የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w11 9/1 ገጽ 15
  • ‘ይሖዋ ሆይ፣ ታውቀኛለህ’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ይሖዋ ሆይ፣ ታውቀኛለህ’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አ ም ላ ክ በእርግጥ ያውቅሃልን?
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • አምላክ ስሜትህን ይረዳልሃል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ይሖዋ በጥንት ዘመናት ሕዝቦቹን ‘ታድጓል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
w11 9/1 ገጽ 15

ወደ አምላክ ቅረብ

‘ይሖዋ ሆይ፣ ታውቀኛለህ’

“አንድ ሰው ማንም ስለ እሱ ደንታ እንደሌለው ወይም የውስጡን የሚረዳለት እንደሌለ ሲያውቅ የሚሰማውን ስሜት ያህል ለመሸከም የሚከብደው ነገር የለም።”a አንተስ ከዚህ ሐሳብ ጋር ትስማማለህ? ማንም ስለ አንተ ደንታ እንደሌለው ወይም በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለህ የሚረዳልህ ሰው እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይሖዋ ስለ አገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች በሙሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። በመዝሙር 139 ላይ የሚገኘው ዳዊት የተናገረው ሐሳብ ይህን ሐቅ ያረጋግጥልናል።

ዳዊት፣ አምላክ እንደሚያስብለት እርግጠኛ ስለነበር “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 1) እዚህ ላይ ዳዊት ግሩም የሆነ አገላለጽ ተጠቅሟል። “መረመርኸኝ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ማዕድን ለማግኘት ፍለጋ ማድረግን (ኢዮብ 28:3)፣ አንድን ምድር መሰለልን (መሳፍንት 18:2) አሊያም ከፍርድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እውነታውን ለማወቅ ምርመራ ማካሄድን (ዘዳግም 13:14) ሊያመለክት ይችላል። አዎ፣ ይሖዋ ጥቃቅን ነገሮችን ጨምሮ አጠቃላይ ሕይወታችንን የመረመረ ያህል በሚገባ ያውቀናል። የዳዊት አነጋገር አምላክ የእያንዳንዱ አገልጋዮቹ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ያስተምረናል። ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ ይመረምራቸዋል እንዲሁም እያንዳንዳቸውን ያውቃቸዋል።

ዳዊት፣ አምላክ ሰዎችን ምን ያህል በጥልቅ እንደሚመረምር ሲገልጽ “አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ” ብሏል። (ቁጥር 2) ይሖዋ ያለው በሰማይ ስለሆነ የሚኖርበት ስፍራ ‘ሩቅ’ ነው ሊባል ይችላል። ያም ሆኖ ቀኑን ሙሉ ስንደክም ውለን ምሽት ላይ ‘ስንቀመጥ’ እንዲሁም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ለማከናወን ጠዋት ላይ ‘ስንነሳ’ ይመለከተናል። በተጨማሪም ሐሳባችንን፣ ምኞታችንን እና ዝንባሌያችንን ያውቃል። ታዲያ ዳዊት፣ አምላክ በጥንቃቄ እንደሚከታተለው ማወቁ ፍርሃት እንዲሰማው አድርጎታል? በጭራሽ፣ እንዲያውም ይሖዋ እንዲመረምረው ጥያቄ አቅርቧል። (ቁጥር 23, 24) ይህን ጥያቄ ያቀረበው ለምን ነበር?

ይሖዋ አገልጋዮቹን በጥንቃቄ የሚመረምረው መልካም ነገር ለማግኘት እንደሆነ ዳዊት ያውቅ ነበር። ዳዊት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ሲጽፍ “መሄድ መተኛቴን አጥርተህ ታውቃለህ፤ መንገዶቼንም ሁሉ ተረድተሃቸዋል” ብሏል። (ቁጥር 3) ይሖዋ በእያንዳንዱ ቀን ‘መንገዳችንን ሁሉ’ ማለትም የሠራናቸውን ስህተቶችና ያደረግናቸውን መልካም ነገሮች ይመለከታል። ታዲያ ትኩረት የሚያደርገው በሠራነው መጥፎ ነገር ላይ ነው ወይስ ባከናወንነው መልካም ሥራ ላይ? “አጥርተህ ታውቃለህ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መንፋት” ወይም “ማዝራት” የሚል መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል፤ ይህም አንድ ገበሬ እህል በማዝራት ፍሬውን ከገለባው ለመለየት ከሚያደርገው ጥረት ጋር ይመሳሰላል። “ተረድተሃቸዋል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ከፍ አድርጎ መመልከት” የሚል ሐሳብ ሊያስተላልፍ ይችላል። ይሖዋ አገልጋዮቹ በየዕለቱ የሚናገሯቸውንና የሚያደርጓቸውን ነገሮች በሚመረምርበት ጊዜ ለሚያገኛቸው መልካም ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጣል። እንዲህ የሚያደርገው ለምንድን ነው? እሱን ለማስደሰት ሲሉ የሚያደርጉትን ጥረት ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ነው።

መዝሙር 139 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በጥልቅ እንደሚያስብ ያስተምረናል። አገልጋዮቹ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ይመረምራቸዋል እንዲሁም ይከታተላቸዋል። ስለሆነም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ያውቃል፤ እንዲሁም እነዚህ ችግሮች የሚያስከትሉባቸውን ከባድ ጭንቀትና የስሜት ሥቃይ ይረዳላቸዋል። ታዲያ አንተስ እንዲህ የመሰለውን አሳቢ አምላክ ለማገልገል አትገፋፋም? ከሆነ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፦ ይሖዋ ‘የምታከናውነውን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳየኸውን ፍቅር’ አይረሳም።​—ዕብራውያን 6:10

በመስከረም ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

◼ ከመዝሙር 119 እስከ 150

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህን ሐሳብ የተናገሩት አርተር ስቴንባክ የተባሉ ደራሲ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