የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w09 5/1 ገጽ 22-25
  • የብሩክሊን ቤቴል የ100 ዓመት ታሪክ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የብሩክሊን ቤቴል የ100 ዓመት ታሪክ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ማኅበሩን ወደ ብሩክሊን ማዛወር ያስፈለገው ለምንድን ነው?
  • ቤቴል የተባለው ለምንድን ነው?
  • ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ
  • ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • “የአምላክን ቤት” በአድናቆት መመልከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ይሖዋ ሕዝቡን መሰብሰብ ጀመረ፣ ለሥራም አስታጠቃቸው
    እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች
  • ይምጡና ይጎብኙ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
w09 5/1 ገጽ 22-25

የብሩክሊን ቤቴል የ100 ዓመት ታሪክ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ122-124 ኮሎምቢያ ሃይትስ የሚገኘው የቤቴል ቤት

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

13-17 ሃይክስ ጎዳና (1909-1918)

ከኒው ዮርክ ሲቲ ጋር በተያያዘ 1909 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓመት ነው። የኩዊንስን አውራጃ ከማንሃተን ጋር የሚያገናኘው ኩዊንስቦሮ ድልድይ እንዲሁም ማንሃተንን ከብሩክሊን ጋር የሚያገናኘው ማንሃተን ድልድይ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በዚህ ዓመት ነበር።

በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥም 1909 ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ዓመት ነው። የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ (የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ድርጅት ነው) ፕሬዚዳንት የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራ ሊስፋፋ እንደሚችል አስተውሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ወንድም ራስል ይህን ለማድረግ የማኅበሩን ዋና መሥሪያ ቤት ከፒትስበርግ፣ ፔንሲልቬንያ ወደ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ማዛወር አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ለዚህም በ1908 ዝግጅት መደረግ የጀመረ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ማኅበሩ ወደ ብሩክሊን ተዛወረ።

ማኅበሩን ወደ ብሩክሊን ማዛወር ያስፈለገው ለምንድን ነው?

በወቅቱ የስብከቱን ሥራ በበላይነት ይመሩ የነበሩት ወንድሞች፣ ስብከቶችን በጋዜጣ ማሳተም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሰራጨት የሚያስችል ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። በ1908 ወንድም ራስል የሚጽፋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች በየሳምንቱ በ11 ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ 402,000 ቅጂዎች ይታተሙ ነበር።

ይሁን እንጂ ወንድም ራስል እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር፦ “ጋዜጦች ሥራቸውን የሚያከናውኑበትን መንገድ የሚያውቁ ወንድሞች . . . እንደገለጹልን በየሳምንቱ የሚወጡት እነዚህ ስብከቶች [በትልቅ ከተማ] ውስጥ ቢዘጋጁ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የመታተም አጋጣሚ ይኖራቸዋል፤ በዚህ መንገድ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች እነዚህን ስብከቶች በቋሚነት ሊያትሙ ይችላሉ።” በዚህም ምክንያት የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት አመቺ የሆነ ቦታ መፈለግ ተጀመረ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩት የራስል ስብከቶች

ብሩክሊን የተመረጠው ለምን ነበር? ወንድም ራስል እንዲህ ብሏል፦ “ሁላችንም በዚህ ጉዳይ ላይ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ለመከሩ ሥራ አመቺ ቦታ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሰናል። ብሩክሊን . . . ብዙ ነዋሪዎች ያሉት ከመሆኑም ሌላ ‘የአብያተ ክርስቲያናት ከተማ’ በመባል የሚታወቅ መሆኑ እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ምክንያት ሆኖናል።” ከዚያ በኋላ የተገኙት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት ይህ ውሳኔ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ 2,000 ጋዜጦች የወንድም ራስልን ስብከት ይዘው መውጣት ጀመሩ።

