የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 4/1 ገጽ 4-7
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት—ለሁሉም ሰው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት—ለሁሉም ሰው
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ ምን ይመስላል?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
    በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት መደሰት የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2012
  • እስካሁን የተማርከውን ወደኸዋል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ማስተዋወቂያ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 4/1 ገጽ 4-7
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት

ሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መማር ትፈልጋለህ?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት—ለሁሉም ሰው

የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ በደንብ ይታወቃሉ። ይሁን እንጂ አንተ፣ በመላው ዓለም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስተምርበት ፕሮግራም እንዳለን ታውቃለህ?

አንድ ሰው በሥራ ቦታው ላይ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ሲማር

በ2014 በ240 አገሮች የሚኖሩ ከ8,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በየወሩ 9,500,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስተምረዋል።a መጽሐፍ ቅዱስን የምናስተምራቸው ሰዎች ብዛት፣ 140 ገደማ የሚሆኑ አገሮች በተናጠል ካላቸው የሕዝብ ብዛት ይበልጣል!

የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የማስተማር ሥራ ለማከናወን በየዓመቱ ወደ አንድ ቢሊዮን ተኩል የሚጠጉ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎችን 700 በሚያህሉ ቋንቋዎች ያዘጋጃሉ! ይህ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የሕትመት ሥራ ሰዎች በሚፈልጉት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ያስችላቸዋል።

“ትምህርት ቤት እያለሁ ማጥናት አልወድም ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ግን አስደሳች ሆኖልኛል። ደግሞም የተማርኳቸው ነገሮች በጣም አጽናንተውኛል!”—ካትሌጎ፣ ደቡብ አፍሪካ

“ከትምህርቱ ለጥያቄዎቼ መልስ ያገኘሁ ከመሆኑም ሌላ ብዙ ነገር አውቄያለሁ።” —በርታ፣ ሜክሲኮ

“መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩኝ ቤቴ ውስጥ እንዲሁም ለእኔ በሚመቸኝ ሰዓት ላይ ነበር። ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ!”—ኤዚኪዬል፣ ብራዚል

“ትምህርቱ ይካሄድ የነበረው የእኔን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን አንዳንዴ ከ15 እስከ 30 ደቂቃ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ እማር ነበር።”—ቪኒያና፣ አውስትራሊያ

“ትምህርቱ የሚሰጠው በነፃ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ በጣም አስደሳች ነበር!”—ኤሚ፣ ቤኒን

“የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዬ በጣም ታጋሽና ደግ ነበረች። ከእሷ ጋር በጣም ተቀራርበናል።”—ካረን፣ ሰሜን አየርላንድ

“ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መሆን ሳይጠበቅባቸው መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ።”—ዴንተን፣ እንግሊዝ

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራማችንን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱ የሚሰጥበት መንገድ ምን ይመስላል?

የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ከጉዳዩ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመረምራለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፦ አምላክ ማን ነው? ምን ዓይነት ባሕርያት አሉት? አምላክ ስም አለው? የሚኖረው የት ነው? ከእሱ ጋር መቀራረብ እንችላለን? በእርግጥ፣ አስቸጋሪ የሚሆነው የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኝበትን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፈልጎ ማግኘት ነው።

ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው በቀላሉ መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀመው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን ባለ 224 ገጽ መጽሐፍb ነው። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች መረዳት እንዲችሉ ማገዝ ነው። ይህ መጽሐፍ ስለ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰው ልጆች ላይ ስለሚደርሰው መከራ፣ ስለ ትንሣኤ፣ ስለ ጸሎትና ስለ ሌሎች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች የሚገልጹ ትምህርቶችን አካትቶ የያዘ ነው።

ትምህርቱ የሚሰጠው መቼና የት ነው?

