የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w12 10/15 ገጽ 3-6
  • ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ብራዚል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ብራዚል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ጆሮዬን ማመን አቃተኝ”
  • አገልግሎቱን መለስ ብሎ እንዲቃኝ አነሳሳው
  • የሙዚቃ ባለሙያ ወይስ አገልጋይ?
  • “የግድ እዚያ መቆየት ነበረብኝ”
  • የይሖዋን ግብዣዎች መቀበል በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ኢኳዶር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • በፊትና አሁን—ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አገኘች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እድገት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
w12 10/15 ገጽ 3-6

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል​—ብራዚል

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ሩብያ የተባለች አንዲት እህት (አሁን 30 ዓመቷ ነው) ሳንድራ የተባለችን በደቡባዊ ብራዚል በሚገኝ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት የምታገለግል እህት ለመጠየቅ ሄዳ ነበር። ሩብያ እዚያ እያለች ያጋጠማት ነገር በጥልቅ ስለነካት አኗኗሯን ለመቀየር ተነሳሳች። ያጋጠማት ነገር ምን ነበር? እስቲ እሷ ራሷ የምትለንን እንስማ።

“ጆሮዬን ማመን አቃተኝ”

ሳንድራ እና ሩብያ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ

“ሳንድራ መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠናት አንዲት ሴት ጋ አብረን ሄድን። እያጠናን እያለ ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ ‘ሳንድራ፣ አብረውኝ የሚሠሩ ሦስት ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይፈልጋሉ፤ ሆኖም በዚህ ዓመት ፕሮግራምሽ በጣም የተጣበበ እንደሆነ ስለማውቅ ተራቸው እስኪደርስ መጠበቅ እንዳለባቸው ነግሬያቸዋለሁ።’ ይህን ስሰማ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ። ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ተራቸው እስኪደርስ መጠበቅ ነበረባቸው! እኔ ባለሁበት ጉባኤ አንድ ጥናት እንኳ ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረግ አስፈልጎኛል። በዚያች ቅጽበት፣ በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የመርዳት ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የምኖርበትን ትልቅ ከተማ ለቅቄ ሳንድራ በአቅኚነት ወደምታገለግልበት ከተማ መጣሁ።”

ታዲያ ሩብያ ምን አጋጥሟት ይሆን? እንዲህ ብላለች፦ “ወደዚያ በተዛወርኩ በሁለት ወራት ውስጥ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመርኩ። ነገሩ እውነት ባይመስልም፣ ብዙም ሳይቆይ እኔም እንደ ሳንድራ ፕሮግራሜ በመጣበቡ ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች ተራ እስኪደርሳቸው እንዲጠብቁ ማድረግ ነበረብኝ!”

አገልግሎቱን መለስ ብሎ እንዲቃኝ አነሳሳው

ድዬጎ

በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ድዬጎ ፕሩዴንቶፑሊስ በተባለች በደቡባዊ ብራዚል የምትገኝ አነስተኛ ከተማ የሚያገለግሉ የተወሰኑ አቅኚዎችን ለመጠየቅ ሄዶ ነበር። ድዬጎ በዚያ ያሳለፈውን ጊዜ ፈጽሞ አይረሳውም፤ የተመለከተው ነገር አገልግሎቱን መለስ ብሎ እንዲቃኝ አነሳሳው። እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት በየወሩ ጥቂት ሰዓታት ከማሳለፍ ውጪ በጉባኤዬ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ አላደርግም ነበር። ከእነዚህ አቅኚዎች ጋር ጊዜ ማሳለፌ እንዲሁም ተሞክሯቸውን መስማቴ እነሱ በአገልግሎታቸው ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ እንድገነዘብ አደረገኝ፤ በሌላ በኩል ግን እኔ ለአገልግሎት ያን ያህል ቅንዓት እንደሌለኝ ተሰማኝ። አቅኚዎቹ ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ስመለከት እኔም እንደ እነሱ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት ተመኘሁ።” ድዬጎ እነዚያን አቅኚዎች ጠይቆ ከተመለሰ በኋላ እሱም አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።

አንተም እንደ ድዬጎ በስብከቱ ሥራ የምትካፈል እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምትገኝ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ብትሆንም አገልግሎት እንዲሁ በዘልማድ የምታከናውነው አሰልቺ ሥራ ሆኖብሃል? ከሆነ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም እንድትችል በሕይወትህ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ? በእርግጥ፣ የተደላደለ ኑሮህን ትተህ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አስቸጋሪ መስሎ ሊታይህ ይችላል። ይሁን እንጂ በርካታ ወጣቶች ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ በግቦቻቸውና በሚፈልጓቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው ማገልገል ችለዋል። ከእነዚህ መካከል እስቲ የብሩኖን ምሳሌ እንመልከት።

የሙዚቃ ባለሙያ ወይስ አገልጋይ?

