የቤተ መቅደሱን ግንብ የተወሰነ ክፍል ማፍረስ ቢችልም በድንገት ጥቃቱን አቁሞ ወደኋላ ተመለሰ። ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች ኢየሱስ አስቀድሞ ከተናገረው ጥፋት ለማምለጥ የሚችሉት በዚህ አጋጣሚ እንደሆነ በመገንዘብ ወደ ተራሮች ሸሹ። የሮም ሠራዊት በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ተመልሶ በመምጣት ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ አወደማት። የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ የወሰዱት ክርስቲያኖች ከዚህ አስከፊ መከራ ተርፈዋል።—ሉቃስ 19:41-44

20. ይሖዋ ‘እንደሚታደገን’ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ባለፉት ዘመናት ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንደረዳ በሚገልጹት ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን እምነታችንን ያጠናክራል። ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያከናወናቸው ነገሮች በእሱ ለመተማመን መሠረት ይሆኑልናል። በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት ምንም ዓይነት ፈተናዎች ቢያጋጥሙን ይሖዋ ‘እንደሚታደገን’ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። ታዲያ ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ሰዎችስ ለጸሎታቸው ምላሽ ያገኙት እንዴት ነው? መልሱን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ታስታውሳለህ?

• መዝሙር 70 ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ይረዳናል?

• ዳዊት በታመመበት ወቅት አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ያገኘው እንዴት ነበር?

• ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ከተቃዋሚዎች ማዳን እንደሚችል የሚያሳዩት የትኞቹ ታሪኮች ናቸው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለሕዝቅያስ ጸሎት መልስ ሰጥቶታል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