በሌሎች ነገሮች ሳትባክን ይሖዋን አገልግል
1 “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” (መዝ. 144:15 አዓት) እነዚህ የንጉሥ ዳዊት ቃላት በአሁኖቹ ክፉ ቀናትም እውነት ናቸውን? (ኤፌ. 5:16) አዎን! ዛሬም ክርስቲያኖች ይሖዋን በማገልገል ይደሰታሉ። ሁኔታዎች ሁልጊዜ ቀላል ሆነው አናገኛቸውም። ሰይጣን በእነዚህ ‘አስጨናቂ ቀናት’ ልዩ ልዩ ችግሮች እንዲደርሱብን ያደርጋል፤ ቢሆንም ልባችን አይዝልም። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸው በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ይህን የበሰበሰ አሮጌ ዓለም ጠራርጎ በማጥፋት ንጹሕ በሆነ አዲስ ዓለም እንደሚተካው የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (2 ጴጥ. 3:13) ይህ ዓለም ጨለማ መሆኑ አስደሳች ተስፋችን የሚፈነጥቅልንን ብርሃን አያደበዝዘውም ወይም አያጠፋውም፤ ከዚህ ይልቅ የመንግሥቱ ተስፋችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ደምቆ እንዲንጸባረቅ ያደርጋል። በዚህ ጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪ ሆነህ ይሖዋን በማገልገልህ አትደሰትምን? — ፊልጵ. 2:15
2 በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን እንዴት አድርገን እያገለገልነው እንዳለን ሳናቋርጥ መመርመር አለብን። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ታላቅ አባካኝ ስለሆነ ነው። አንድ መዝገበ ቃላት መባከን ተብሎ ሊተረጎም የሚችለውን “ዲስትራክት” የሚል የእንግሊዝኛ ቃል “ወደ ጎን ዞር ማድረግ”፣ “የአንድን ሰው ትኩረት ወደ ተለየ ነገር ወይም አቅጣጫዎች ዘወር እንዲል ማድረግ” እንዲሁም “እርስ በእርስ በሚቃረኑ ውስጣዊ ስሜቶች ወይም የልብ ፍላጎቶች መነሳሳት ወይም ግራ መጋባት” በማለት ይፈታዋል። ሰይጣን ወደዚች ምድር ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የሰውን ዘር ‘ለማሳት’ ቆርጦ ተነስቷል፤ ተሳክቶለታልም። ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ሊተኮርባቸው ከሚገቡ አበይት ጉዳዮች የሰውን ሐሳብ ዘወር የሚያደርግባቸው ብዙ መሣሪያዎች አሉት። (ራእይ 12:9) የይሖዋ ምሥክሮች ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት መንግሥቱን በመስበክ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ስለ ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች ይኸውም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የአምላክ ስም ስለሚቀደስበትና ሉዓላዊነቱ ስለሚረጋገጥበት ሁኔታ የተገነዘቡት ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ከጥረቱ አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት ናቸው። (1 ዮሐ. 5:19) ሰይጣን በዚህች ምድር ላይ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በማዘናጋት ልባቸው እንዲባክን ማድረግ ከቻለ እኛንም በሌሎች ነገሮች እንድንጠላለፍ ወይም ትኩረታችን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞርና የይሖዋን አገልግሎት እንድንተው ሊያደርገን ይችላል። ይህ ምን ጊዜም ያለ አደጋ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን በሰይጣን ማባከኛ ዘዴዎች ግራ ተጋብተዋል፤ ይህም የሚያሳዝን ነው። አሳባቸው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲሳብ ፈቅደውለታል። በዛሬው ጊዜ እንድንባክን የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ። እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።