ብሩኖ ጊታር ሲያስተምር

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ብሩኖ (አሁን 28 ዓመቱ ነው) በአንድ ታዋቂ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እየተማረ ነበር፤ የኦርኬስትራ ሙዚቃ መሪ የመሆን ግብ ነበረው። እንዲያውም በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ስላገኘ የኦርኬስትራ ሙዚቃ እንዲመራ በተለያዩ ወቅቶች ይጋበዝ ነበር። የተዋጣለት የሙዚቃ ባለሙያ የመሆን አጋጣሚ ከፊቱ ተዘርግቶለት ነበር። “ያም ቢሆን በሕይወቴ ውስጥ የሆነ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር” ይላል ብሩኖ። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሕይወቴን ለይሖዋ ብወስንም ራሴን ሙሉ በሙሉ ለእሱ እንዳልሰጠሁ አውቅ ነበር፤ ይህም ውስጤን ይረብሸኝ ነበር። ይህን ስሜቴን አውጥቼ ለይሖዋ ነገርኩት፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞችን አነጋገርኩ። ጉዳዩን በቁም ነገር ካሰብኩበት በኋላ አገልግሎቴን ከሙዚቃ ለማስቀደም ወሰንኩ፤ በመሆኑም ከሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ወጣሁና የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውሬ ማገልገል ጀመርኩ።” ብሩኖ ምን አጋጥሞት ይሆን?

ብሩኖ ከሳኦ ፓውሎ ከተማ 260 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኝ ግዋፒያራ የተባለች ትንሽ ከተማ (7,000 ገደማ ነዋሪዎች አሏት) ተዛወረ። ይህ ትልቅ ለውጥ ማድረግ የሚጠይቅ ነበር። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “በምኖርባት ትንሽ ቤት ውስጥ ማቀዝቀዣ፣ ቴሌቪዥንም ሆነ ኢንተርኔት የለም። ያም ሆኖ በዚህ ቤት በመኖሬ ከዚያ በፊት ያልነበሩኝን ነገሮች ይኸውም በግቢዬ ውስጥ የጓሮ አትክልት የማለማበት መሬትና የፍራፍሬ ዛፎች ያሉበት የአትክልት ቦታ አገኘሁ!” ብሩኖ በዚያ አካባቢ በሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ የሚያገለግል ሲሆን በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ ምግብ፣ ውኃና ጽሑፎች በቦርሳው ይዞ ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ለመስበክ በሞተር ብስክሌት ይሄዳል። በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን ጨርሶ ሰምተው አያውቁም። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “18 ጥናቶች ነበሩኝ። እነዚህ ጥናቶቼ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ሲያደርጉ መመልከቴ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል!” አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በሕይወቴ ውስጥ እንደጎደለኝ ይሰማኝ የነበረውን ነገር እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ፤ ይህም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደም የሚያስገኘው ጥልቅ የእርካታ ስሜት ነው። በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት ብመራ ኖሮ እንዲህ ዓይነቱን እርካታ ፈጽሞ ማግኘት አልችልም ነበር።” ብሩኖ ‘ታዲያ በምን ትተዳደራለህ?’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት ፈገግ ብሎ “ጊታር አስተምራለሁ” በማለት መለሰ። ብሩኖ አሁንም ቢሆን የሙዚቃ ባለሙያ ነው ማለት ይቻላል።

“የግድ እዚያ መቆየት ነበረብኝ”

ቢያንካ እና ጁሊያና በስብከቱ ሥራ ላይ

በ20ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የምትገኘው ማሪያና የነበረችበት ሁኔታ ከብሩኖ ጋር ተመሳሳይ ነው። ጠበቃ የነበረች ሲሆን ዳጎስ ያለ ደሞዝ ታገኝ ነበር፤ ያም ቢሆን እርካታ አልነበራትም። ማሪያና “ሕይወቴ ‘ነፋስን እንደ መከተል’ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። (መክ. 1:17) በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ማሪያናን አቅኚ እንድትሆን አበረታቷት። እሷም ጉዳዩን በጥሞና ካሰበችበት በኋላ ቢያንካ፣ ካሮሊን እና ጁሊያና ከተባሉ ጓደኞቿ ጋር ሆና ባራ ዱ ቡግሬስ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ጉባኤ ለማገልገል ወሰኑ። በቦሊቪያ አቅራቢያ ያለችው ይህች ከተማ የምትገኘው ከሚኖሩበት አካባቢ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ነው። ታዲያ ማሪያና ምን አጋጠማት?