ኒው ዮርክ ጥሩ ምርጫ እንዲሆን ያደረገው ሌላም ምክንያት አለ። በ1909 በታላቋ ብሪታንያ፣ በጀርመንና በአውስትራሊያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በሌሎች ቦታዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተከፈቱ። በመሆኑም ዋናው መሥሪያ ቤት፣ በርካታ መንገዶችና የባቡር መስመሮች እንዲሁም የባሕር ወደብ ባለው ከተማ ውስጥ መሆኑ ምክንያታዊ ነበር።

ቤቴል የተባለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

18 ኮንኮርድ ጎዳና (1922-1927)

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

117 አዳምስ ጎዳና (ከ1927 እስከ ዛሬ ድረስ)

በ1880ዎቹ ዓመታት የተቋቋመው የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ዋና መሥሪያ ቤት የመጀመሪያ ቢሮ የሚገኘው በአሌጌኒ (አሁን የፒትስፐርግ ክፍል ናት)፣ ፔንሲልቬንያ ነበር። በዚያን ወቅት ማኅበሩ የነበረበት ሕንፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤት ተብሎ ይጠራ ነበር። በ1896 በዚህ ሕንፃ ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች 12 ነበሩ።

በ1909 ማኅበሩ ወደ ብሩክሊን ሲዛወር ለወንድሞች መኖሪያ የተደረገው አዲሱ ቤት ቤቴል ተባለ።a ቤቴል የተባለው ለምንድን ነው? ዎች ታወር ሶሳይቲ የገዛው በ13-17 ሂክስ ጎዳና ላይ የሚገኘው ሕንፃ፣ ሄንሪ ዋርድ ቢቸር የተባለው ታዋቂ ቄስ ንብረት ሲሆን ሕንፃውም የቢቸር ቤቴል ተብሎ ይጠራ ነበር። ማኅበሩ በ124 ኮሎምቢያ ሃይትስ የሚገኘውን የቢቸርን የቀድሞ መኖሪያ ቤትም ገዝቶ ነበር። የመጋቢት 1, 1909 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “የቀድሞውን የቢቸር ቤቴል፣ ከዚያም በአጋጣሚ ደግሞ የቀድሞ መኖሪያ ቤቱን መግዛታችን በጣም የሚያስገርም ነው። . . . አዲሱ ቤት ‘ቤቴል’ ተብሎ ይጠራል፤ አዲሱ ቢሮና አዳራሹ ደግሞ ‘የብሩክሊን የመገናኛ ድንኳን’ ይባላሉ። ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ቤት’ የሚለው መጠሪያ በእነዚህ ስሞች ይተካል።”

በዛሬው ጊዜ በብሩክሊን፣ በዎልኪልና በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ውስጥ የሚገኙት የፈቃደኛ ሠራተኞቹ መኖሪያ ሕንፃዎችም ሆኑ ማተሚያዎቹንና ቢሮዎቹን የያዙት ሰፋፊ ሕንፃዎች ቤቴል ተብለው ይጠራሉ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በ113 አገሮች ውስጥ የቤቴል ቤቶች ይገኛሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በማሰራጨቱ ሥራ የሚካፈሉ ከ19,000 የሚበልጡ አገልጋዮች በእነዚህ የቤቴል ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ።

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

35 መርትል ጎዳና (1920-1922)

ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

እነዚህ ሕንፃዎች ጥር 31, 1909 ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰኑ። ሰኞ መስከረም 6, 1909 ቤቴል ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ። በዚያን ዕለት፣ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሕንፃውን ጎብኝተዋል። አብዛኞቹ ጎብኚዎች ወደ ቤቴል የመጡት ከኒው ዮርክ ሲቲ በስተ ሰሜን 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳራቶጋ ስፕሪንግስ የተደረገው ትልቅ ስብሰባ እንዳበቃ ነበር። ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ጎብኚዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ተቀብሏቸዋል።b

