አብርሃም ማን ነበር?
በዓለም ባሉ ሃይማኖቶች ላይ የእሱን ያህል የጎላ ተጽዕኖ ያሳደሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው። በአይሁዶች፣ በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈው አብርሃምa “በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው” እንዲሁም “ድንቅ የእምነት ተምሳሌት” ተብሎ ተጠርቷል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብርሃም ‘እምነት ላላቸው ሁሉ አባት’ እንደሆነ ይናገራል።—ሮም 4:11
አብርሃም እንዲህ ያለ አክብሮት ሊያተርፍ የቻለው ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ወዳጅ እንደሆነ በቀጥታ የተገለጸው ብቸኛው ሰው አብርሃም ነው! ቅዱሳን መጻሕፍት፣ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሳይሆን በሦስት ቦታዎች ላይ አብርሃም የአምላክ ወዳጅ እንደሆነ ይናገራሉ።—2 ዜና መዋዕል 20:7፤ ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23
በሌሎች መንገዶች ግን አብርሃም እንደ እኛው ዓይነት ሰው ነበር። በሕይወቱ ውስጥ እኛ የሚያጋጥሙን ዓይነት በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሙት ሲሆን እነዚህን ሁኔታዎችም በጽናት ተወጥቷቸዋል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለዚህ ታላቅ ሰው ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።
የኋላ ታሪኩ
አብርሃም የተወለደው በ2018 ዓ.ዓ. ሲሆን ያደገው ዑር በተባለች ከተማ ነበር። (ዘፍጥረት 11:27-31) ዑር ትልቅና የበለጸገች ከተማ ነበረች። በሌላ በኩል ግን በከተማዋ ውስጥ ጣዖት አምልኮ ተስፋፍቶ ነበር። የአብርሃም አባት የሆነው ታራም ቢሆን የተለያዩ አማልክትን ጣዖታት የሚያመልክ ሰው ሳይሆን አይቀርም። (ኢያሱ 24:2) አብርሃም ግን ሕይወት አልባ የሆኑ ጣዖታትን ከማምለክ ይልቅ ይሖዋንb ብቻ ያመልክ ነበር።
አብርሃም፣ ይሖዋን ብቻ እንዲያመልክ ያነሳሳው ምን ነበር? አብርሃም የተወለደው የኖኅ ልጅ የሆነው ሴም ከመሞቱ ከ150 ዓመት በፊት ስለነበር ከሴም ጋር በአንድ ዘመን ኖሯል። አብርሃም በዕድሜ በጣም ከሚበልጠው ከሴም ጋር ተቀራርቦ ከነበረ ምን ጥቅም አግኝቶ ሊሆን ይችላል? ዓለምን ካጠፋው ጎርፍ ስለተረፈበት ሁኔታ ከራሱ ከሴም አንደበት መስማት ይችል ነበር። ከዚህም ሌላ ሴምንና ቤተሰቡን ከጥፋቱ ያተረፈውን አምላክ ማለትም ይሖዋን የማምለክን አስፈላጊነት ተምሮ ሊሆን ይችላል።
አብርሃም ስለ እውነተኛው አምላክ የተማረው ከሴምም ይሁን በሌላ መንገድ፣ ያወቀው ነገር በጎ ተጽዕኖ አሳድሮበታል። ‘ልብን የሚመረምረው’ ይሖዋ፣ አብርሃምን ሲመለከተው መልካም ባሕርያቱን ያስተዋለ ሲሆን እነዚህን ባሕርያት ይበልጥ እንዲያዳብር ረድቶታል።—ምሳሌ 17:3፤ 2 ዜና መዋዕል 16:9
ያሳለፈው ሕይወት
አብርሃም አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት መርቷል፤ በሕይወቱ ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ቢያጋጥሙትም ሕይወቱ ፈጽሞ ትርጉም የለሽ አልነበረም። ካጋጠሙት ሁኔታዎች መካከል ጥቂቶቹን እስቲ እንመልከት።
▪ አብርሃም በዑር ይኖር በነበረበት ወቅት አምላክ የትውልድ አገሩን ትቶ እሱ ወደሚያሳየው ቦታ እንዲሄድ አዝዞት ነበር። አብርሃምና ሣራ፣ አምላክ አገራቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ የፈለገው ለምን እንደሆነና ወደ የት እንደሚሄዱ ባያውቁም የተሰጣቸውን መመሪያ ታዝዘዋል። ከጊዜ በኋላ አብርሃምና ሣራ በከነዓን ምድር በድንኳን መኖር የጀመሩ ሲሆን ሕይወታቸውን ሙሉ እንደ መጻተኛ ሆነው ኖረዋል።—የሐዋርያት ሥራ 7:2, 3፤ ዕብራውያን 11:8, 9, 13
▪ እነዚህ ባልና ሚስት ገና ልጅ ሳይወልዱ ይሖዋ፣ አብርሃምን ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገው ቃል ገብቶለት ነበር። ይሖዋ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በእሱ አማካኝነት እንደሚባረኩም ለአብርሃም ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 11:30፤ 12:1-3) ከጊዜ በኋላም ይሖዋ ይህንን ቃሉን በድጋሚ አረጋግጦለታል። ዘሮቹ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዙ ለአብርሃም ነግሮታል።—ዘፍጥረት 15:5, 6
