የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 7/1 ገጽ 8-9
  • ስለ አደጋ በማሰብ መጨነቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ አደጋ በማሰብ መጨነቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጸሎት ይረዳል
  • የወደፊቱ ተስፋችን
  • ጭንቀት የሌለበት ቦታ የለም!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • በወንዶች ላይ የሚከሰት ጭንቀት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን የመፍትሔ ሐሳብ ይሰጣል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ጭንቀትህን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 7/1 ገጽ 8-9

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ጭንቀትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

ስለ አደጋ በማሰብ መጨነቅ

አሎና “የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉን ስሰማ ልቤ በኃይል መምታት ይጀምራል” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከቦምብ ድብደባው ለመሸሸግ ወደተዘጋጀው መጠለያ እየሮጥኩ እሄዳለሁ፤ እዚያም ሆኜ ግን እጨነቃለሁ። ምንም መደበቂያ የሌለበት አካባቢ ስሆንማ ጭንቀቴ ይጨምራል። አንድ ቀን መንገድ ላይ እየሄድኩ ሳለ የምሆነው ጠፍቶኝ ማልቀስ ጀመርኩ፤ መተንፈስም አቃተኝ። ለመረጋጋት ሰዓታት ፈጅቶብኛል። ከዚያም የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉ በድጋሚ ጮኸ።”

አሎና የቦምብ ፍንዳታ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብላ ተጨንቃለች

አሎና

ጦርነት ከብዙ የአደጋ መንስኤዎች አንዱ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንተ ወይም የቤተሰብህ አባል ለሕይወት የሚያሰጋ በሽታ እንዳለባችሁ ስታውቅ በመብረቅ የተመታህ ያህል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ሌሎች ደግሞ ስለወደፊቱ ጊዜ በመፍራት ሊጨነቁ ይችላሉ። ብዙዎች ‘ጦርነት፣ ወንጀል፣ ብክለት፣ የአየር ንብረት መዛባትና ወረርሽኝ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው፤ ታዲያ ልጆቻችን ወይም የልጅ ልጆቻችን በምን ዓይነት ዓለም ውስጥ ለመኖር ይገደዱ ይሆን?’ እያሉ ይጨነቃሉ። እንዲህ ዓይነቱን ጭንቀት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

መጥፎ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድመን ማወቃችን “ብልህ ሰው አደጋ አይቶ ይሸሸጋል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል። (ምሳሌ 27:12) አካላዊ ጤንነታችንን ለመንከባከብ ጥረት እንደምናደርግ ሁሉ አእምሯዊና ስሜታዊ ጤንነታችንንም ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል። ዓመፅ የሞላበት መዝናኛ ሌላው ቀርቶ ዘግናኝ ምስሎች የሚታዩባቸው የዜና ዘገባዎች እኛንም ሆነ ልጆቻችንን ለጭንቀት ሊዳርጉ ይችላሉ። ከእነዚህ ነገሮች መራቅ በገሃዱ ዓለም ያለውን እውነታ ላለማየት ዓይንን እንደመጨፈን ሊቆጠር አይገባም። አምላክ የፈጠረን መጥፎ ነገሮችን እያውጠነጠንን እንድንጨነቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘እውነት፣ ጽድቅ፣ ንጹሕና ተወዳጅ ስለሆኑ ነገሮች’ እንድናስብ ነው። እንዲህ ካደረግን ‘የሰላም አምላክ’ አእምሯችንንና ልባችንን ያረጋጋልናል።—ፊልጵስዩስ 4:8, 9

ጸሎት ይረዳል

ጠንካራ እምነት ጭንቀትን ለመቋቋም ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ “በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 4:7) አምላክ ‘የምንጠይቀውን ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ’ እንዲረዳን እንዲሁም ጥበብና ድፍረት እንዲሰጠን መለመን እንችላለን፤ ይህም ያለንን አጋጣሚ ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ያስችለናል።—1 ዮሐንስ 5:15