3 የኢኮኖሚ ችግሮችና ፍቅረ ንዋይ፦ በአብዛኞቹ አገሮች ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ጭንቀት አስከትለዋል። እውነት ነው፣ ለራሳችንና ለቤተሰባችን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘት መቻል አለብን። ነገር ግን ለመኖር ስለሚያስፈልጉን ስለእነዚህ ነገሮች ከመጠን በላይ ከተጨነቅን እነዚህ ሐሳቦች አእምሮአችንን ይቆጣጠራሉ። በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚኖረው በመንግሥቱ ላይ ለተነሣው አከራካሪ ጉዳይ ድጋፍ መስጠት ሳይሆን አካላዊ ደህንነታችን ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን በተመለከተ በዕብራውያን 13:5, 6 ላይ ምክር ሰጥቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድመው መንግሥቱን የሚፈልጉት ሰዎች መጨነቅ የሌለባቸው መሆኑን አረጋግጧል። ይሖዋ በእርግጥ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ይሰጠናል። (ማቴ. 6:25–34) በዓለም ዙሪያ ያሉት አቅኚዎችና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ይህ እውነት መሆኑን ሊያረጋግጡ ችለዋል።
4 የሰይጣን ዓለም ቁሳዊ ነገሮችን መውደድን ያበረታታል። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ተጨማሪ ቁሳቁሶችን ወይም የኑሮ ዋስትና ማግኘት ነው። በኢየሱስ ዘመንም ሐሳብን የሚከፋፍሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ። አንድ ወጣት የሕዝብ አለቃ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ላድርግ ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስም “ፍጹም [ሙሉ] ልትሆን ብትወድ፣ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ” አለው። (ማቴ. 19:16–23) ይህ ወጣት ሰው የነበረው ብዙ ቁሳዊ ሀብት አምላክን በሙሉ ነፍሱ እንዳያገለግል ልቡን የከፋፈለበት ይመስላል። ልቡ ወደ ንብረቱ አዘንብሎ ነበር። ኢየሱስ ወጣቱ ሰው እንዲባክን ካደረጉት ከእነዚህ ነገሮች ጫና ነፃ ቢሆን እንደሚጠቀም አውቋል። የነበረው ቁሳዊ ሀብት በሙሉ ልብ ለአምላክ ያደረ ከመሆን አግዶታል። የአንተ ሁኔታስ እንዴት ነው? የለመድከው አኗኗር እንዳይቀር ስትል በሰብአዊ ሥራ ላይ ብዙ ሰዓታት ታጠፋለህን? ይህስ ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት ነክቶብሃልን? ያሉህ ቁሳዊ ንብረቶች የመንግሥቱን ፍላጎቶች ከልብህ ውስጥ ገፍትረው አስወጥተዋቸዋልን? (ማቴ. 6:24) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የበለጠ ጊዜ ለማግኘት አኗኗርህን ቀለል ማድረግ ትችላለህን?
5 ተራ የሆኑ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች፦ ጠንቃቆች ካልሆን በስተቀር ተራ በሆኑ የዕለት ተዕለት ጉዳዮች በጣም ልንመሰጥና መሟላት የሚገባቸውን መንፈሳዊ ግቦቻችንን ችላ ማለት ልንጀምር እንችላለን። በኖኅ ዘመን የነበሩትን ሰዎች አስታውስ። ኖኅ ስለሚመጣው የውኃ መጥለቅልቅ ይናገር የነበረውን መልእክት ልብ ለማለት ጊዜ እስኪያጡ ድረስ በማኅበራዊ ጉዳዮች ይኸውም በመብልና በመጠጥ፣ በማግባትና ልጆቻቸውን በመዳር ጊዜያቸው በጣም የተጣበበ ሆኖ ነበር። ሁኔታውን ከመገንዘባቸው በፊት የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ አጠፋቸው። በሌሎች ጉዳዮች መባከናቸው ጥፋት አምጥቶባቸዋል። ኢየሱስ “የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል” ብሏል። (ማቴ. 24:37–39) ዛሬም አብዛኞቹ ሰዎች የምናደርስላቸውን የማስጠንቀቂያ መልእክት ትኩረት እንዳይሰጡት በኑሮ ጉዳዮች እጅግ በጣም ተጠላልፈዋል። ለመንፈሳዊ ነገሮች አሳዛኝ ግዴለሽነት አሳይተዋል።
6 ሕይወትህ በማኅበራዊ ጉዳዮች በጣም ከመጣበቡ የተነሣ ለመንፈሳዊ ነገሮች የምትሰጠው ትኩረት እየቀነሰ መጥቷልን? አንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ በማርታና በማርያም ቤት እንግድነት ተጠርቶ ነበር። ማርያም ኢየሱስ የሚናገረውን በጥሞና ታዳምጥ ነበር። በሌላ በኩል ግን ማርታ የቤት ሥራ “ስለበዛባት ባከነች።” ማርታ ጥሩ አስተናጋጅ ሆና ለመገኘት ከመጠን በላይ ተጨንቃ ነበር። ኢየሱስን ማዳመጡን ክብደት አልሰጠችውም። ኢየሱስ ለማርታ ብዙ ዝግጅት ከማድረግ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ትኩረት መስጠት ተገቢ መሆኑን በደግነት አስገነዘባት። ይህን ምክር ልትሠራበት ያስፈልግህ ይሆን? (ሉቃስ 10:38-42) በተጨማሪም ኢየሱስ ከመጠን በላይ በመብላትና በመጠጣት የማስተዋል ስሜታችን እንዳይደንዝ መንቃት ያለብን መሆኑን አስጠንቅቋል። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት ላይ ሙሉ በሙሉ ንቁ መሆን ያስፈልገናል።—ሉቃስ 21:34-36
7 ተድላን ማሳደድ፦ ዲያብሎስ የሰዎችን ትኩረት ከመንግሥቱ ጉዳዮች ዘወር ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ማባከኛዎች አንዱ ተድላን ማሳደድ ነው። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ ቦታ ተድላን ተክተዋል። የአምላክን ቃል በቁም ነገር ከመከታተል ይልቅ በአንዳንድ የጊዜ ማሳለፊያዎች መደሰትን ይመርጣሉ። (2 ጢሞ. 3:4) እርግጥ ነው፣ ጤናማ የሆኑ የጊዜ ማሳለፊያዎችና መዝናኛዎች በራሳቸው መጥፎ አይደሉም። ይሁን እንጂ በእያንዳንዱ ሳምንት እንደ ቴሌቪዥን፣ ፊልም፣ ቪድዮ፣ ስፖርት፣ ዓለማዊ ጽሑፎችን ማንበብ ወይም ደስ የሚሉንን ነገሮች ማድረግን በመሳሰሉ ሁኔታዎች ከመጠን በላይ ጊዜ ማጥፋታችን ከይሖዋ የሚያርቅ ተንኮለኛ ልብ በውስጣችን እንዲበቅል ሊያደርግ ይችላል። (ኤር. 17:9፤ ዕብ. 3:12) ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወቅት አእምሮህ ሊባዝን ይችላል። እንዲሁም ስብሰባው ቶሎ ባለቀና ወደ መደሰቻ ነገሮች መመለስ በቻልኩ ብለህ ልትመኝ ትችላለህ። ብዙም ሳትቆይ በስብሰባ ከመገኘት ወይም በመስክ አገልግሎት ከመሠማራት ይልቅ እቤት የምትቀርበትን ሰበብ መፈላለግ ትጀምራለህ። እነዚህ መደሰቻዎች በሕይወትህ ውስጥ ልብን የሚከፋፍሉ ነገሮች ሆነውብህ እንደሆነና እንዳልሆነ አስበህ ትክክለኛውን ሁኔታ ለማወቅ ጊዜው አሁን ነው። (ሉቃስ 8:14) ለመደሰቻ ከሚባክነው ውድ ጊዜያችን አንዳንዱ ለመንፈሳዊ እድገታችን ቢውል አይሻልም ነበርን?
