የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w18 ጥር ገጽ 7-11
  • ‘ለደከመው ኃይል ይሰጣል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ለደከመው ኃይል ይሰጣል’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል
  • በወንድሞቻችን ቅር ስንሰኝ
  • ቀደም ሲል በሠራናቸው ኃጢአቶች በጥፋተኝነት ስሜት ስንዋጥ
  • ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የሰው ልጅ ደካማነት የይሖዋን ኃይል አጉልቶ ያሳያል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • “ይሖዋንና እርሱ የሚሰጠውን ብርታት ፈልጉ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
w18 ጥር ገጽ 7-11
አንዲት እህት ከዶክተር ጋር ስትነጋገር፣ ሰብዓዊ ሥራ ስትሠራ፣ በዕድሜ የገፋ የቤተሰቧን አባል ስትንከባከብ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ

‘ለደከመው ኃይል ይሰጣል’

የ2018 የዓመት ጥቅስ፦ “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ . . . ኃይላቸው ይታደሳል።”—ኢሳ. 40:31

መዝሙሮች፦ 3, 47

የሚከተሉት ጥቅሶች የዓመቱን ጥቅስ ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችሉን እንዴት ነው?

  • ኢሳይያስ 40:26

  • ማቴዎስ 11:28-30

  • 2 ቆሮንቶስ 12:9, 10

1. በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሙናል? ይሖዋ በታማኝ አገልጋዮቹ እንዲደሰት የሚያደርገው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት መቼም ቢሆን ከመከራ ነፃ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። በከባድ በሽታ የሚሠቃዩ በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሉ። ሌሎች ደግሞ እነሱ ራሳቸው በዕድሜ ቢገፉም፣ አረጋውያን የሆኑ የቤተሰባቸውን አባላት የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር እንኳ ማሟላት ትግል ሆኖባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮች የተደራረቡባቸው ብዙ ወንድሞች አሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የሚያደርጉት ጥረት በገንዘብ ረገድ ከሚያስከትልባቸው ጫና ባሻገር ጊዜያቸውንና ኃይላቸውንም ያሟጥጥባቸዋል። ያም ሆኖ እነዚህ ወንድሞች አምላክ በገባው ቃል ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው፤ ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣም ጨርሶ አይጠራጠሩም። ይሖዋ ይህን መመልከቱ ምንኛ ያስደስተው ይሆን!

2. ኢሳይያስ 40:29 ምን ማበረታቻ ይሰጠናል? አንዳንዶች ምን ዓይነት ስህተት ይሠራሉ?

2 በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟችሁ ችግሮች ከአቅማችሁ በላይ እንደሆኑ የሚሰማችሁ ጊዜ አለ? ከሆነ እንዲህ የሚሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም። በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም አቅማቸው እንደተሟጠጠ የተናገሩበት ጊዜ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (1 ነገ. 19:4፤ ኢዮብ 7:7) ይሁንና ባጋጠማቸው ሁኔታ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ይሖዋን ብርታት እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል። እሱም ቢሆን አላሳፈራቸውም። አምላካችን “ለደከመው ኃይል . . . ይሰጣል።” (ኢሳ. 40:29) የሚያሳዝነው ግን በዘመናችን ያሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ጫና ሲደራረብባቸው ‘ትንሽ ፋታ እስኪያገኙ ድረስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማቆሙ’ የተሻለ እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማል፤ እንዲህ ያለው አመለካከት ግን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች በረከት ከማስገኘት ይልቅ ሸክም እንደሆኑ የመናገር ያህል ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ማንበብ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መካፈል ያቆማሉ፤ ሰይጣንም የሚፈልገው ይህንኑ ነው።

3. (ሀ) ሰይጣን እኛን ለማዳከም የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ዲያብሎስ፣ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ መጠመዳችን ብርታት እንደሚሰጠን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ አይፈልግም። እንግዲያው ኃይላችሁ እንደተሟጠጠና እንደዛላችሁ በሚሰማችሁ ጊዜ ከይሖዋ አትራቁ። እንዲያውም ይበልጥ ወደ እሱ ቅረቡ፤ እሱም “ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል።” (1 ጴጥ. 5:10፤ ያዕ. 4:8) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት እንድንቀንስ ሊያደርጉን የሚችሉ ሁለት ሁኔታዎችን እንመለከታለን፤ በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እናያለን። በመጀመሪያ ግን ኢሳይያስ 40:26-31⁠ን እንመርምር፤ ይህ ጥቅስ ይሖዋ እኛን ለማበርታት የሚያስችል ኃይል እንዳለው ይጠቁመናል።

ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው ይታደሳል

4. ከኢሳይያስ 40:26 ምን ትምህርት እናገኛለን?

