የሕይወት ታሪክ
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት አርኪ ሕይወት
ጊዜው 1951 ነው። የካናዳ ግዛት በሆነችው በኩዊቤክ ወደምትገኘው ሩወን የተባለች አነስተኛ ከተማ ገና መድረሴ ነው። በተሰጠኝ አድራሻ መሠረት አንድ በር አንኳኳሁ። በጊልያድ የሠለጠነ ሚስዮናዊ የሆነው ማርሴል ፊልቶa በሩን ከፈተልኝ። እሱ 23 ዓመቱ ሲሆን ቁመቱ ረጅም ነው፤ እኔ ደግሞ 16 ዓመቴ ሲሆን ቁመቴም አጭር ነው። የአቅኚነት ምድቤን የሚገልጸውን ደብዳቤ አሳየሁት። እሱም ደብዳቤውን ካነበበው በኋላ አየት አደረገኝና “እዚህ መሆንህን እናትህ ታውቃለች?” አለኝ።
የልጅነት ሕይወቴ
የተወለድኩት በ1934 ነው። ወላጆቼ ከስዊዘርላንድ መጥተው በኦንታሪዮ፣ ካናዳ በምትገኘው ቲሚንስ የተባለች ማዕድን የሚወጣባት ከተማ መኖር ጀምረው ነበር። በ1939 ገደማ እናቴ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ማንበብና በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች። እኔንም ሆነ ስድስት ወንድሞቼንና እህቶቼንም ይዛን ትሄድ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።
አባቴ በውሳኔዋ ደስተኛ አልነበረም። ሆኖም እናቴ እውነትን ስለምትወድ በታማኝነት ለመጽናት ቆርጣ ነበር። በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ካናዳ ውስጥ በታገደበት ወቅትም በታማኝነት ጸንታለች። በተጨማሪም አባቴ በኃይለ ቃል ቢያናግራትም እንኳ ምንጊዜም ደግነትና አክብሮት ታሳየው ነበር። የእሷ ግሩም ምሳሌነት እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ እውነትን እንድንቀበል ረድቶናል። ደስ የሚለው፣ አባቴ በጊዜ ሂደት አመለካከቱን በማስተካከል ቤተሰባችንን በደግነት መያዝ ጀመረ።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ
ነሐሴ 1950 በኒው ዮርክ ሲቲ በተካሄደው “የቲኦክራሲው እድገት” የተሰኘ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ከተለያዩ አገሮች የመጡ ወንድሞችንና እህቶችን ካገኘሁ እንዲሁም ከጊልያድ ተመራቂዎች ጋር የተደረጉትን አስደሳች ቃለ መጠይቆች ካዳመጥኩ በኋላ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ለማድረግ ተነሳሳሁ። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ቆረጥኩ። ልክ ወደ ቤቴ እንደተመለስኩ የዘወትር አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። ከዚያም ከካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ በመጀመሪያ መጠመቅ እንዳለብኝ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። እኔም ጥቅምት 1, 1950 ተጠመቅኩ። ከአንድ ወር በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። የመጀመሪያ የአገልግሎት ምድቤ ካፐስኬሲንግ ነበር። ይህ ከተማ የሚገኘው በወቅቱ ከምኖርበት ከተማ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ነበር።
ኩዊቤክ ውስጥ ሳገለግል
