የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w18 ነሐሴ ገጽ 13-17
  • እጆቼ እንዳይዝሉ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እጆቼ እንዳይዝሉ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወላጆቼ እንዲሁም ወንድሞቼና እህቶቼ
  • የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመርኩበት መንገድ
  • ከተሞክሮ መማር
  • በኩዊቤክ ያደረግነው ትግል
  • ወንድሞችን በቋንቋቸው ማሠልጠን
  • በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተካሄደ ግንባታ
  • ቀናተኛ ከሆነች ክርስቲያን ጋር ትዳር መሠረትኩ
  • በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያከናወንነው ተጨማሪ ሥራ
  • በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት አርኪ ሕይወት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በመላው ሕይወታችን ከታላቁ አስተማሪያችን ያገኘናቸው ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ሰዎች መማሬ ብዙ በረከት አስገኝቶልኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
w18 ነሐሴ ገጽ 13-17

የሕይወት ታሪክ

እጆቼ እንዳይዝሉ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ

ማክሲም ዳኒሌኮ እንደተናገሩት

“አባባ፣” “ፓፓ፣” “አጎቴ።” በቤቴል ያሉ ወጣቶች በአብዛኛው የሚጠሩኝ በዚህ መንገድ ነው። እኔም የ89 ዓመት አረጋዊ እንደመሆኔ መጠን እንዲህ ብለው ሲጠሩኝ ደስ ይለኛል። በዚህ መንገድ በፍቅር መጠራቴ፣ ለ72 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈሌ ከይሖዋ ያገኘሁት ወሮታ እንደሆነ ይሰማኛል። ደግሞም አምላክን በማገልገል ካለኝ ተሞክሮ በመነሳት፣ እነዚህን ወጣቶች ‘እጆቻችሁ ካልዛሉ የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’ ብዬ በእርግጠኝነት ማበረታታት እችላለሁ።—2 ዜና 15:7 ግርጌ

ወላጆቼ እንዲሁም ወንድሞቼና እህቶቼ

ማክሲም ዳኒሌኮ

ወላጆቼ የዩክሬን ተወላጆች ሲሆኑ ወደ ካናዳ ፈልሰው ነበር። ካናዳ ከደረሱ በኋላ በማንቶባ ግዛት በምትገኘው በራስበርን ከተማ ኑሯቸውን መሠረቱ። አፍቃሪ የሆነችው እናቴ 8 ወንዶችና 8 ሴቶች ልጆች የወለደች ሲሆን እኔ 14ኛ ልጅ ነበርኩ፤ ከመካከላችን መንትያ ያለው የለም። አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚወድ ሁልጊዜ እሁድ ማለዳ ላይ ያነብልን ነበር። ይሁን እንጂ ሃይማኖት ገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ እንደሆነ ይሰማው ነበር፤ ብዙ ጊዜ በቀልድ መልክ “ኢየሱስ ሲሰብክና ሲያስተምር ገንዘብ የከፈለ አለ?” ይል ነበር።

ከወንድሞቼና ከእህቶቼ መካከል ስምንቱ ማለትም አራት ወንድሞቼና አራት እህቶቼ ውሎ አድሮ እውነትን ተቀብለዋል። ሮዝ የተባለችው እህቴ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ በአቅኚነት አገልግላለች። ከመሞቷ በፊት፣ የምታገኘውን ሰው ሁሉ በአምላክ ቃል ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ታበረታታ ነበር፤ “በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንድንገናኝ እፈልጋለሁ” ትል ነበር። ታላቅ ወንድሜ ቴድ ደግሞ ቀደም ሲል ስለ ገሃነመ እሳት በግለት ይሰብክ ነበር። በየሳምንቱ እሁድ ጠዋት በሬዲዮ የሚሰብክ ሲሆን ኃጢአተኞች በማይጠፋ እሳት ለዘላለም እንደሚቃጠሉ በመናገር አድማጮቹን ያስጨንቃቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ታማኝና ቀናተኛ የይሖዋ አገልጋይ ሆኗል።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመርኩበት መንገድ

ሰኔ 1944 አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ በምግብ ጠረጴዛችን ላይ ዘ ካሚንግ ዎርልድ ሪጀነሬሽን​a የሚል ርዕስ ያለው ቡክሌት አገኘሁ። የመጀመሪያውን ገጽ ቀጥሎም ሁለተኛውን ካነበብኩ በኋላ ማቆም ስላልቻልኩ ሙሉውን ቡክሌት አንብቤ ጨረስኩ። ከዚያም እንደ ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ።