8 ከመስመር ወጣ ያሉ ጊዜን የሚያባክኑ ነገሮች፦ አንዳንዶች በዘመናዊው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱትን ችግሮች ለማቃለል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ በመግባት ተጠላልፈዋል። ክርስቲያኖች ማለቂያ በሌላቸው አከራካሪ የዓለም ማኅበራዊ ጉዳዮች ወይም የፍትሕ መጓደልን ለማስተካከል በሚደረጉ ፍሬ ቢስ ትግሎች ከመካፈል መራቅ አለባቸው። (ዮሐ. 17:16) ይህ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዲሁም ዘላቂና ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት ነው ከሚለው መሠረታዊ ሐቅ ሐሳባችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ ዘወር ለማድረግ ሰይጣን የሸረበው አንዱ ሸር ነው። በግላችን ጉዳት ከደረሰብን ወይም ፍትሕ ከተጓደለብን ተበቃዮች ወይም በጣም ስሜታዊ በመሆን ማንነታችንን ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እስከመርሳት እንዳንደርስ መጠንቀቅ አለብን። ከሁሉም በላይ በደል ሲደርስበት የኖረው ይሖዋ ነው፤ መቀደስ ያለብንም የእርሱን ስም ነው። — ኢሳ. 43:10–12፤ ማቴ. 6:9
9 ማንም ሰው በመጠኑ ጥሩ ጤንነት እንዲኖረው ይፈልጋል። ነገር ግን የሚቀርቡልንን ለቁጥር የበዙ የጤና አጠባበቅ ምክሮችና መድኃኒቶች ከልክ በላይ የምንከታተል ከሆነ የጤንነት ሐሳብ ሊያስጨንቀን ይችላል። ብዙዎች ለአካላዊና ለስሜታዊ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ብለው የሚናገሩላቸው ዓይነታቸው በጣም የበዛና አንዳቸው ከሌላው የሚቃረኑ የምግብና የሕክምና ዓይነቶች አሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ ጤንነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች በግል የሚወሰኑ ናቸው። ለሰው ልጅ ልዩ ልዩ ሕመም እውነተኛ መፍትሔ የአምላክ መንግሥት ነው የሚለውን እምነታችንን ዘወትር አጽንተን እንያዝ—ኢሳ. 33:24፤ ራእይ 21:3, 4
10 የምትደላደል፣ የማትነቃነቅም ሁን፦ መጨረሻው በቀረበ መጠን ሰይጣን ሐሳባችንን ለይሖዋ ከምናቀርበው አገልግሎት ወደ ሌላ አቅጣጫ ዘወር ለማድረግ በጣም ይጥራል። “በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” (1 ጴጥ. 5:9) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ሐሳቦችን እንደ ምግብ አድርገን ለመመገብ ነው። (ማቴ. 4:4) አንተና ቤተሰብህ በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰልና በጸጥታ ለማብሰልሰል ሊውል የሚችለውን ጊዜ በዓለም ያሉት ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮች እንዲሰርቋችሁ አትፍቀዱ። በአንድ ላይ በምትመገቡበት ጊዜ በሚያንጹ ተሞክሮዎችና በሌሎች መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ። ለግል ጥናትና ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ቋሚ ፕሮግራም አውጣና ፕሮግራምህን አጥብቀህ ተከተል።
11 አእምሮህ እንዳይረጋጋ የሚደርጉ ልዩ ልዩ ሐሳቦች ሲገጥሙህ በጸሎት አማካኝነት ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል። እርሱ ስለ አንተ እንደሚያስብ እርግጠኛ ሁን። (1 ጴጥ. 5:7) የአምላክ ሰላም ልብህንና የማሰብ ኃይልህን እንዲጠብቅ ፍቀድለት። (ፊልጵ. 4:6, 7) ልብን የሚከፋፍሉ ነገሮች መንፈሳዊ እይታህን እንዲያደበዝዙት አትፍቀድ። ኢየሱስ እንዳደረገው ሁልጊዜ ይሖዋን በፊትህ እየው። (ሥራ 2:25) እይታህን ግብህ ላይ አነጣጥር። ምሳሌ 4:25–27 እንዲህ ሲል ያበረታታናል:- “ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፣ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ። የእግርህን መንገድ አቅና፣ አካሄድህም ሁሉ ይጽና ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ።”
12 ሳታቋርጥ በሁሉም ስብሰባዎች ተገኝ። ራስህን እየገሰጽህ ከአምላክ ቃል የሚገኘውን ትምህርት በጥሞና አዳምጥ። (ዕብ. 2:1፤ 10:24, 25) ይህ ውዳቂ ዓለም የሚሰጣቸውን ደስታዎች ከመፈለግ ይልቅ ፍሬያማ አገልግሎት ማገልገል ግብህ ይሁን። ዘላቂ ደስታና እርካታ የሚያስገኘው ይህ ነው። (1 ተሰ. 2:19, 20) በመጨረሻም ምንም ወይም ማንም ከቅዱስ አገልግሎትህ ዘወር አያድርግህ። “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁል ጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” — 1 ቆሮ. 15:58