በ1951 የጸደይ ወቅት ላይ ቅርንጫፍ ቢሮው፣ ፈረንሳይኛ መናገር የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረንሳይኛ ወደሚነገርበት ወደ ኩዊቤክ ግዛት እንዲዛወሩ ግብዣ አቀረበ። እዚያ ተጨማሪ ሰባኪዎች ያስፈልጉ ነበር። እኔም ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ መናገር ስለምችል ግብዣውን ተቀበልኩ። ከዚያም በሩወን እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ ማንም የማውቀው ሰው አልነበረም። በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት የተሰጠኝ አንድ አድራሻ ብቻ ነበር። ሆኖም ሁሉም ነገር ተሳካ። እኔና ማርሴል ጥሩ ጓደኛሞች ሆንን። ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ኩዊቤክ ውስጥ በደስታ አገለገልኩ። እንዲሁም ልዩ አቅኚ ሆንኩ።
ጊልያድ እና የዘገዩ ተስፋዎች
ኩዊቤክ እያለሁ በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በሚካሄደው የጊልያድ ትምህርት ቤት 26ኛ ክፍል እንድማር ስጋበዝ በጣም ተደሰትኩ። የካቲት 12, 1956 ተመረቅን። ከዚያም በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በአሁኗ ጋናb እንዳገለግል ተመደብኩ። ሆኖም እዚያ መሄድ እንድችል የጉዞ ሰነዶቼ እስኪሟሉ ድረስ ወደ ካናዳ ተመልሼ “ለተወሰኑ ሳምንታት” መጠበቅ ነበረብኝ።
ሆኖም ሂደቱ ሰባት ወር ስለፈጀ በቶሮንቶ ከጠበቅኩት በላይ መቆየት አስፈልጎኛል። በዚያ ወቅት የወንድም ክሪፕስ ቤተሰቦች በደግነት አስተናገዱኝ። እዚያ እያለሁ ከልጃቸው ከሺላ ጋር ተዋወቅኩ። ከእሷ ጋር ተዋደድን። እንድታገባኝ ልጠይቃት እያሰብኩ ሳለሁ ቪዛ አገኘሁ። እኔና ሺላ ስለ ጉዳዩ ከጸለይን በኋላ ወደ ምድቤ ብሄድ የተሻለ እንደሆነ ወሰንን። ሆኖም መጻጻፋችንን በመቀጠል ወደፊት መጋባት እንችል እንደሆነ ለማየት ተነጋገርን። ይህን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ሆኖም በኋላ ላይ እንደተገነዘብነው ትክክለኛ ውሳኔ ነበር።
በባቡር፣ በዕቃ መጫኛ መርከብና በአውሮፕላን ተሳፍሬ ለአንድ ወር ያህል ከተጓዝኩ በኋላ አክራ፣ ጋና ደረስኩ። እዚያም የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ምድቤ በመላዋ ጋና እንዲሁም አጎራባች ወደሆኑት ወደ አይቮሪ ኮስት (የአሁኗ ኮት ዲቩዋር) እና ወደ ቶጎላንድ (የአሁኗ ቶጎ) መጓዝን ይጠይቅ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የምጓዘው፣ የቅርንጫፍ ቢሮው ንብረት በሆነ ጂፕ መኪና ብቻዬን ነበር። የጉብኝት ሥራዬን በጣም እወደው ነበር።
ቅዳሜና እሁድ በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ሥራ ይኖረኛል። በወቅቱ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ አልነበረንም። በመሆኑም ወንድሞች የቀርከሃ እንጨትና የዘንባባ ዝንጣፊ ተጠቅመው ከኃይለኛው ፀሐይ ጊዜያዊ መጠለያ ይሠሩ ነበር። ካፊቴሪያው ውስጥ ፍሪጅ ስላልነበር ወንድሞች ከብቶችን ወደ ስብሰባ ቦታው ካመጡ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ አርደው ለተሰብሳቢዎቹ ምግብ ያዘጋጁ ነበር።
በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አንዳንድ አስቂኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። በአንድ ወቅት፣ ሚስዮናዊ የሆነው ወንድም ኸርብ ጄኒንዝc ንግግር እያቀረበ ሳለ አንድ ወይፈን ከካፊቴሪያው አምልጦ ወጣ። ወይፈኑ በመድረኩና በተሰብሳቢዎቹ መካከል ይሯሯጥ ጀመር። ወንድም ኸርብ ንግግር ማቅረቡን አቆመ። ወይፈኑም ደንብሮ ነበር። ሆኖም አራት ጠንካራ ወንድሞች ወይፈኑን ይዘው ወደ ካፊቴሪያው መለሱት። በዚህ ጊዜ ተሰብሳቢዎቹ አጨበጨቡ።
