መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ማቅረብ
1 ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ቁጥር ያላቸው መስማት የተሳናቸው ሰዎች ወደ መልካሙ እረኛ ተስበው በመምጣት ራሳቸውን ለእርሱ ወስነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ዝምድና በመመሥረት ላይ ይገኛሉ። (ዮሐ. 10:3, 11) ሌሎች የጉባኤው ወንድሞች በተለይም ሽማግሌዎች መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ መሆን አለባቸው።
2 መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት፦ ችሎታ ያላቸው ተርጓሚዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ የጉባኤ ስብሰባዎችን በምልክት ቋንቋ ለመተርጎም ዝግጅት ተደርጓል። በጉባኤ ውስጥ የምልክት ቋንቋ የሚችል አንድም ሰው ከሌለ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ሊሰጥ ወደሚችል በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጉባኤ መላክ ተገቢ ይሆናል። በአካባቢያችሁ እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ከሌለ ግን የተወሰኑ አስፋፊዎች ተመድበው መስማት ከተሳነው ግለሰብ አጠገብ በየተራ በመቀመጥ እየተነገረ ያለውን ሐሳብ ዋና ዋና ነጥቦች በማስታወሻ ጽፈው ሊያሳዩት ይችላሉ።
3 በክልልና በጉባኤ ደረጃ የሚደረጉ ዝግጅቶች፦ በክልል ስብሰባዎችና በልዩ ስብሰባ ቀኖች ላይ በምልክት ቋንቋ ለማስተርጎም የሚደረጉትን ዝግጅቶች የክልል የበላይ ተመልካቹ ያስተባብራል። አንድ ሽማግሌ ወይም ብቃት ያለው ዲያቆን አስተባባሪ ሆኖ ሊመረጥ ይችላል። በአርዓያነታቸው የሚጠቀሱ ብቃት ያላቸው ወንድሞችና እህቶች የስብሰባውን ፕሮግራም ተከፋፍለው እንዲያስተረጉሙ ሊመደቡ ይችላሉ። መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እየተሟሉላቸው እንዳሉ በማረጋገጥ በጉባኤም ውስጥ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት መከተል ይቻላል።
4 መስማት የተሳናቸው ሰዎች ተርጓሚዎቹንም መድረኩንም በአንድ አቅጣጫ ሊያዩ በሚችሉበት ቦታ ላይ ቢቀመጡ ጥሩ ነው። በጉባኤም ሆነ በክልል ስብሰባዎች ላይ እንደዚህ ማድረጉ ተገቢ ነው። መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ተርጓሚው ተቀምጦ ቢያስተረጉም ይመረጣል። ተገቢውን አቀማመጥ በተመለከተ ሽማግሌዎች አንድን የጎለመሰ መስማት የተሳነው ወንድም ቢያማክሩት ጥሩ ነው።
5 ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ሆኖ የሚያገለግል አንድ ብቃት ያለው ተርጓሚ ከተገኘና መስማት የተሳናቸው ወንድሞችና እህቶች ቁጥር ብዙ ከሆነ ሽማግሌዎች አንዳንድ ስብሰባዎች በምልክት ቋንቋ ብቻ እንዲደረጉ ሊወስኑ ይችላሉ። በዚህ መልክ ተደራጅተው ሊጀመሩ ከሚችሉት ሳምንታዊ ስብሰባዎች የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል። ጉባኤው በምልክት ቋንቋ (ወይም ጉባኤው በማይጠቀምበት በሌላ በማንኛውም ቋንቋ) ከአምስቱ ሳምንታዊ ስብሰባዎች አንዱን ለማድረግ ከፈለገ ሽማግሌዎች ይህንን ፍላጎታቸውን ለማኅበሩ ማሳወቅ ይገባቸዋል። በአካባቢያችን ባሉት በአብዛኞቹ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ ትምህርት የሚሰጥበትና ሰዎች የሚገባቸው የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ይመስለናል።
6 ምንም እንኳን መስማት የተሳናቸውና መስማት የሚችሉ ሰዎች እርስ በርስ ለመግባባት እንዲችሉ በሁለቱም ወገን ልዩ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ልባዊ ማበረታቻ ለመለዋወጥ እንዲችሉ ሁሉም የጉባኤው አባላት እርስ በርስ ለመተዋወቅ መጣር ይገባቸዋል። (ዕብ. 10:24) በወንድሞች መካከል ይህ ዓይነት መንፈስ ካለ አዲሶች ሁሉ እንግድነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል።