ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች አለመሸሽ
1 ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የማያውቋቸውን ሰዎች ማነጋገሩ ንጹሑን አምልኮ መከተል ለጀመሩ ብዙ ሰዎች በእርግጥ ፈታኝ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለይሖዋ ያለው እውነተኛ ፍቅር ከዚህ ፈታኝ ሁኔታ እንዳይሸሽ ይረዳዋል። እንዲያውም በተፈጥሯቸው ዓይን አፋሮች የነበሩ ሰዎች እንኳን በየጊዜው እያሻሻሉ በመሄድ የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ወደመሆን ደረጃ ደር ሰዋል።
2 የጥንት ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ያበሥሩ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ሥራ 5:42፤ 20:20, 21) በ20ኛው መቶ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖችም በዚህ ሥራ እንካፈላለን። ሰዎች ለመልእክቱ ግድ የሌላቸው ቢሆኑም ወይም ቢበሳጩ፣ የንቀት መልክ ቢያሳዩን ወይም በቀጥታ ቢቃወሙን እንኳን ለአምላክና ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር ይህንን ሥራ ለመሥራት ይገፋፋናል።
3 ከፈታኙ ሁኔታ አለመሸሽ የሚያመጣው ውጤት፦ ወደ ቤታቸው በሄድን ቁጥር ጥቂት የእውነት ዘሮች ለመዝራት ጥረት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም እነዚህ ዘሮች ተጠራቅመው የኋላ ኋላ የመንግሥቱን ፍሬ ሊያፈሩ እንደሚችሉ እናውቃለን። (መክ. 11:6) ግለሰቦች የሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ። የቤቱ ባለቤት አንዳችን በበሩ ላይ ስለተናገርነው ጉዳይ እንዲያስታውስ የሚያደርገው አንድ ነገር ደርሶበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ ስንሄድ ይበልጥ ተቀባይ ሆኖ ልናገኘው እንችል ይሆናል።
4 ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎት ለእውነትና ለጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ተምረው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ይህን ካደረግን ዓለማዊ ደስታዎችን የሚያሳድዱ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ ያገኙ ዘንድ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚገልጽ ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። የቤቱ ባለቤት ይስማም አይስማ ይህ አገልግሎት የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ያደርጋል፤ እንዲሁም ለእርሱ ክብር ያመጣለታል። — ሕዝ. 3:11
5 በአገልግሎቱ መሥራት ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላምና ትዕግሥት የመሳሰሉትን የመንፈስ ፍሬዎች በውስጣችን እንድናዳብር ይረዳናል። (ገላ. 5:22) በአገልግሎቱ መካፈል ለሌሎች ጥሩ ማድረግንም ስለሚጨምር ትሑትና አዛኝ እንድንሆን ይረዳናል። የይሖዋ ሥራ የበዛልን መሆናችን ከዓለም ይጠብቀናል። — 1 ቆሮ. 15:58
6 ሌሎች ከፈታኙ ሁኔታ እንዳይሸሹ እርዱአቸው፦ አዲሶች በጣም አስደሳች በሆነው በዚህ ሥራ እንዴት ለመካፈል እንደሚችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል። ብዙውን ጊዜ በራሳቸው ስለማይተማመኑ ከቤት ወደ ቤት የመሄዱ ሐሳብ ብቻ እንኳን ያስፈራቸዋል። ሊያጋጥሙን የሚችሉት የተለመዱ ተቃውሞዎች ምን እንደሆኑና ለተቃውሞዎቹ ምን ምላሽ ልንሰጥ እንደምንችል ልናወያያቸው እንችላለን። ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሆነ ብለው ውይይታችንን ለማቆም ለሚፈልጉ ሰዎች ምን ልንመልስላቸው እንደምንችል የተሰጡትን ጥሩ ጥሩ ሐሳቦች ተጠቅመን ልንለማመድ እንችላለን። እነርሱን ለመስክ አገልግሎት ለማዘጋጀት ልትረዳቸው እንደምትችል ለምን አትገልጽላቸውም? በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው በመገኘትና ከዚያ ስብሰባ በኋላም የበለጠ ልምድ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር በመሥራት ተጨማሪ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። ከአንድ ቡድን ጋር መሥራታቸውም በጣም ሊያበረታታቸው ይችላል።
7 ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ አምላካችንን ይሖዋን ወክለን የመናገር መብት ይኖረናል። አንድ ሰው የአምላክ ተባባሪ ሠራተኛ ከመሆን የበለጠ ምን ክብር ሊኖረው ይችላል? (1 ቆሮ. 3:9) እርሱን መደገፊያችን ካደረግነው መንፈሱ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት የሚያጋጥመንን ፈታኝ ሁኔታ እንዳንሸሽ ሊረዳን ይችላል። — 2 ቆሮ. 3:5