በሳምንቱ መሃል ባሉት ቀናት ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የተባለውን ፊልም በአቅራቢያ ባሉ መንደሮች አሳይ ነበር። ቪዲዮውን የማሳየው በሁለት ምሰሶዎች ወይም በሁለት ዛፎች ላይ ነጭ ሸራ ወጥሬ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች በጣም ይወዱት ነበር! ብዙዎቹ በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ፊልም ያዩት ያኔ ነው። ሰዎች ሲጠመቁ የሚያሳዩትን ትዕይንቶች ሲመለከቱ በደስታ ያጨበጭቡ ነበር። ፊልሙ አንድነት ያለን ዓለም አቀፋዊ ድርጅት እንደሆንን ብዙዎች እንዲገነዘቡ ረድቷል።
በ1959 ጋና ውስጥ ተጋባን
አፍሪካ ውስጥ ለሁለት ዓመት ገደማ ካገለገልኩ በኋላ በ1958 ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መገኘት በመቻሌ በጣም ተደሰትኩ። በወቅቱ ኩዊቤክ ውስጥ በልዩ አቅኚነት ታገለግል የነበረችው ሺላም ወደ ስብሰባው መጥታ ነበር። ሳገኛት በጣም ተደሰትኩ። እስከዚያ ድረስ ደብዳቤ እንጻጻፍ ነበር። ሆኖም በአካል ሳገኛት እንድታገባኝ ጠየቅኳት። እሷም ጥያቄዬን ተቀበለች። ለወንድም ኖርd ደብዳቤ በመጻፍ ሺላ ጊልያድ ተምራ አብራኝ በአፍሪካ ማገልገል ትችል እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም በሐሳቤ ተስማማ። በስተ መጨረሻ ሺላ ጋና መጣች። ጥቅምት 3, 1959 አክራ ውስጥ ተጋባን። ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ እሱን በማስቀደማችን በጣም እንደባረከን ተሰማን።
በካሜሩን አብረን ማገልገል
በካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ስሠራ
በ1961 በካሜሩን እንድናገለግል ተመደብን። አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ በማቋቋሙ ሥራ እንድካፈል ተጠይቄ ስለነበር ሥራ በጣም ይበዛብኝ ነበር። አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ እንደመሆኔ መጠን መማር ያለብኝ ብዙ ነገር ነበር። ከዚያም በ1965 ሺላ እንዳረገዘች አወቅን። እውነቱን ለመናገር፣ በቅርቡ ወላጆች እንደምንሆን አምነን መቀበል ትንሽ ከብዶን ነበር። ሆኖም ይህን አዲስ ኃላፊነት ለመቀበል በጉጉት መጠበቅና ወደ ካናዳ ለመመለስ መዘጋጀት በጀመርንበት ወቅት አሳዛኝ ሁኔታ አጋጠመን።
ሺላ ጽንሱ ጨነገፈባት። ሐኪሙ፣ ልጃችን ወንድ እንደነበር ነገረን። ይህ ከሆነ ከ50 ዓመት በላይ አልፏል። ሆኖም ሁኔታውን አልረሳነውም። የተፈጠረው ነገር እጅግ ቢያሳዝነንም በጣም በምንወደው የውጭ አገር ምድባችን ቀጠልን።
በ1965 ከሺላ ጋር ካሜሩን ውስጥ
በካሜሩን ያሉ ወንድሞች በገልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ብዙ ጊዜ ስደት ይደርስባቸው ነበር። በፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ወቅት ደግሞ ሁኔታው ይባባሳል። ግንቦት 13, 1970 የፈራነው ነገር ደረሰ፤ የይሖዋ ምሥክሮች እገዳ ተጣለባቸው። ለአምስት ወር ብቻ የኖርንበት የሚያምረው ቅርንጫፍ ቢሯችን በመንግሥት ተወረሰ። እኔንና ሺላን ጨምሮ ሁሉም ሚስዮናውያን በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአገሪቱ ተባረሩ። ወንድሞችና እህቶችን በጣም ስለምንወዳቸው እነሱን ትተን መሄድ ከብዶን ነበር። ደግሞም ‘ወደፊት ምን ያጋጥማቸው ይሆን’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦን ነበር።