▪ አብርሃም የ99 ዓመት ሰው እያለ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሊሆናት አካባቢ ይሖዋ፣ ለእነዚህ ባልና ሚስት ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገባላቸው። ይህ በሰዎች ዓይን የማይቻል ነገር ቢመስልም አብርሃምና ሣራ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር [እንደሌለ]” ብዙም ሳይቆይ ተገንዝበዋል። (ዘፍጥረት 18:14) ይሖዋ ይህን ቃል ከገባ ከአንድ ዓመት በኋላ አብርሃም በ100 ዓመቱ የወንድ ልጅ አባት ሆነ፤ ልጁንም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። (ዘፍጥረት 17:21፤ 21:1-5) አምላክ፣ በዚህ ልጅ ማለትም በይስሐቅ በኩል ታላቅ በረከት እንደሚያገኙ ቃል ገባ።
▪ ይስሐቅ ከተወለደ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይሖዋ አብርሃምን እንግዳ የሆነ ነገር እንዲያከናውን ይኸውም የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ ጠየቀው፤ በወቅቱ ይስሐቅ አግብቶ ልጆች አልወለደም ነበር።c አብርሃም ልጁን ማጣቱ በጣም እንደሚያስጨንቀው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ያም ቢሆን የአምላክን መመሪያ በመታዘዝ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ተዘጋጀ። አምላክ ቃሉን ለመፈጸም ሲል አስፈላጊ ከሆነ ይስሐቅን ከሞት እንኳ ሊያስነሳው እንደሚችል አብርሃም ጠንካራ እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:19) አብርሃም ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ እጁን ባነሳበት ቅጽበት አምላክ ጣልቃ በመግባት የይስሐቅ ሕይወት እንዲተርፍ አደረገ። ይህ የአምላክ አገልጋይ ላሳየው አስደናቂ ታዛዥነት ይሖዋ ያመሰገነው ሲሆን ቀደም ሲል የገባለትን ቃል እንደገና ደገመለት።—ዘፍጥረት 22:1-18
▪ አብርሃም 175 ዓመት ከኖረ በኋላ በሞት አንቀላፋ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ” ይላል። (ዘፍጥረት 25:7, 8) በመሆኑም አምላክ ለአብርሃም የተናገረው ሌላ ነገር ይኸውም ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንደሚሞት የገባለት ቃል ተፈጽሟል።—ዘፍጥረት 15:15
የተወው ቅርስ
ስለ አብርሃም ስናስብ፣ በሃይማኖት ሰዎችና በታሪክ የሚዘከር በጥንት ዘመን የኖረ ግለሰብ ከመሆኑ ባለፈ ወደ አእምሯችን የሚመጡ ነገሮች አሉ። ዛሬም ቢሆን ታሪኩ ሕያው ከመሆኑም ሌላ ሁላችንም ልንከተለው የምንችል ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዕብራውያን 11:8-10, 17-19) አብርሃም ያንጸባረቃቸውን አራት ግሩም ባሕርያት እስቲ እንመልከት። መጀመሪያ የምንመለከተው በዋነኝነት የሚታወቅበትን ባሕርይ ይኸውም እምነቱን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአብርሃም ስም “አብራም” ነበር፤ ሚስቱ ደግሞ “ሦራ” ትባል ነበር። ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ የአብራምን ስም ወደ “አብርሃም” የቀየረው ሲሆን ትርጉሙ “የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው፤ ሦራን ደግሞ “ሣራ” ያላት ሲሆን ፍቺው “ልዕልት” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 17:5, 15) ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ እነዚህን ሰዎች አብርሃም እና ሣራ ብለን እንጠራቸዋለን።
b የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።
c በዚህ መጽሔት ገጽ 23 ላይ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . . አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግ አምላክ የጠየቀው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ሰው
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ በመጀመሪያዎቹ አሥር ምዕራፎች ላይ የአቤልን፣ የሄኖክንና የኖኅን ጨምሮ የበርካታ የእምነት ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ይዘግባል። ቀጣዮቹ 15 ምዕራፎች ግን በዋነኝነት በአንድ ሰው ይኸውም በአብርሃም ሕይወት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጹት ከአብርሃም ጋር በተያያዘ ነው። ለምሳሌ በአብርሃም የሕይወት ታሪክ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እናገኛለን፦
▪ አምላክ ለአገልጋዮቹ ጋሻ እንደሆነ ወይም ከጥቃት እንደሚከላከልላቸው የሚገልጸው የመጀመሪያው ሐሳብ።—ዘፍጥረት 15:1፤ በተጨማሪም ዘዳግም 33:29ን፣ መዝሙር 115:9ን እና ምሳሌ 30:5ን ተመልከት።
▪ በአምላክ ስለማመን የሚናገረው የመጀመሪያው ዘገባ።—ዘፍጥረት 15:6
▪ ነቢይ የሚለው ቃል መጀመሪያ የሚገኝበት ቦታ።—ዘፍጥረት 20:7
▪ ወላጅ ለልጁ ስላለው ፍቅር የሚገልጸው የመጀመሪያው ዘገባ።—ዘፍጥረት 22:2