“ተዘጋጅታችሁ ኑሩ”
1 ኢየሱስ የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ በዕለት ተዕለት የሕይወት ሩጫ ከልክ በላይ መጠላለፍን በሚመለከት አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴ. 24:36-39፤ ሉቃስ 21:34, 35) ታላቁ መከራ በማንኛውም ጊዜ ሊጀምር ስለሚችል “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” የሚለውን የኢየሱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 24:44) በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 የኑሮ ጭንቀቶችንና ጊዜን የሚያባክኑ ነገሮችን ማሸነፍ:- ልንጠነቀቅበት የሚገባን አንዱ መንፈሳዊ ወጥመድ ‘ስለ ኑሮ መጨነቅ’ ነው። (ሉቃስ 21:34 አ.መ.ት) በአንዳንድ አገሮች ድህነት፣ ሥራ ማጣትና የኑሮ ውድነት ለሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገውታል። በሌሎች አገሮች ደግሞ ቁሳዊ ንብረቶችን ማፍራት ከባድ አይደለም። ሆኖም ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ ከጀመርን ትኩረታችንን መንግሥቱን በሚመለከቱ ተጨባጭ እውነታዎች ላይ ማድረግ ያቅተናል። (ማቴ. 6:19-24, 31-33) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትኩረታችንን በመንግሥቱ ላይ እንድናደርግ ይረዱናል። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የመገኘት ግብ አለህ?—ዕብ. 10:24, 25
3 ዛሬ ያለው ዓለም ውድ ጊዜያችንን ሊሻሙብን የሚችሉ በርካታ ነገሮች ያቀርብልናል። አንድ ሰው ኢንተርኔት በመቃኘት፣ ኢ-ሜይል በመጻጻፍ ወይም የኮምፒውተር ጨዋታዎች በመጫወት ከልክ በላይ ጊዜ የሚያጠፋ ከሆነ ኮምፒውተር ወጥመድ ሊሆንበት ይችላል። ቴሌቪዥን ወይም የቪዲዮ ፊልሞችን በመመልከት፣ ዓለማዊ ጽሑፎችን በማንበብ ወይም በስፖርትና በሌሎች የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በርካታ ሰዓታት ማባከን ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ልናውለው የምንችለውን ጊዜና ጉልበት ሊያሟጥጥብን ይችላል። መዝናኛ ጊዜያዊ እርካታ ሊያስገኝልን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስን በግልና በቤተሰብ ማጥናት ግን ዘላቂ ጥቅሞች አሉት። (1 ጢሞ. 4:7, 8) በየዕለቱ በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ትመድባለህ?—ኤፌ. 5:15-17
4 የይሖዋ ድርጅት “ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም” እንድንችል መንፈሳዊ ትምህርት የምናገኝበትን ፕሮግራም ስላዘጋጀልን ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል! (ሉቃስ 21:36) በእነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች በሚገባ በመጠቀምና ‘ተዘጋጅተን በመኖር’ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፣ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም” የሚሆን እምነት ይኑረን።—1 ጴጥ. 1:6, 7