ቀጣዮቹን ስድስት ወራት ያሳለፍነው በፈረንሳይ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው። እዚያ እያለን፣ በካሜሩን ያሉ ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የምችለውን ሁሉ ማድረጌን ቀጠልኩ። በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ በናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተመደብን። በወቅቱ የናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ በካሜሩን የሚከናወነውን እንቅስቃሴ መከታተል ጀምሮ ነበር። በናይጄርያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን። ለተወሰኑ ዓመታት እዚያ በደስታ አገልግለናል።
ከባድ ውሳኔ
በ1973 አንድ ከባድ ውሳኔ ለማድረግ ተገደድን። ሺላ ከተለያዩ የጤና እክሎች ጋር ትታገል ነበር። በትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ኒው ዮርክ በሄድንበት ወቅት እያለቀሰች እንዲህ አለችኝ፦ “ከዚህ በላይ መቀጠል አልችልም! አቅሜ ተሟጧል፤ ሁልጊዜ እንደታመምኩ ነው።” ከ14 ዓመት በላይ በምዕራብ አፍሪካ አብራኝ አገልግላለች። ባከናወነችው የታማኝነት አገልግሎት ደስተኛ ነበርኩ። ሆኖም አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ነበረብን። ስለ ሁኔታችን ከተወያየንና አጥብቀን ከጸለይን በኋላ ወደ ካናዳ መመለስ እንዳለብን ወሰንን። እዚያ የእሷን ጤንነት መንከባከብ ይበልጥ ይቀለናል። የሚስዮናዊነት ምድባችንን እና የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን መተው በሕይወታችን ውስጥ ካደረግናቸው ውሳኔዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ነው።
ካናዳ ከደረስን በኋላ፣ ለረጅም ዘመን ጓደኛችን የነበረ አንድ ወንድም ጋ ሥራ ተቀጠርኩ፤ ወንድም ከቶሮንቶ በስተ ሰሜን በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ የመኪና መሸጫ ነበረው። አፓርታማ ተከራየን፤ እንዲሁም ያገለገሉ የቤት ዕቃዎችን ገዛን። በዚህ መንገድ፣ ዕዳ ውስጥ ሳንገባ አዲሱን ሕይወታችንን መጀመር ቻልን። አንድ ቀን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ልንመለስ እንደምንችል ተስፋ ስላደረግን አኗኗራችንን ቀላል ማድረግ ፈልገን ነበር። የሚገርመው፣ ተስፋችን ከጠበቅነው በላይ በፍጥነት ተፈጸመልን።
በኖርቫል፣ ኦንታሪዮ በሚካሄድ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ግንባታ ላይ ቅዳሜ ቅዳሜ ለመሥራት ራሴን አቀረብኩ። ከጊዜ በኋላ የትላልቅ ስብሰባዎቹ አዳራሽ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጠየቅኩ። የሺላ ጤንነት እየተሻሻለ ስለነበር ይህን አዲስ ምድብ መቀበል እንደምትችል ተሰማን። ስለዚህ ሰኔ 1974 በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሹ ውስጥ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤት ተዛወርን። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ በመቻላችን በጣም ተደሰትን!