በአሁኑ ጊዜም ቤቴል ለጎብኚዎች ክፍት ነው። በየዓመቱ ከ40,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በብሩክሊን የሚገኙትን ሕንፃዎች ይጎበኛሉ። የብሩክሊን ቤቴል ከይሖዋ መንግሥት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወት ሲሆን ይህም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በረከት አምጥቷል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዎልኪል የሚገኘው ማተሚያ ቤት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፓተርሰን የሚገኘው የትምህርት ማዕከል

a “ቤቴል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም አለው። ቤቴል ታዋቂ የሆነች የእስራኤል ከተማ ነበረች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከቤቴል የበለጠ በብዛት የተጠቀሰች ከተማ ኢየሩሳሌም ብቻ ናት።

b ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ተጨማሪ የታሪክ ዘገባዎችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተሰኘውን መጽሐፍ ገጽ 718-723 ተመልከት።

ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ስለተባለው ሕጋዊ ማኅበር ምን ያህል ታውቃለህ?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንሲልቬንያ ተብሎ የሚጠራው ኮርፖሬሽን የተቋቋመው በ1884 ሲሆን በወቅቱ ዛዮንስ ዎች ታወር ትራክት ሶሳይቲ ተብሎ ይጠራ ነበር። የማኅበሩ ዓላማ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተለይ በጽሑፎች አማካኝነት በመላው ዓለም ማሰራጨት ነው። በዛሬው ጊዜም ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ከሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ ማኅበሮች አንዱ ነው።c—ፊልጵስዩስ 1:7

ይህ ማኅበር፣ መጽሐፍ ቅዱሶችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በ473 ቋንቋዎች ሲያትም ቆይቷል። ማኅበሩ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉምን በከፊልም ሆነ በሙሉ በ72 ቋንቋዎች ከ150 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች አሳትሟል። የዎች ታወር ማኅበር፣ ከአዲስ ዓለም ትርጉም በተጨማሪ በራሱ ማተሚያ ቤት ያተማቸው አሊያም በሌሎች ማተሚያ ቤቶች ያሳተማቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የሚከተሉት ናቸው፦ አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን፣ ዘ ባይብል ኢን ሊቪንግ ኢንግሊሽ፣ ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት፣ የሆልማን ሊኒየር ፓራለል ኢዲሽን፣ ኪንግ ጄምስ ቨርዥን (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን ትርጉም ይጨምራል) እንዲሁም ዘ ኒው ቴስታመንት ኒውሊ ትራንስሌትድ ኤንድ ክሪቲካሊ ኢምፋሳይዝድ፣ ሁለተኛ እትም።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሶችን ከማተም በተጨማሪ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ20 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ እንደ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ትራክቶች፣ ሲዲዎችና ዲቪዲዎች ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የማስተማሪያ መሣሪያዎችን አዘጋጅተዋል።d ከእነዚህ ጽሑፎች፣ ሲዲዎችና ዲቪዲዎች አብዛኞቹ የተዘጋጁት፣ የታሸጉትና ወደ ተለያዩ ቦታዎች የተላኩት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አገሮች ውስጥ እንደሚገኙት ባሉ የቤቴል ቤቶች ውስጥ ነው፦ ሕንድ፣ ማያንማር፣ ሜክሲኮ፣ ስፔን፣ ብሪታንያ፣ ብራዚል፣ ናይጄሪያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ፊሊፒንስና ፊንላንድ።

1998-2008 ባሉት ዓመታት

ማኅበሩ ያዘጋጃቸው የማስተማሪያ መሣሪያዎች

መጻሕፍት

458,230,708

መጽሔቶች

11,292,413,199

ትራክቶች

7,996,906,376

ብሮሹሮች

862,050,233

ሲዲ/በMP3

34,621,130

ዲቪዲዎች

13,500,125

ሌሎች

129,083,031

በአጠቃላይ

20,786,804,802

c በ2008 በ236 አገሮች ውስጥ የሚያገለግሉ 7,124,443 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነዚህ ክርስቲያኖች በ103,267 ጉባኤዎች ታቅፈዋል።

d እነዚህ ጽሑፎች፣ ሲዲዎችና ዲቪዲዎች ለሽያጭ የሚቀርቡ አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