ቡክሌቱን ጠረጴዛችን ላይ ያስቀመጠው ማን ነው? ታላቅ ወንድሜ ስቲቭ፣ መጻሕፍትና ቡክሌቶች “የሚሸጡ” ሁለት ሰዎች ቤታችን መጥተው እንደነበረ ነገረኝ። “ዋጋው አምስት ሳንቲም ብቻ ስለሆነ ይህን ገዛሁት” አለ። ሰዎቹ በቀጣዩ እሁድ ተመልሰው መጡ። እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑና ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ እንደሚሰጡ ነገሩን። ወላጆቻችን ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲኖረን አድርገው ስላሳደጉን እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የተናገሩት ነገር አስደሰተን። በተጨማሪም ሁለቱ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዊነፔግ ከተማ በቅርቡ ትልቅ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ነገሩን፤ እህቴ ኤልሲ የምትኖረው እዚያ ነበር። እኔም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ወሰንኩ።

ብስክሌቴን እየነዳሁ 320 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ያለውን መንገድ ተጉዤ ወደ ዊነፔግ ሄድኩ፤ እግረ መንገዴን ግን ቤታችን መጥተው የነበሩት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚኖሩባት ኬልውድ የምትባል ከተማ ጎራ አልኩ። በኬልውድ በጉባኤ ስብሰባ ላይ የተገኘሁ ሲሆን ጉባኤ የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ ያወቅሁት ያን ጊዜ ነው። ከዚህም ሌላ ወንድ ሴት፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ሰው እንደ ኢየሱስ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ማስተማር እንዳለበት ተገነዘብኩ።

ዊነፔግ ስደርስ፣ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከሰሜናዊ ኦንታሪዮ ከመጣው ከታላቅ ወንድሜ ከጃክ ጋር ተገናኘን። በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን አንድ ወንድም ጥምቀት እንደሚኖር ማስታወቂያ ተናገረ። እኔና ጃክ በዚያ ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ወሰንን። ሁለታችንም ከተጠመቅን በኋላ ወዲያውኑ አቅኚ ለመሆን ቆርጠን ነበር። ጃክ ስብሰባው እንዳለቀ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። እኔ ግን ገና 16 ዓመቴ ስለነበር ትምህርቴን መጨረስ ነበረብኝ፤ ሆኖም በቀጣዩ ዓመት እኔም የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።

ከተሞክሮ መማር

በማንቶባ ግዛት በምትገኝ ሱሪ የምትባል ከተማ ስታን ኒኮልሰን ከሚባል ወንድም ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። በአቅኚነት አገልግሎት ነገሮች ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ እንዳልሆኑ የተገነዘብኩት ብዙም ሳልቆይ ነበር። ገንዘባችን እያለቀ መሆኑን ብንመለከትም መስበካችንን ቀጠልን። አንድ ቀን ስንሰብክ ውለን ወደ ቤት ስንመለስ በጣም ርቦን ነበር፤ በኪሳችን ውስጥ ደግሞ ቤሳ ቤስቲን አልነበረም። ቤታችን ስንደርስ ግን በራችን ላይ አንድ ትልቅ ጆንያ ሙሉ ቀለብ አገኘን! ያንን ጆንያ ማን እንዳመጣልን እስከ ዛሬም ድረስ አናውቅም። የዚያን ዕለት ማታ የበላነው እንደ ነገሥታት ነበር። ይህ እጃችን ባለመዛሉ ያገኘነው ወሮታ እንደሆነ ተሰምቶናል! እንዲያውም በዚያ ወር ወፈር ብዬ ነበር።

ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ከሶሪስ በስተ ሰሜን 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በጊልበርት ፕሌንስ ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ጉባኤ፣ የጉባኤውን ወርሃዊ የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ትልቅ ሠንጠረዥ መድረኩ ላይ ይለጥፍ ነበር። በአንደኛው ወር ላይ የጉባኤው የአገልግሎት እንቅስቃሴ ዝቅ ስላለ፣ ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ንግግር ሰጠሁ። ከስብሰባው በኋላ፣ የማያምን ባል ያላት አንዲት አረጋዊት አቅኚ ወደ እኔ መጣችና ዓይኖቿ እንባ አቅርረው “የቻልኩትን ያህል ጥረት አድርጌ ነበር፤ ግን ከዚህ የበለጠ መሥራት አልቻልኩም” አለችኝ። ይህን ስትለኝ እኔም በተራዬ አለቀስኩ፤ ከዚያም ይቅርታ ጠየቅኳት።