4 ኢሳይያስ 40:26⁠ን አንብብ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ከዋክብት በሙሉ መቁጠር የቻለ ሰው የለም። የሳይንስ ሊቃውንት፣ ፍኖተ ሐሊብ በተባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ብቻ እስከ 400 ቢሊዮን የሚደርሱ ከዋክብት ሊገኙ እንደሚችሉ ይናገራሉ። የሚገርመው ይሖዋ ለእያንዳንዱ ኮከብ ስም ሰጥቶታል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ፣ ሕይወት የሌለውን እያንዳንዱን ፍጥረቱን በሚገባ የሚያውቀው ከሆነ በፍቅር ተነሳስተው ለሚያገለግሉት ሕዝቦቹማ የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጥ መገመት አያዳግትም! (መዝ. 19:1, 3, 14) አባታችን የእኛን ማንነት በሚገባ ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” ይላል። (ማቴ. 10:30) መዝሙራዊውም “ይሖዋ ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች የሕይወት ጎዳና ያውቃል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝ. 37:18) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችን የሚመለከት ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱን ፈተና ለመወጣት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።

5. ይሖዋ ብርታት ሊሰጠን እንደሚችል እርግጠኞች የሆንነው ለምንድን ነው?

5 ኢሳይያስ 40:28⁠ን አንብብ። ይሖዋ ገደብ የሌለው ኃይል ያለው አምላክ ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ፀሐይ ያላትን ኃይል እንመልከት። የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ የሆኑት ዴቪድ ቦዳኒስ እንደገለጹት ፀሐይ በእያንዳንዱ ሴኮንድ የምታመነጨው ኃይል፣ በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ የአቶሚክ ቦምቦች ፍንዳታ ጋር የሚመጣጠን ነው። ሌላ ተመራማሪ እንዳሰሉት ደግሞ ፀሐይ በአንድ ሴኮንድ ብቻ የምታመነጨው ኃይል፣ የዓለም ሕዝብ ለ200,000 ዓመታት የሚያስፈልገውን የኃይል መጠን ማሟላት ይችላል! ለፀሐይ ይህን ሁሉ ኃይል የሰጣት አምላክ፣ እኛም የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን ምንም ጥርጥር የለውም!

6. የኢየሱስ ቀንበር ልዝብ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

6 ኢሳይያስ 40:29⁠ን አንብብ። ይሖዋን ማገልገል ታላቅ ደስታ ያስገኛል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ . . . ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” ብሏቸዋል። (ማቴ. 11:28-30) ብዙዎቻችን የዚህን አባባል እውነተኝነት በሕይወታችን ተመልክተናል! አንዳንድ ጊዜ ወደ ጉባኤ ስብሰባ ለመሄድ ወይም በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ከቤታችን ስንወጣ በጣም ዝለን ሊሆን ይችላል። ወደ ቤታችን የምንመለሰው ግን መንፈሳችን ታድሶ እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል አግኝተን ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ቀንበር ልዝብ ነው!

7. በማቴዎስ 11:28-30 ላይ ያለውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

7 ኬላa የተባለች እህት ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም በተባለ ከፍተኛ ድካም የሚያስከትልና አቅም የሚያሳጣ ሕመም፣ በመንፈስ ጭንቀት እንዲሁም በጣም ኃይለኛ በሆነ ራስ ምታት ትሠቃያለች። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይከብዳታል። ይሁንና በአንድ ወቅት እንደምንም ብላ ወደ ስብሰባ በመሄድ የሕዝብ ንግግር ካዳመጠች በኋላ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ንግግሩ ስለ ተስፋ መቁረጥ የሚያወሳ ነበር። ተናጋሪው ንግግሩን ያቀረበው የሌሎችን ችግር እንደሚረዳና እንደሚያስብላቸው በሚያሳይ መንገድ ስለነበር አለቀስኩ። ይህ አጋጣሚ፣ ሁልጊዜ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዳለብኝ እንዳስታውስ አድርጎኛል።” ኬላ በስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥረት በማድረጓ በእጅጉ እንደተደሰተች ጥርጥር የለውም!

