የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 8/1 ገጽ 3-4
  • ስንሞት ምን እንሆናለን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስንሞት ምን እንሆናለን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሞቱ ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
  • ሲኦል ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • ትንሣኤ—ለማንና የት?
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • እውነት ሲኦል አለ? የመጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 8/1 ገጽ 3-4

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሰው ከሞተ በኋላ ዳግመኛ በሕይወት መኖር ይችላል?

ስንሞት ምን እንሆናለን?

መካነ መቃብር ውስጥ ሬሳ ሣጥን አጠገብ የቆሙ አዋቂዎችና ልጆች

“ሰው ሲሞት ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል አሊያም ወደ መንጽሔ ይሄዳል ብዬ አስብ ነበር። እርግጥ ወደ ሰማይ የሚያስገባ ጥሩ ነገር እንዳልሠራሁ አሊያም ለሲኦል የሚያበቃ ክፉ ነገር እንዳልሠራሁ አውቃለሁ። በሌላ በኩል መንጽሔ ውስጥ ምን እንዳለ በትክክል የማውቀው ነገር አልነበረም። ሰዎች ሲያወሩ ከሰማሁት ውጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጽ ሐሳብ አንብቤ አላውቅም።”—ላየነል

“ሰዎች ሁሉ ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለውን ትምህርት አውቃለሁ፤ ሆኖም አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ሞት የሁሉም ነገር ፍጻሜ እንደሆነ አድርጌ ስለማስብ ሙታን ምንም ተስፋ እንደሌላቸው ይሰማኝ ነበር።”—ፈርናንዶ

‘ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች የሆነ ቦታ ሄደው እየተሠቃዩ ይሆን? ዳግመኛ እናያቸው ይሆን? ከሆነስ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች አስበህባቸው ታውቃለህ? እባክህ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ጉዳይ ምን ብለው እንደሚያስተምሩ ለማስተዋል ሞክር። እስቲ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሞት ምን እንደሚል እንመልከት። ከዚያም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተስፋ እንመረምራለን።

የሞቱ ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም፤ ከእንግዲህም የሚያገኙት ብድራት የለም፤ ምክንያቱም የሚታወሱበት ነገር ሁሉ ተረስቷል። እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን፤ አንተ በምትሄድበት በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።”a—መክብብ 9:5, 10

በአጭር አነጋገር፣ መቃብር ሰዎች ሲሞቱ የሚያርፉበት ቦታ ሲሆን ቃሉ ምሳሌያዊ ቦታን ወይም ሁኔታን ያመለክታል፤ መቃብር ውስጥ ማሰብም ሆነ መሥራት አይቻልም። ታማኙ ኢዮብ መቃብርን እንዴት ይመለከተው ነበር? ኢዮብ በአንድ ቀን ንብረቱንና ልጆቹን በሙሉ አጣ፤ ከዚያም ክፉኛ የሚያሠቃይ እባጭ መላ ሰውነቱን ወረሰው። አምላክን “ምነው በመቃብር [“በሲኦል፣” የ1954 ትርጉም] ውስጥ በሰወርከኝ” በማለት ተማጽኖ ነበር። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7፤ 14:13) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢዮብ ሲኦልን የማቃጠያ ቦታ አድርጎ አልተመለከተውም፤ ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ወደሚሠቃይበት ቦታ ለመሄድ አይመኝም ነበር። ከዚህ ይልቅ እፎይታ የሚያገኝበት ቦታ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።

የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ከሞት ስለተነሱ ስምንት ሰዎች የሚናገረውን ታሪክ መመርመር እንችላለን።—“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ከስምንቱ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ከሞት ሲነሱ ተድላ ወይም ሥቃይ ወዳለበት ቦታ ሄደው እንደነበር አልተናገሩም። እነዚህ ሰዎች ሲሞቱ እንዲህ ወዳለ ቦታ ሄደው ቢሆን ኖሮ ስለዚህ ጉዳይ ለሰዎች አያወሩም ነበር? ደግሞስ ተናግረው ቢሆን ኖሮ ሁላችንም እንድናነበው በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይካተትም ነበር? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የትም ቦታ ላይ እንዲህ ያለ ሐሳብ ተመዝግቦ አናገኝም። እነዚህ ስምንት ሰዎች ይህን በተመለከተ ሊናገሩ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ድብን ያለ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ስለነበር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን ለመግለጽ እንቅልፍን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኙ ዳዊትም ሆነ እስጢፋኖስ ‘በሞት እንዳንቀላፉ’ ተገልጿል።—የሐዋርያት ሥራ 7:60፤ 13:36

ታዲያ የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? ከዚህ እንቅልፍ መንቃት ይችላሉ?

a በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “መቃብር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የዕብራይስጡን “ሲኦል” እና የግሪክኛውን “ሐዲስ” ያመለክታል። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሲኦል የሚለው ቃል የሞቱ ሰዎች እየተቃጠሉ የሚሠቃዩበት ቦታ እንደሆነ ያስባሉ፤ ይሁንና ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ትንሣኤዎችb

የአንዲት መበለት ልጅ፦ ነቢዩ ኤልያስ፣ በሰሜናዊ እስራኤል በሰራፕታ የምትኖር አንዲት መበለት ልጇ በሞተ ጊዜ አስነስቶላታል።—1 ነገሥት 17:17-24

የሹነማዊቷ ልጅ፦ የኤልያስ ተተኪ የሆነው ኤልሳዕ በሹነም ከተማ አንድን ልጅ ከሞት አስነስቶ ለወላጆቹ ሰጥቷቸዋል።—2 ነገሥት 4:32-37

መቃብር ውስጥ የተጣለው በድን፦ ሰዎች የአንድን ሰው አስከሬን፣ የኤልሳዕ አፅም አርፎበት በነበረው ቦታ ላይ በጥድፊያ ወርውረውት ሄዱ። የሰውየው በድን የነቢዩ ኤልሳዕን አፅም በነካ ጊዜ ሰውየው ከሞት ተነሳ።—2 ነገሥት 13:20, 21

በናይን የምትኖረው መበለት ልጅ፦ ኢየሱስ ከናይን ከተማ ውጭ ወደ ቀብር እየሄዱ ከነበሩ ሰዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ሞቶ የነበረውን ልጅ አስነስቶ እያለቀሰች ለነበረችው እናቱ ሰጣት።—ሉቃስ 7:11-15

የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፦ ኢያኢሮስ የሚባል አንድ የምኩራብ አለቃ ታማ የነበረችውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ተማጽኖት ነበር። ኢየሱስም ልጅቷ ከሞተች በኋላ ብዙም ሳትቆይ አስነስቷታል።—ሉቃስ 8:41, 42, 49-56

የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር፦ ኢየሱስ አልዓዛርን በብዙ ሰዎች ፊት ከሞት ያስነሳው በሞተ በአራተኛው ቀን ነበር።—ዮሐንስ 11:38-44

ዶርቃ፦ ሐዋርያው ጴጥሮስ በደግነቷ የምትታወቀውን ይህችን ተወዳጅ ሴት ከሞት አስነስቷታል።—የሐዋርያት ሥራ 9:36-42

አውጤኪስ፦ አውጤኪስ የሚባል አንድ ወጣት ከፎቅ ላይ ወድቆ ሕይወቱ ባለፈበት ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ አስነስቶታል።—የሐዋርያት ሥራ 20:7-12

b ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚይዘው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ ከእነዚህ ስምንት ትንሣኤዎች ፈጽሞ የተለየ ነው፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይህን እንመለከታለን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