ቀናተኛ የሆኑ ወጣት ወንድሞች ልክ እንደ እኔ ዓይነት ስህተት ይሠሩ ይሆናል፤ ይህም ተስፋ ሊያስቆርጣቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ከተሞክሮ እንደተማርኩት፣ በመሳሳታቸው ምክንያት እጃቸው እንዲዝል ከመፍቀድ ይልቅ ከስህተታቸው ተምረው ወደፊት መጓዛቸው የተሻለ ነው። በታማኝነት እያገለገሉ መቀጠል ወሮታ ያስገኛል።

በኩዊቤክ ያደረግነው ትግል

በ21 ዓመቴ በጊልያድ ትምህርት ቤት 14ኛው ክፍል መማር መቻሌን እንደ ታላቅ መብት እቆጥረዋለሁ! የተመረቅነው የካቲት 1950 ሲሆን ከተማሪዎቹ መካከል አንድ አራተኛ የምንሆነው ካናዳ ውስጥ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ወዳሉባት ወደ ኩዊቤክ ተላክን፤ በወቅቱ በኩዊቤክ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ስደት ይደርስ ነበር። እኔ የተመደብኩት የወርቅ ማዕድን በሚወጣባት በቫልዶር ከተማ ነው። አንድ ቀን በአቅራቢያዋ በምትገኘው በቫል-ሴንቪል መንደር በቡድን ሆነን ለመስበክ ሄድን። የአካባቢው ቄስ መንደሯን ወዲያውኑ ለቀን ካልሄድን ሕዝቡን እንደሚያስነሳብን ዛተ። እንዲህ ያለ ዛቻ በመሰንዘሩ ፍርድ ቤት ከሰስኩት። ቄሱም ቅጣት ተጣለበት።b

እንደዚህ ያሉ በርካታ ክስተቶች በኩዊቤክ ያደረግነውን ትግል ያሳያሉ። ኩዊቤክ ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ሥር ቆይታለች። በመሆኑም ቀሳውስቱና ፖለቲካዊ አጋሮቻቸው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ያደርሱ ነበር። ጊዜው በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ ቁጥራችን ጥቂት ነበር፤ ይሁን እንጂ በዚህ የተነሳ እጃችን እንዲዝል አልፈቀድንም። ቅን ልብ ያላቸው የኩዊቤክ ነዋሪዎች ቀና ምላሽ ሰጥተዋል። ብዙ ሰዎችን ያስጠናሁ ሲሆን እነሱም እውነትን ተቀብለዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ መካከል አሥር አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ይገኝበት ነበር። ከጊዜ በኋላ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ይሖዋን ማገልገል ጀምረዋል። ይህ ቤተሰብ ያሳየው ድፍረት ሌሎችም ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ጥሩ ምሳሌ ሆኗቸዋል። እኛም መስበካችንን የቀጠልን ሲሆን ውሎ አድሮም በትግሉ አሸንፈናል!

ወንድሞችን በቋንቋቸው ማሠልጠን

በ1956 በሄይቲ እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ ከተመደቡት አዳዲስ ሚስዮናውያን አብዛኞቹ ፈረንሳይኛ መናገር ቢያታግላቸውም ሕዝቡ መልእክታችንን ይሰማ ነበር። ስታንሊ ቦገስ የተባለው ሚስዮናዊ “ሕዝቡ፣ ሐሳባችንን መግለጽ እንድንችል እኛን ለመርዳት ምን ያህል እንደሚጥር ማየታችን አስገርሞናል” በማለት ተናግሮ ነበር። እኔ ኩዊቤክ ውስጥ ፈረንሳይኛ መማሬ መጀመሪያ ላይ ጠቅሞኝ ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የአካባቢው ወንድሞች የሚናገሩት ሄይቲኛ ክሪኦል ብቻ እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብን። በመሆኑም በሄይቲ የተመደብነው ሚስዮናውያን ውጤታማ መሆን ከፈለግን የአካባቢውን ቋንቋ መማር ነበረብን። በመሆኑም ቋንቋውን የተማርን ሲሆን ጥረታችንም ተክሷል።