ለአንተ አመቺ የሆነውን ጊዜና ቦታ መምረጥ ትችላለህ።

አንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በየሳምንቱ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ ይመድባሉ። ነገር ግን ትምህርቱ የሚወስደው ጊዜ እንደ ሁኔታው ሊለዋወጥ ይችላል። ፕሮግራሙን ለአንተ እንደሚስማማ ማስተካከል እንችላለን። አንዳንዶች በየሳምንቱ ለ10 ወይም ለ15 ደቂቃ ብቻ ይማራሉ።

ትምህርቱ ምን ያህል ያስከፍላል?

ትምህርቱንም ሆነ የመማሪያ ጽሑፎቹን የምንሰጠው በነፃ ነው። ይህም ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠው መመሪያ ጋር የሚስማማ ነው።—ማቴዎስ 10:8

ትምህርቱን ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?

ይህ በአንተ ላይ የተመካ ነው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ 19 ትምህርቶችን ይዟል። ከመጽሐፉ ውስጥ አንተ የምትፈልጋቸውን ወይም ሁሉንም ትምህርቶች ለአንተ በሚስማማህ ፍጥነት መማር ትችላለህ።

ትምህርቱን ከወሰድኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክር መሆን ይጠበቅብኛል?

አይጠበቅብህም። እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን ለማመን ያለውን መብት እናከብራለን። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያገኙ ሰዎች ባወቁት ነገር ላይ ተመሥርተው ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

jw.org የተሰኘው ድረ ገጽ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮችና ስለሚያከናውኑት ሥራ ትክክለኛ መረጃ ያቀርባል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሰጠኝ መጠየቅ የምችለው እንዴት ነው?

  • ሰዎች በኢንተርኔት ላይ፣ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲሁም የስልክ ማውጫን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለማግኘት ጥያቄ ሲያቀርቡ

    www.jw.org/am በተሰኘው ድረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ቅጽ ሙላ።

  • በዚህ መጽሔት ገጽ ሁለት ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች መካከል ለአንተ ቅርብ ወደሆነው አድራሻ ጻፍ።

  • በአካባቢህ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝ። ▪

a በአጠቃላይ ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራሙ የሚካሄደው ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ ወይም በቡድን በማስተማር ነው።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። ይህ መጽሐፍ ከ260 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን ከ230 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቅጂዎች ታትመዋል።

ቤተሰቦች ጥቅም አግኝተዋል

ኤዚኪዬል

“ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስትጀምር ጉልህ ለውጦች ማድረጓን አስተዋልኩ። የቤተሰብ ሕይወታችን ተሻሻለ። እየተማረች ስለነበረው ነገር ለማወቅ ስለጓጓሁ እኔም መማር ጀመርኩ። የተማርኩት ነገር ባሕርዬን እንዳሻሽል ረዳኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ቤተሰባችንን አንድ አድርጎታል።”—ኤዚኪዬል

ካረን

“መጽሐፍ ቅዱስን መማር ከጀመርኩ በኋላ የነበረብኝን የዕፅ ሱስ ማሸነፍ ቻልኩ፤ ከልክ በላይ መጠጣት አቆምኩ፣ እንዲሁም ቁጣዬን መቆጣጠር ተማርኩ። አሁን ቤቴ ንጹሕና ያልተዝረከረከ ነው። ለቤተሰቤ ያለኝ ፍቅር ያደገ ሲሆን እነሱን የሚያስደስታቸውን ነገር ማድረግ ደስ ይለኛል። በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ።”—ካረን

ቪኒያና

“አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በመማሬ ነቅፈውኝ ነበር። ባለቤቴ ግን ይህን ውሳኔዬን በመደገፍ ‘ሰዎች ስለሚሉት ነገር ደንታ የለኝም። ለእኔ ትልቁ ነገር አንቺ ጥሩ ለውጥ እያደረግሽ መሆኑ ነው። እያደረግሽ ያለሽውን ነገር ቀጥዪበት’ አለኝ። የቤተሰብ ሕይወታችን የአሁኑን ያህል ጥሩ ሆኖ አያውቅም!”—ቪኒያና

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