8, 9. ሐዋርያው ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

8 ኢሳይያስ 40:30⁠ን አንብብ። ምንም ዓይነት ችሎታ ቢኖረን በራሳችን ጥንካሬ ልናከናውን የምንችለው ነገር ውስን ነው። ይህ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ ሐቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይችል የነበረ ቢሆንም የሚፈልገውን ሁሉ እንዳያደርግ የሚያግዱት ነገሮች ነበሩ። ይህን ሁኔታ በተመለከተ ወደ አምላክ ሲጸልይ ያገኘው ምላሽ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው” የሚል ነበር። ጳውሎስ፣ ይሖዋ ምን ሊለው እንደፈለገ ገብቶታል። “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” በማለት የተናገረውም ለዚህ ነው። (2 ቆሮ. 12:7-10) ይሁንና ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

9 ጳውሎስ ከእሱ በላይ ኃይል ካለው አካል እርዳታ ካላገኘ በቀር ማከናወን የሚችለው ነገር ውስን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው በሚደክምበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ኃይል የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሊሰጠው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ በራሱ ጥንካሬ ፈጽሞ ሊያከናውን የማይችላቸውን ነገሮች እንዲያከናውን የአምላክ መንፈስ ኃይል ይሰጠዋል። ለእኛም እንዲሁ ሊያደርግልን ይችላል። በእርግጥም ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን ሲሰጠን ብርቱዎች መሆን እንችላለን!

10. ዳዊት ያጋጠሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንዲችል ይሖዋ የረዳው እንዴት ነው?

10 የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመዝሙራዊው ዳዊት በተደጋጋሚ ጊዜያት ኃይል ሰጥቶታል። “በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤ በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 18:29) ረጅም ቅጥር ወይም ግንብ ላይ “መውጣት” አዳጋች እንደሆነው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በራሳችን ጥንካሬ መቋቋም አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል።

11. መንፈስ ቅዱስ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት እንዴት እንደሚረዳን አብራራ።

11 ኢሳይያስ 40:31⁠ን አንብብ። ንስር ወደ ላይ የሚወጣውና በአየር ላይ እየተንሳፈፈ ረጅም ርቀት የሚጓዘው በራሱ ኃይል ብቻ አይደለም። ንስሩ ወደ ሰማይ ከፍ እያለ የሚወጣው፣ ሞቃት በሆነ አየር እየተገፋ ሲሆን እንዲህ ማድረጉም ጉልበቱን ለመቆጠብ ይረዳዋል። እናንተም ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ የምታስቡት ችግር ሲያጋጥማችሁ፣ ንስር ኃይል የሚያገኝበትን መንገድ አስታውሱ። ይሖዋ “ረዳት” በሆነው ‘በመንፈስ ቅዱስ’ አማካኝነት ተጨማሪ ኃይል እንዲሰጣችሁ ለምኑት። (ዮሐ. 14:26) ደስ የሚለው ነገር፣ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይህን ኃይል እንዲሰጠን መጠየቅ እንችላለን። በተለይ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር አለመግባባት በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋ የሚሰጠን ኃይል እንደሚያስፈልገን ይሰማን ይሆናል። ለመሆኑ እንዲህ ያሉ አለመግባባቶች የሚፈጠሩት ለምንድን ነው?

12, 13. (ሀ) በክርስቲያኖች መካከል አለመግባባቶች የሚፈጠሩት ለምንድን ነው? (ለ) የዮሴፍ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

12 በግለሰቦች መካከል አለመግባባት የሚፈጠረው ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን ነው። በዚህም የተነሳ የእምነት ባልንጀሮቻችን በሚናገሩት ወይም በሚያደርጉት ነገር ቅር የምንሰኝባቸው ጊዜያት አሉ፤ እነሱም ቢሆን በእኛ ይከፉ ይሆናል። ይህ ደግሞ ከባድ ፈተና ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደ ሌሎች ፈተናዎች ሁሉ ከወንድሞቻችን ጋር የሚፈጠር አለመግባባትም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጠናል፤ እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን ባይሆኑም ይሖዋ ይወዳቸዋል፤ እኛም ወንድሞቻችንን በመውደድና ከእነሱ ጋር ተስማምተን በመሥራት ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ማሳየት እንችላለን።

ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ

ይሖዋ ዮሴፍን አልተወውም፤ አንተንም ቢሆን አይተውህም (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13 ይሖዋ፣ በአገልጋዮቹ ላይ ፈተና እንዳይደርስ እንደማይከላከል ከዮሴፍ ታሪክ መመልከት እንችላለን። ዮሴፍ ወጣት እያለ ወንድሞቹ ስለቀኑበት ለባርነት ሸጡት፤ ከዚያም ወደ ግብፅ ተወሰደ። (ዘፍ. 37:28) ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንደተመለከተና ጻድቅ የሆነው ወዳጁ በደረሰበት በደል እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ዮሴፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳይደርስበት አልተከላከለም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዮሴፍ የጶጢፋርን ሚስት ለመድፈር ሞክሯል በሚል ተከስሶ እስር ቤት ተወረወረ፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን አምላክ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ አልወሰደም። ይህ ሲባል ግን አምላክ ዮሴፍን ትቶት ነበር ማለት ነው? በጭራሽ፤ እንዲያውም ዮሴፍ “የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ይሖዋ [ያሳካለት]” ነበር።—ዘፍ. 39:21-23

14. ‘ከቁጣ መቆጠብ’ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

14 ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። የአምላክ ወዳጅ የሆነው ዳዊት ብዙ ግፍ ደርሶበታል። ያም ሆኖ ምሬት ሕይወቱን እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። እንዲያውም “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤ ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ” ሲል ጽፏል። (መዝ. 37:8) ከቁጣ እንድንቆጠብ የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ምክንያት ይሖዋን ለመምሰል ያለን ፍላጎት ነው፤ እሱ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም።” (መዝ. 103:10) ‘ከቁጣ መቆጠብ’ የሚያስገኛቸው ጥቅሞችም አሉ። ቁጣ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም የመተንፈሻ አካላት ችግር ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም በጉበትና በቆሽት (ፓንክሪያስ) ላይ ጉዳት ሊያስከትል ብሎም በጨጓራ ሕመም እንድንሠቃይ ሊያደርገን ይችላል። በምንበሳጭበት ወቅት በትክክል ማሰብ ያቅተን ይሆናል። በቁጣ ገንፍለን የምንናገረው ነገር ወይም የምንወስደው እርምጃ ደግሞ ሌሎችን ይጎዳል፤ ይህም በመንፈስ ጭንቀት እንድንዋጥ ሊያደርገን ይችላል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። (ምሳሌ 14:30) ታዲያ ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከወንድማችን ጋር ሰላም መፍጠር የምንችለውስ እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር በተግባር በማዋል ነው።

በወንድሞቻችን ቅር ስንሰኝ

15, 16. አንድ ሰው ቅር ቢያሰኘን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 ኤፌሶን 4:26⁠ን አንብብ። በዓለም ያሉ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢናገሩን ወይም ቢያደርጉብን ብዙም አይገርመንም። ሆኖም የእምነት ባልንጀራችን ወይም የቤተሰባችን አባል እንዲህ ቢያደርግ ስሜታችን በጣም ሊጎዳ ይችላል። በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ችላ ብለን ማለፍ ቢከብደንስ? ለዓመታት ቂም ይዘን እንቆያለን? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ አለመግባባቶችን ሳንውል ሳናድር እንድንፈታ የሚሰጠውን ምክር እንከተላለን? ከወንድማችን ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ሳንፈታው በቆየን መጠን ሁኔታውን ማስተካከል ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነብን ይሄዳል።

16 በአንድ ወንድም ቅር ተሰኝተህ ሁኔታውን መርሳት ከበደህ እንበል። ከወንድምህ ጋር ሰላም ለመፍጠር ምን እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? በቅድሚያ፣ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርብ። ከወንድምህ ጋር በተረጋጋ መንፈስ ለመወያየት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ቅር ያሰኘህ ወንድም ከይሖዋ ወዳጆች አንዱ መሆኑን አትዘንጋ። (መዝ. 25:14) አምላክ ይህን ሰው ይወደዋል። ይሖዋ ለወዳጆቹ ደግነት የሚያሳይ ሲሆን እኛም እንዲሁ እንድናደርግ ይጠብቅብናል። (ምሳሌ 15:23፤ ማቴ. 7:12፤ ቆላ. 4:6) ልታደርገው የሚገባው ሌላው ነገር ደግሞ ወንድምህን ምን ብለህ እንደምታነጋግረው አስቀድመህ ማሰብ ነው። ወንድምህ ስሜትህን የጎዳው ሆን ብሎ እንደሆነ አድርገህ አታስብ፤ ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ተረድተኸው አሊያም ወንድምህ ሳያውቅ ቅር አሰኝቶህ ሊሆን ይችላል። አንተም ለተፈጠረው አለመግባባት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን አስተዋጽኦ አድርገህ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። ውይይቱን ለመጀመር “ምናልባት እኔ ሆደ ባሻ ሆኜ ሊሆን ይችላል፤ ትናንትና እንደዚያ ስትለኝ ግን . . . ተሰምቶኝ ነበር” ማለት ትችል ይሆናል። ውይይታችሁ ያሰብከውን ውጤት ካላስገኘ ከወንድምህ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚያስችልህ ሌላ አጋጣሚ ፈልግ። በተጨማሪም ወንድምህ የይሖዋ በረከት እንዳይለየው ጸልይ። በወንድምህ በጎ ባሕርያት ላይ ለማተኮር እንዲረዳህ አምላክን ለምነው። ያደረግከው ጥረት የሚያስገኘው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ ከወንድምህ ጋር ሰላም ለመፍጠር የምትችለውን ሁሉ ማድረግህ ይሖዋን እንደሚያስደስተው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