ማሪያና እና ካሮሊን ከአንድ ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ሲያደርጉ

እንዲህ ብላለች፦ “ወደዚያ ስሄድ ያሰብኩት ሦስት ወር ለመቆየት ነበር። ሆኖም ያሰብኩት ጊዜ ሲያልቅ 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየመራሁ ነበር! ጥናቶቼ በእውነት ውስጥ እድገት እንዲያደርጉ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። በመሆኑም አካባቢውን ለቅቄ ልሄድ እንደሆነ ለጥናቶቼ ለመናገር ድፍረት አጣሁ። የግድ እዚያ መቆየት ነበረብኝ።” ሌሎቹ ሦስት እህቶችም ተመሳሳይ ውሳኔ አደረጉ። ታዲያ ማሪያና ያደረገችው ውሳኔ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ አስችሏታል? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ በእኔ እንደሚጠቀም ማወቄ ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርብኛል። ጊዜዬንና ጉልበቴን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሥራ ለማከናወን ማዋሌ ትልቅ በረከት እንደሆነ ይሰማኛል።” ካሮሊን የተናገረችው የሚከተለው ሐሳብ የአራቱን እህቶች ስሜት ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል፦ “ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም የምችለውን ያህል እያደረግሁ ስለሆነ ማታ ወደ መኝታዬ ስሄድ በውስጤ ጥልቅ እርካታ ይሰማኛል። ትኩረቴ በሙሉ ያረፈው ጥናቶቼን መርዳት በምችልበት መንገድ ላይ ነው። ጥናቶቼ እድገት ሲያደርጉ መመልከት ልዩ ስሜት ይፈጥራል። ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ’ የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት በራሴ ሕይወት ተመልክቻለሁ።”—መዝ. 34:8

ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወጣት ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱን ምሥራች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለመስበክ ራሳቸውን ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ሲያቀርቡ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (መዝ. 110:3፤ ምሳሌ 27:11) እነዚህ ፈቃደኛ አገልጋዮች በሙሉ የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ።—ምሳሌ 10:22

“ምንም ነገር ጎድሎብን አያውቅም”

ዥዋው፣ ፓውሎና ኖኤሚ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ

ዥዋው ፓውሎ እና ባለቤቱ ኖኤሚ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለማገልገል እንደሚፈልጉ ሲናገሩ አንዳንዶች ተስፋ የሚያስቆርጥ አስተያየት ሰጥተዋቸው ነበር። በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞች እንደሚከተሉት ያሉ ሐሳቦችን ሰንዝረው ነበር፦ “ወደ ትንሽ ከተማ ከሄዳችሁ የኢኮኖሚ ችግር ሊያጋጥማችሁ ይችላል።” “በጉባኤያችን ውስጥ ገና ብዙ የሚሠራ እያለ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ምን አስፈለጋችሁ?” ዥዋው ፓውሎ “እንደ እነዚህ ያሉት በአሳቢነት የተነገሩ ሆኖም ተስፋ የሚያስቆርጡ አስተያየቶች ቅንዓታችንን እንዳያቀዘቅዙት መታገል ነበረብን” ብሏል። ዥዋው ፓውሎ እና ኖኤሚ፣ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው ማገልገል ከጀመሩ ብዙ ዓመታት አልፈዋል፤ ዛሬም ቢሆን አገልግሎታቸውን ለማስፋት ከዓመታት በፊት ባደረጉት ውሳኔ በመጽናታቸው ደስተኞች ናቸው። ዥዋው ፓውሎ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ወደዚህ አካባቢ ተዛውረን ከመጣን ወዲህ ምንም ነገር ጎድሎብን አያውቅም። እንዲያውም በእርግጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ረገድ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከበፊቱ የተሻለ ነው።” ኖኤሚም አክላ “እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማድረጋችን ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይደለም” ብላለች።

በትናንሽ ከተሞች ውስጥ መተዳደሪያ ማግኘት ተፈታታኝ ነው። ታዲያ ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች የተዛወሩት አስፋፊዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት የቻሉት እንዴት ነው? ሥራ ፈጣሪዎች በመሆን ነው። አንዳንዶች እንግሊዝኛ ወይም ሌላ ቋንቋ ያስተምራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ተማሪዎችን ያስጠናሉ፤ እንደ ልብስ መስፋትና ቤት ቀለም መቀባት የመሳሰሉትን ወይም በትርፍ ጊዜያቸው ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ሌሎች ሥራዎችን የሚሠሩም አሉ። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው የሚያገለግሉ ወንድሞች በሙሉ በጋራ የሚስማሙበት አንድ ነገር አለ። እዚያ በማገልገላቸው የሚያጋጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ከሚያገኙት በረከት አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም!

ናፍቆትን መቋቋም

ቲያጉ አገልግሎት ላይ

ቲያጉ፦ “ወደ አዲሱ ጉባኤ ከሄድኩ ብዙም ሳይቆይ ውስጤ መረበሽ ጀመረ። በከተማው ውስጥ የነበሩት አስፋፊዎች በጣም ጥቂት ሲሆኑ ለትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ የሚሆን ምንም ነገር አልነበረም። በመሆኑም ናፍቆት አስቸገረኝ። ይህን ስሜት ለማጥፋት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ በጉባኤ ውስጥ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል! አዳዲስ ጓደኞች ያፈራሁ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እንደ ቀድሞው ደስተኛ መሆንና አዲሱን ሁኔታ መላመድ ቻልኩ።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