የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w16 ሰኔ ገጽ 16-17
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘በግንባራቸው ላይ ምልክት አድርግ’
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
  • ከጥፋት ለመትረፍ ምልክት ይደረግብህ ይሆን?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
  • ማዘንና መቃተት፣ ምልክት ማድረግ፣ ማጥፋት—መቼና እንዴት?
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
  • “አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል”
    የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
w16 ሰኔ ገጽ 16-17
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዘመናችን፣ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ ከጥፋቱ በሚተርፉ ሰዎች ላይ በማይታይ ሁኔታ ምልክት የሚያደርግባቸውም እሱ ነው

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይ የተጠቀሰው የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘ ሰው እንዲሁም የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች ማንን ያመለክታሉ?

ኢየሩሳሌምን በማጥፋቱ ሥራ የተካፈለውንና ወደፊትም በአርማጌዶን ወቅት የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት በማጥፋት የሚካፈለውን ሰማያዊ ሠራዊት ያመለክታሉ። በዚህ ረገድ ባለን ግንዛቤ ላይ እንዲህ ያለ ማስተካከያ መደረጉ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሕዝቅኤል ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. ከመጥፋቷ ቀደም ብሎ በውስጧ ይፈጸሙ የነበሩትን ክፉ ነገሮች ከተመለከተ በኋላ፣ ከዚህ ጥፋት በፊት ስለሚፈጸሙት ክንውኖች የሚያሳይ ራእይ ተመልክቷል። የማጥፊያ መሣሪያ የያዙ ስድስት ሰዎች በራእዩ ላይ አይቷል። በተጨማሪም ሕዝቅኤል፣ “በፍታ የለበሰ” እና “የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘ አንድ ሰው” ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተመልክቷል። (ሕዝ. 8:6-12፤ 9:2, 3) ይህ ሰው እንዲህ ተብሏል፦ “በከተማዋ መካከል . . . እለፍ፤ በከተማዋ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉት አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ እያዘኑና እየቃተቱ ባሉት ሰዎች ግንባር ላይም ምልክት አድርግ።” ከዚያም የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ምልክቱ ያልተደረገባቸውን ሰዎች በሙሉ እንዲገድሉ ታዘዙ። (ሕዝ. 9:4-7) ከዚህ ራእይ እኛ ምን ትምህርት እናገኛለን? ደግሞስ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ማን ነው?

ይህ ትንቢት የተነገረው በ612 ዓ.ዓ. ሲሆን የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው፣ ሕዝቅኤል ራእዩን ከተመለከተ ከአምስት ዓመት በኋላ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ሠራዊት ስትጠፋ ነው። ኢየሩሳሌምን ያጠፏት አረማውያን የሆኑት ባቢሎናውያን፣ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚዎች ሆነው አገልግለዋል። (ኤር. 25:9, 15-18) ይህ የሆነው ይሖዋ፣ ከሃዲ የነበሩትን ሕዝቡን ለመቅጣት በባቢሎናውያን ስለተጠቀመ ነው። ይሁን እንጂ ጥፋቱ ሁሉንም በጅምላ የሚደመስስ አልነበረም። ጻድቃን፣ ከክፉዎች ጋር እንዲጠፉ አልተደረገም። ይሖዋ፣ በከተማዋ ውስጥ በሚፈጸመው አስጸያፊ ድርጊት ያልተስማሙትን አይሁዳውያን ከጥፋቱ ለማትረፍ በፍቅር ተነሳስቶ ዝግጅት አድርጎ ነበር።

ሕዝቅኤል፣ ምልክት በማድረጉም ሆነ በማጥፋቱ ሥራ ተካፋይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ፍርድ የማስፈጸሙን ሥራ የመሩት መላእክት ነበሩ። በመሆኑም በዚህ ትንቢት አማካኝነት፣ በዓይን የማይታየውን ይኸውም በሰማይ የተከናወነውን ሁኔታ ማየት የቻልን ያህል ነው። ይሖዋ፣ ክፉዎችን እንዲያጠፉ ብቻ ሳይሆን ጻድቃንን ለይተው ከጥፋቱ እንዲያተርፉ ለመላእክቱ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል።a

በዚህ ራእይ ዘመናዊ ፍጻሜ ላይ፣ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ቅቡዓን ቀሪዎችን እንደሚያመለክት ከዚህ በፊት በጽሑፎቻችን ላይ ተብራርቶ ነበር። ለሚሰበከው መልእክት ቀና ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ከጥፋት ለመትረፍ በአሁኑ ጊዜ ምልክት እየተደረገባቸው እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚህ ማብራሪያ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በማቴዎስ 25:31-33 ላይ በተገለጸው መሠረት በሰዎች ላይ የሚፈርደው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በሕይወት የሚተርፉትን በግ መሰል ሰዎች፣ ጥፋት ከሚጠብቃቸው ፍየል መሰል ሰዎች በመለየት የመጨረሻ ፍርዱን የሚሰጠው በታላቁ መከራ ወቅት ነው።