ወንድሞችን የበለጠ ለመርዳት ሲባል መጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች ጽሑፎችን ወደ ሄይቲኛ ክሪኦል እንድንተረጉም ከበላይ አካሉ ፈቃድ አገኘን። ከዚያ በኋላ በመላ አገሪቱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኘው ሰው ቁጥር በፍጥነት ጨመረ። በ1950 ሄይቲ ውስጥ 99 አስፋፊዎች ነበሩ፤ በ1960 ግን የአስፋፊዎቹ ቁጥር ከ800 በላይ ሆኖ ነበር! በዚያ ወቅት በቤቴል እንዳገለግል ተመደብኩ። በ1961 ደግሞ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የማስተማር መብት አግኝቼ ነበር። ለ40 የጉባኤ ሽማግሌዎችና ልዩ አቅኚዎች ሥልጠና መስጠት ችለን ነበር። ጥር 1962 በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ፣ ብቃት ያላቸውን የአካባቢው ወንድሞች አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ አበረታታናቸው፤ አንዳንዶቹም ልዩ አቅኚ ሆነው ተመደቡ። በዚያ ወቅት እንዲህ መደረጉ ጠቃሚ እንደነበር በኋላ ተገንዝበናል፤ ምክንያቱም ከፊታችን ተቃውሞ ይጠብቀን ነበር።

ስብሰባው ካለቀ ብዙም ሳይቆይ ይኸውም ጥር 23, 1962 እኔና አንድሩ ዳሚኮ የተባለው ሚስዮናዊ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ እያለን ተይዘን ታሰርን፤ በተጨማሪም የጥር 8, 1962 ንቁ! (ፈረንሳይኛ) ተወረሰ። ንቁ! መጽሔት ሄይቲ ውስጥ ቩዱ የሚባለው ጥንቆላ እንደሚካሄድ የፈረንሳይኛ ጋዜጦች የዘገቡትን ሐሳብ ጠቅሶ ነበር። አንዳንዶች ይህንን ሐሳብ አልወደዱትም፤ ርዕሱን በሄይቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንደጻፍነው ተሰምቷቸው ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዚያ የምናገለግል ሚስዮናውያን በሙሉ ከአገር እንድንወጣ ተደረገ።c ይሁን እንጂ ሥልጠና ያገኙት የአካባቢው ወንድሞች ሥራውን ተረክበው በአስደናቂ ሁኔታ ቀጠሉ። በዛሬው ጊዜ፣ እነዚያ ወንድሞች ባሳዩት ጽናትና ባደረጉት መንፈሳዊ እድገት እኔም እደሰታለሁ። በአሁኑ ጊዜ በሄይቲኛ ክሪኦል አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሟል፤ ይህ በዚያ ጊዜ ሕልም መስሎ ይታየን የነበረ ነገር ነው።

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተካሄደ ግንባታ

ከሄይቲ በኋላ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ በሚስዮናዊነት እንዳገለግል ተመደብኩ። በኋላ ላይ በዚያ አገር በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ከዚያም በቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካችነት የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

በዚያ ወቅት ብዙዎቹ የስብሰባ አዳራሾች ያን ያህል ማራኪ አልነበሩም። እኔም ሣር ሰብስቤ በማምጣት የሣር ክዳን ጣሪያ መሥራት ተማርኩ። አላፊ አግዳሚው ይህን ሥራ ለመልመድ ስታገል በማየት በጣም ይገረም ነበር። በተጨማሪም ወንድሞች ይህን ማየታቸው የራሳቸውን የስብሰባ አዳራሾች በመገንባቱና በመንከባከቡ ሥራ ይበልጥ እንዲካፈሉ አበረታቷቸዋል። የሃይማኖት መሪዎቹ የእነሱ አብያተ ክርስቲያናት የቆርቆሮ ክዳን፣ የእኛ አዳራሽ ግን የሣር ክዳን በመሆኑ ያሾፉብን ነበር። እኛም በዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ በቀላል መንገድ የሚሠሩትን ባለ ሣር ክዳን የስብሰባ አዳራሾቻችንን መገንባታችንን ቀጠልን። ዋና ከተማዋን ባንጊን ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ሲመታት ግን የሃይማኖት መሪዎቹ በእኛ ላይ ማፌዛቸውን አቆሙ። አውሎ ነፋሱ የአንድን ቤተ ክርስቲያን የቆርቆሮ ክዳን ገንጥሎ በአውራ ጎዳናው ላይ ጣለው። የእኛ የስብሰባ አዳራሾች የሣር ክዳን ግን ምንም አልሆነም። ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዘው ሥራ በተሻለ መንገድ አመራር ለመስጠት እንዲያመች ሲባል በአምስት ወራት ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮና የሚስዮናውያን ቤት ገነባን።d