አቪና አሎና አምላክ እንዲረዳቸው ሲጸልዩ

ከባሏ ከአቪ ጋር

መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” አምላክ ሳይሆን ሰይጣን እንደሆነና “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር” እንደሚገኝ ይገልጻል። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በመሆኑም ኢየሱስ “ከክፉው አድነን” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እየተናገረ አልነበረም። (ማቴዎስ 6:13) አሎና እንዲህ ብላለች፦ “የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወሉ መጮኽ ሲጀምር ከልክ በላይ እንዳልረበሽ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ውዱ ባለቤቴ ስልክ ይደውልልኝና አብሮኝ ይጸልያል። ጸሎት በእርግጥ ይረዳል።” መጽሐፍ ቅዱስም “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በቅንነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ይላል።—መዝሙር 145:18 የግርጌ ማስታወሻ

የወደፊቱ ተስፋችን

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት አላግባብ የሚያስጨንቁንን ነገሮች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግድልናል። አምላክ “የሰላም መስፍን” በሆነው በኢየሱስ አማካኝነት “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።” (ኢሳይያስ 9:6፤ መዝሙር 46:9) “[አምላክ] በብዙ ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ . . . አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም። . . . የሚያስፈራቸውም አይኖርም።” (ሚክያስ 4:3, 4) ደስተኛ ቤተሰቦች “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።” (ኢሳይያስ 65:21) “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24

በዛሬው ጊዜ የተለያዩ የአደጋ ማስጠንቀቂያዎች ቢኖሩም “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሙሉ በሙሉ እንዳይደርሱ መከላከል ወይም ባልሆነ ሰዓት ያልሆነ ቦታ መገኘት ከሚያስከትለው አደጋ ማምለጥ ሁልጊዜ ይቻላል ማለት አይደለም። (መክብብ 9:11) ባለፉት መቶ ዘመናት እንደታየው ሁሉ ጦርነት፣ ዓመፅና በሽታ የጥሩ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፋቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ምን ተስፋ ይኖራቸዋል?

ምን ያህል ሰዎች የዚህ ሰለባ እንደሆኑ የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነው፤ ያም ሆነ ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙታን እንደገና በሕይወት ይኖራሉ። ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ከዚያ የሚወጡበት’ ጊዜ እስኪመጣ ይኸውም ፍጹም የማስታወስ ችሎታ ያለው አምላክ እስኪያስነሳቸው ድረስ ግን በሞት አንቀላፍተው ይቆያሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን” በማለት ትንሣኤ የተረጋገጠ ተስፋ መሆኑን ይነግረናል። (ዕብራውያን 6:19) ደግሞም አምላክ “[ኢየሱስን] ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።”—የሐዋርያት ሥራ 17:31

በአሁኑ ጊዜ አምላክን ለማስደሰት የተቻላቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ሰዎችም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ፖል፣ ጃኔትና አሎና ተግባራዊ የሆኑ የጥበብ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ በመቅረብና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚገልጸው ተስፋ ላይ እምነት በማሳደር የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን በተሳካ መንገድ ተቋቁመው እየኖሩ ነው። እናንተም ‘በእሱ ስለታመናችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ እንዲሞላባችሁ’ እንመኛለን።—ሮም 15:13

የባለሙያ እርዳታ ማግኘት ያስፈልግህ ይሆን?

ተግባራዊ እርምጃዎችን ከወሰድክም በኋላ ጭንቀት ዕለታዊ ሕይወትህን ማወኩን የሚቀጥል ከሆነ ሐኪም ማማከር ያስፈልግህ ይሆናል። አንድ ሰው የገጠመው ችግር ወይም ውጥረት ከልክ በላይ እንዲጨነቅ የሚያደርገው ከሆነ ሥር የሰደደ የጤና ችግር እንዳለበት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ጭንቀት የሚከሰተው በሌላ ከባድ ውስጣዊ የጤና እክል ሊሆን ስለሚችል ሐኪምህ አጠቃላይ ምርመራ ያዝልህ ይሆናል። ከዚህ በመነሳት ሐኪሙ ተጨማሪ ሕክምና እንድትወስድ ሊረዳህ ይችላል።a

a ይህ መጽሔት አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ አስተያየት አይሰጥም። ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በተጨማሪም በመጋቢት 2012 ንቁ! ላይ የወጣውን “በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ የስሜት ቀውስ ያለባቸውን ሰዎች መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት፤ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