ከዚህ ማስተካከያ አንጻር፣ ሕዝቅኤል ከተመለከተው ራእይ ምን እንማራለን? ቢያንስ አምስት ነገሮችን እንማራለን፦

  1. የኢየሩሳሌም ጥፋት እየተቃረበ በነበረበት ወቅት ሕዝቅኤልና ኤርምያስ ጠባቂ ሆነው አገልግለዋል፤ ኢሳይያስም ከዚያ ቀደም ብሎ ይህን ሥራ አከናውኗል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመመገብና ታላቁ መከራ ከመፈንዳቱ በፊት ለሌሎች ማስጠንቀቂያ ለማሰማት ቅቡዓን አገልጋዮቹን ባቀፈ አነስተኛ ቡድን እየተጠቀመ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቶስ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ይህን ማስጠንቀቂያ በማሰማቱ ሥራ የራሳቸው ድርሻ አላቸው።—ማቴ. 24:45-47

  2. ሕዝቅኤል ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት በማድረጉ ሥራ ተካፋይ አልነበረም፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም በዚህ ሥራ ተካፋይ አይደሉም። የእነሱ ሥራ የይሖዋን መልእክት ማስተላለፍ ሲሆን ይህም በመላእክት እየተመሩ የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ አንዱ ክፍል ነው።—ራእይ 14:6

  3. በሕዝቅኤል ዘመን፣ ቃል በቃል በግንባሩ ላይ ምልክት የተደረገበት ሰው አልነበረም። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ታዲያ ሰዎች ከጥፋቱ ለመትረፍ የሚያስችለው ምሳሌያዊ ምልክት እንዲደረግባቸው ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል? በዛሬው ጊዜ ለሚከናወነው የስብከቱ ሥራ በጎ ምላሽ መስጠት፣ አዲሱን ክርስቲያናዊ ስብዕና መልበስ፣ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰንና የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ ያስፈልጋቸዋል። (ማቴ. 25:35-40) እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉ ሰዎች፣ ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችላቸው ምልክት የሚደረግባቸው በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ይሆናል።

  4. በዘመናችን፣ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው የሚያመለክተው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፤ ከጥፋቱ በሚተርፉ ሰዎች ላይ በማይታይ ሁኔታ ምልክት የሚያደርግባቸውም እሱ ነው። እጅግ ብዙ ሕዝብ ምልክት የሚደረግባቸው፣ በጎች እንደሆኑ በታላቁ መከራ ወቅት ሲፈረድላቸው ነው። ይህም በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ያስችላቸዋል።—ማቴ. 25:34, 46b

  5. በዘመናችን፣ የማጥፊያ መሣሪያ የያዙት ስድስት ሰዎች የሚያመለክቱት ኢየሱስንና እሱ የሚመራን የሰማይ ሠራዊት ነው። በቅርቡ ብሔራትን እንዲሁም ክፋትን በሙሉ ያጠፋሉ።—ሕዝ. 9:2, 6, 7፤ ራእይ 19:11-21

እነዚህን ጠቃሚ ትምህርቶች መረዳታችን፣ ይሖዋ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር አብሮ እንደማያጠፋ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። (2 ጴጥ. 2:9፤ 3:9) በተጨማሪም በዘመናችን የሚካሄደውን የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ያስገነዝበናል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ሁሉም ሰው ማስጠንቀቂያውን መስማት ያስፈልገዋል!—ማቴ. 24:14

a እንደ ባሮክ (የኤርምያስ ጸሐፊ)፣ ኢትዮጵያዊው ኤቤድሜሌክና ሬካባውያን ያሉት ሰዎች በግምባራቸው ላይ በዓይን የሚታይ ምልክት ባይደረግላቸውም ከጥፋቱ ተርፈዋል። (ኤር. 35:1-19፤ 39:15-18፤ 45:1-5) በሕይወት ለመትረፍ የሚያስችል ምሳሌያዊ ምልክት ተደርጎባቸዋል።

b ታማኝ ቅቡዓን ከጥፋቱ ለመትረፍ ይህ ምልክት አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ከመሞታቸው በፊት አሊያም ታላቁ መከራ ከመፈንዳቱ ቀደም ብሎ የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል።—ራእይ 7:1, 3

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