ቀናተኛ ከሆነች ክርስቲያን ጋር ትዳር መሠረትኩ

ማክሲምና ሃፒ ዳኒሌኮ በሠርጋቸው ዕለት

በሠርጋችን ዕለት

በ1976 በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ሥራችን ታገደ፤ እኔም የአጎራባቿ አገር የቻድ ዋና ከተማ በሆነችው በንጃሚና ተመደብኩ። በዚያ መመደቤ በጎ ጎን ነበረው፤ ምክንያቱም ሃፒ ከምትባል ቀናተኛ ልዩ አቅኚ ጋር ተዋወቅሁ። ሃፒ የመጣችው ከካሜሩን ሲሆን ሚያዝያ 1, 1978 ተጋባን። በዚያው ወር የእርስ በርስ ጦርነት ስለፈነዳ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች እኛም ወደ አገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ሸሸን። ውጊያው አብቅቶ ስንመለስ ቤታችን የአንድ ታጣቂ ቡድን ጠቅላይ መምሪያ ሆኖ አገኘነው። ጽሑፎቻችን ብቻ ሳይሆኑ የሃፒ የሠርግ ልብስና ለሠርጋችን የተሰጡን ስጦታዎች ጭምር ተወስደው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት እጃችን እንዲዝል አልፈቀድንም። ሁለታችንም በሕይወት መኖራችን ትልቅ ነገር ነው፤ ሥራችንን ለመቀጠልም ዝግጁ ነበርን።

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ በሥራችን ላይ የተጣለው እገዳ ተነሳ። እኛም ወደዚያ የተመለስን ሲሆን ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። የምንኖረው በመኪናችን ውስጥ ሲሆን አንድ ታጣፊ አልጋ፣ 200 ሊትር ውኃ የሚይዝ በርሜል፣ በጋዝ የሚሠራ ማቀዝቀዣ እና የጋዝ ምድጃ ነበረን። በወቅቱ ከቦታ ቦታ መጓዝ አስቸጋሪ ነበር። እንዲያውም በአንድ ጉዞ ላይ ፖሊሶች በ117 የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ አስቁመውናል።

የሙቀቱ መጠን ብዙውን ጊዜ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለጥምቀት በቂ ውኃ ማግኘት አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ነበር። በመሆኑም ወንድሞች የደረቁ ወንዞችን ቆፍረው ከዚያ የሚፈልቀውን ውኃ በመቅዳት ለጥምቀት የሚበቃ ውኃ ያጠራቅማሉ፤ ብዙውን ጊዜ ጥምቀት የሚካሄደው በበርሜል ውስጥ ነበር።

በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያከናወንነው ተጨማሪ ሥራ

በ1980 ወደ ናይጄርያ ተዛወርን። እዚያም አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመገንባት በሚደረገው ዝግጅት ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል እገዛ አበርክተናል። ወንድሞች ባለ አንድ ፎቅ መጋዘን ገዝተው ነበር፤ መጋዘኑ ከተነቃቀለ በኋላ እኛ ለግንባታ ያዘጋጀነው ቦታ ላይ እንደ አዲስ እንዲገጣጠም ታስቦ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት መጋዘኑን በመነቃቀሉ ሥራ ላይ እገዛ ለማድረግ ፎቁ ላይ ወጣሁ። እኩለ ቀን አካባቢ በዚያው በወጣሁበት መንገድ ወደ ታች መውረድ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ በሥራው ሂደት የተለዋወጡ ነገሮች ስለነበሩ ለመውረድ ስሞክር ተንሸራትቼ ከፎቁ ላይ ወደቅሁ። ሁኔታዬ በጣም አሳሳቢ ቢመስልም ራጅ ከተነሳሁና ምርመራ ከተደረገልኝ በኋላ ሐኪሙ ሃፒን “አይዞሽ። ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ደህና ይሆናል” አላት።