ደስ የሚለው፣ የሺላ ጤንነት ይበልጥ እየተሻሻለ ሄደ። ከሁለት ዓመት በኋላ፣ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል የቀረበልንን ግብዣ መቀበል ቻልን። ወረዳው የሚገኘው በኃይለኛ ቅዝቃዜው በሚታወቀው ማንቶባ የተባለ የካናዳ ግዛት ነበር። ሆኖም እዚያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ሞቅ ያለ ፍቅርና ወዳጅነት ነበራቸው፤ በዚህም በጣም ተደስተናል። የምናገለግለው የትም ይሁን የት ለውጥ እንደማያመጣ ተምረናል፤ ዋናው ነገር ባለንበት ቦታ ይሖዋን ማገልገላችን ነው።
ወሳኝ ትምህርት አገኘሁ
ለተወሰኑ ዓመታት በወረዳ ሥራ ከተካፈልን በኋላ በ1978 በካናዳ ቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቆንጠጥ የሚያደርግ ሆኖም ወሳኝ ትምህርት አገኘሁ። በሞንትሪያል በተካሄደ ልዩ ስብሰባ ላይ በፈረንሳይኛ የአንድ ሰዓት ተኩል ንግግር እንዳቀርብ ተመደብኩ። የሚያሳዝነው፣ ንግግሬ የአድማጮቼን ትኩረት መያዝ አልቻለም፤ በመሆኑም በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ የሚሠራ አንድ ወንድም ስለ ንግግሬ ምክር ሰጠኝ። እውነቱን ለመናገር፣ አንደበተ ርቱዕ የምባል ተናጋሪ እንዳልሆንኩ ልገነዘብ ይገባ ነበር፤ ሆኖም ይህ የገባኝ ዘግይቶ ነው። ስለዚህ ምክሩን የተቀበልኩበት መንገድ ጥሩ አልነበረም። ባሕርያችን እንደማይጣጣም፣ እንዲሁም ከመጠን በላይ ተቺ እንደሆነና አመስጋኝ እንዳልሆነ ተሰማኝ። ምክሩ በተሰጠበት መንገድ እንዲሁም ምክሩን በሰጠኝ ሰው ላይ በማተኮሬ የተሳሳተ ምላሽ ሰጠሁ።
በፈረንሳይኛ ንግግር ካቀረብኩ በኋላ ወሳኝ ትምህርት አገኘሁ
ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ስለ ጉዳዩ አነጋገረኝ። እኔም ለምክሩ የሰጠሁት ምላሽ ጥሩ እንዳልነበር አምኜ ተቀበልኩ፤ እንዲሁም በድርጊቴ መጸጸቴን ገለጽኩለት። ከዚያም ምክር የሰጠኝን ወንድም አነጋገርኩት። እሱም ይቅርታዬን በደግነት ተቀበለኝ። ይህ አጋጣሚ ትሕትናን በተመለከተ የማልረሳው ትምህርት ሰጥቶኛል። (ምሳሌ 16:18) ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ በተደጋጋሚ ጸልያለሁ፤ እንዲሁም ከዚህ በኋላ ምክርን አሉታዊ በሆነ መንገድ ላለመመልከት ቆርጫለሁ።
አሁን በካናዳ ቤቴል ማገልገል ከጀመርኩ 40 ዓመት አልፎኛል፤ ከ1985 አንስቶ ደግሞ በቅርንጫፍ ኮሚቴው ውስጥ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። የካቲት 2021 ውዷ ባለቤቴ ሺላ በሞት አንቀላፋች። የእሷ ሞት ካስከተለብኝ ሐዘን በተጨማሪ ከአንዳንድ የጤና እክሎች ጋር መታገል ያስፈልገኛል። ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት ስለተጠመድኩና በዚህም ደስተኛ ስለሆንኩ ‘የሚያልፈውን የሕይወት ዘመኔን ፈጽሞ ልብ አልለውም።’ (መክ. 5:20) ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም ያገኘሁት ደስታ ከመከራው እጅግ የላቀ ነው። በሕይወቴ ውስጥ ይሖዋን በማስቀደሜ እንዲሁም ለ70 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈሌ አርኪ ሕይወት መምራት ችያለሁ። ወጣት ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ይሖዋን ማስቀደማቸውን እንዲቀጥሉ እጸልያለሁ። ምክንያቱም እንዲህ ካደረጉ እነሱም ይሖዋን በማገልገል ብቻ የሚገኘውን አስደሳችና አርኪ ሕይወት ማጣጣም እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ።
a በየካቲት 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ይሖዋ መጠጊያዬና ኃይሌ ነው” በሚል ርዕስ የወጣውን የማርሴል ፊልቶን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።
b እስከ 1957 ድረስ ይህ የአፍሪካ ክፍል “ጎልድ ኮስት” ተብሎ የሚጠራ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነበር።
c በታኅሣሥ 1, 2000 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም” በሚል ርዕስ የወጣውን የኸርበርት ጄኒንዝን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።
d በወቅቱ ሥራችንን በግንባር ቀደምነት የሚመራው ወንድም ናታን ኖር ነበር።