ቀደም ሲል በሠራናቸው ኃጢአቶች በጥፋተኝነት ስሜት ስንዋጥ

17. ይሖዋ ኃጢአት የፈጸመን ሰው ለመርዳት ምን ዝግጅት አድርጓል? ግለሰቡ በዚህ ዝግጅት መጠቀም ያለበትስ ለምንድን ነው?

17 አንዳንዶች ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። በመሆኑም የጥፋተኝነት ስሜት እንደ ጨካኝ ጌታ ሕይወታቸውን ይቆጣጠረዋል። በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ የነበረው ንጉሥ ዳዊት ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ዝም ባልኩ ጊዜ፣ ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሳ አጥንቶቼ መነመኑ። ቀንና ሌሊት እጅህ በእኔ ላይ ከብዳለችና።” ደስ የሚለው ግን ዳዊት፣ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ነገር አድርጓል። “በመጨረሻ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ . . . አንተም ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ” ሲል ጽፏል። (መዝ. 32:3-5) አንተም ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ ይሖዋ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ አቋምህ እንድትመለስ ሊረዳህ ይፈልጋል። ሆኖም በጉባኤው አማካኝነት ባደረገው ዝግጅት መጠቀም ይኖርብሃል። (ምሳሌ 24:16፤ ያዕ. 5:13-15) የዘላለም ሕይወት ማግኘትህ በዚህ ላይ የተመካ ነው፤ እንግዲያው እርምጃ ለመውሰድ አትዘግይ! ይሁንና ይሖዋ ኃጢአትህን ይቅር ካለልህ ከዓመታት በኋላም የጥፋተኝነት ስሜት የሚያሠቃይህ ቢሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

18. ይሖዋን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች ከጳውሎስ ታሪክ ምን መገንዘብ ይችላሉ?

18 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ቀደም ሲል በፈጸማቸው ስህተቶች ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሕሊናው ይወቅሰው ነበር። “እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ” ሲል ጽፏል። ይሁን እንጂ “አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:9, 10) ጳውሎስ ቀደም ሲል ስህተት የፈጸመ ቢሆንም ይሖዋ ተቀብሎታል፤ ደግሞም ሐዋርያው ይህን እንዲገነዘብ ይሖዋ ይፈልግ ነበር። አንተም ቀደም ሲል ለፈጸምከው ኃጢአት ከልብህ ንስሐ ከገባህ ብሎም እንደ አስፈላጊነቱ ሽማግሌዎችን ካነጋገርክ፣ ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግልህ መተማመን ትችላለህ። ይሖዋ ይቅር እንዳለህ አምነህ ተቀበል!—ኢሳ. 55:6, 7

19. የ2018 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ መመረጡ ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?

19 ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ በሄደ መጠን በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መጨመራቸው አይቀርም። ያም ቢሆን “ለደከመው ኃይል፣ ጉልበት ለሌላቸውም የተሟላ ብርታት” የሚሰጠው አምላክ፣ ለእኛም በጽናት ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ኃይል እንደሚሰጠን መተማመን እንችላለን። (ኢሳ. 40:29፤ መዝ. 55:22፤ 68:19) በ2018 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በተገኘን ቁጥር፣ በዚህ አስፈላጊ እውነት ላይ ለማሰላሰል አጋጣሚ እናገኛለን። ምክንያቱም “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ . . . ኃይላቸው ይታደሳል” የሚለውን የዓመቱን ጥቅስ በስብሰባ አዳራሾቻችን ውስጥ ሁልጊዜ እንመለከታለን።—ኢሳ. 40:31

a ስሟ ተቀይሯል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