ማክሲምና ሃፒ ዳኒሌኮ ወደ ትልቅ ስብሰባ ሲሄዱ

“በሕዝብ መጓጓዣ” ተጠቅመን ወደ ትልቅ ስብሰባ ስንሄድ

በ1986 ወደ ኮት ዲቩዋር ተዛወርንና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ሥራችን አጎራባቿ ቡርኪና ፋሶን መጎብኘትንም ይጨምር ነበር። ከዓመታት በኋላ በቡርኪና ፋሶ እንደምንመደብ በዚያን ጊዜ ጨርሶ አላሰብኩም ነበር።

ማክሲም ዳኒሌኮ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እያሉ ይኖሩበት ከነበረው መኪና አጠገብ ተቀምጠው

ተጓዥ የበላይ ተመልካች እያለሁ የምንኖረው መኪና ውስጥ ነበር

ከካናዳ የወጣሁት በ1956 ነበር፤ ከ47 ዓመታት በኋላ በ2003 ከሃፒ ጋር በካናዳ ወዳለው ቤቴል ተመለስኩ። የካናዳ ዜግነት ቢኖረንም እኛ ግን የሚሰማን አፍሪካውያን እንደሆንን ነው።

ማክሲም ዳኒሌኮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ

ቡርኪና ፋሶ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስመራ

ከዚያም በ2007 በ79 ዓመት ዕድሜዬ እንደገና ወደ አፍሪካ ተመለስን! የተመደብነው በቡርኪና ፋሶ ሲሆን በዚያ ያለው የአገር ኮሚቴ አባል ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ በቡርኪና ፋሶ ያለው ቢሮ በቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ሆኖ የሚሠራ የርቀት ትርጉም ቢሮ ሆነ፤ እኛም ነሐሴ 2013 በቤኒን ቤቴል እንድናገለግል ተመደብን።

ማክሲምና ሃፒ ዳኒሌኮ በቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ

ከሃፒ ጋር በቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ሳለን

አቅሜ ውስን ቢሆንም አገልግሎት በጣም ያስደስተኛል። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ዠድዮንና ፍሬዠስ የተባሉ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ሲጠመቁ በማየቴ ተደስቻለሁ፤ እርግጥ ይህን ማድረግ የቻልኩት ሽማግሌዎች በደግነት ያደረጉልኝ እርዳታና የባለቤቴ ፍቅራዊ ድጋፍ ስላልተለየኝ ነው። ዠድዮንና ፍሬዠስ በአሁኑ ወቅት ይሖዋን በቅንዓት ያገለግላሉ።

ከጊዜ በኋላ እኔና ባለቤቴ በደቡብ አፍሪካ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የተዛወርን ሲሆን በዚያም የቤቴል ቤተሰብ አባላት ከጤናዬ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገኝን እንክብካቤ በደግነት ያደርጉልኛል። ደቡብ አፍሪካ፣ በአፍሪካ ውስጥ የማገልገል መብት ካገኘሁባቸው አገሮች ሰባተኛዋ ናት። ጥቅምት 2017 ደግሞ ሌላ አስደናቂ መብት አገኘን። በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ የሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት የውሰና ፕሮግራም ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። ይህ ፈጽሞ የማንረሳው ክንውን ነው!

የ1994 የዓመት መጽሐፍ በገጽ 255 ላይ “በሥራው ላይ ለብዙ ዓመታት ለጸናችሁ ሁሉ ‘የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጆቻችሁ አይዛሉ’ ብለን እናበረታታችኋለን።—2 ዜና 15:7” የሚል ሐሳብ ይዟል። እኔና ሃፒ ይህን ማበረታቻ በተግባር ለማዋልና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።

a በ1944 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን መታተም አቁሟል።

b በኅዳር 8, 1953 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-5 ላይ የወጣውን “የኩዊቤክ ቄስ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተፈረደበት” የሚል ርዕስ ተመልከት።

c በ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 148-150 ላይ ሙሉውን ታሪክ ማግኘት ይቻላል።

d በግንቦት 8, 1966 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 27 ላይ የወጣውን “በጠንካራ መሠረት ላይ መገንባት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