በጊዜ አጠቃቀማችሁ ረገድ ጠንቃቆች ሁኑ
1. ዛሬ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ምን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
1 ጊዜና ጉልበት እንዲቆጥቡ ተብለው የተዘጋጁ መሣሪያዎች ባሉበት በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ሊያከናውኗቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች እንዳሉና እነዚህን ለመፈጸም ግን ጊዜ እንደሚያጥራቸው ይሰማቸዋል። ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ ፕሮግራም መከተል አስቸጋሪ ሆኖብሃል? ለአገልግሎት የበለጠ ጊዜ ብታገኝ ደስ ይልሃል? ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?—መዝ. 90:12፤ ፊልጵ. 1:9-11
2, 3. የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ ምን ፈታኝ ሁኔታ አስከትሏል? እያንዳንዳችን ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
2 ጊዜ የሚያባክኑብህን ነገሮች እወቅ:- ሁላችንም ጊዜያችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት አልፎ አልፎ መመርመር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (ኤፌ. 5:15, 16) የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ ያደረገው እድገት ያስከተለውን ፈታኝ ሁኔታ አስብ። ኮምፒውተሮችም ሆኑ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ጠቃሚ ቢሆኑም በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ጠንቃቆች ካልሆንን ወጥመድ ሊሆኑብን ይችላሉ።—1 ቆሮ. 7:29, 31
3 ሁላችንም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል:- ‘በኮምፒውተር አማካኝነት የሚተላለፉ ምንም የማይጠቅሙ መልእክቶችን በማንበብ ወይም መልስ በመጻፍ በየቀኑ ጊዜ አጠፋለሁ? ፍሬከርስኪ ስለሆኑ ጉዳዮች በስልክ የማውራት ወይም ኢ- ሜይል የመላክ ልማድ አለኝ? (1 ጢሞ. 5:13) ምንም ዓላማ ሳይኖረኝ ኢንተርኔት በመመልከት ወይም የተለያየ ጣቢያ እየቀያየርኩ ቴሌቪዥን በማየት ጊዜዬን አባክናለሁ? በኮምፒውተር ጨዋታዎች መጠመዴ የአምላክን ቃል ለማጥናት የመደብኩትን ጊዜ እየተሻማብኝ ነው? ሻይ ቤት ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጬ ወይም ከማያምኑ ዘመዶቼ ጋር በመጫወት ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ?’ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ሳይታወቀን መንፈሳዊነታችንን ሊያሳጡን ይችላሉ።—ምሳሌ 12:11
4. አንድ ወጣት ምን ለውጥ አደረገ? ለምንስ?
4 ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም:- የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ጊዜያችንንም ሆነ ትኩረታችንን ይሰርቃሉ። በኮምፒውተር ጨዋታዎች በጣም ተጠምዶ የነበረ አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “አንዳንድ ጊዜ ወደ አገልግሎት ከመውጣቴ ወይም ስብሰባ ከመሄዴ በፊት የኮምፒውተር ጨዋታ ከተጫወትኩ ትኩረቴን መሰብሰብ በጣም ያስቸግረኛል። ሁልጊዜ ማለት ይቻላል፣ እቤት ከተመለስኩ በኋላ አንድን ጨዋታ እንዴት በተሻለ መንገድ ልጫወተው እንደምችል አስባለሁ። የግል ጥናቴና ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራሜ ተዳከመ። አምላክን በማገልገል የማገኘውን ደስታ እያጣሁ መጣሁ።” ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ስለተገነዘበ የኮምፒውተር ጨዋታዎቹን በሙሉ ደመሰሳቸው። “እንደዚያ ማድረጉ በጣም ከብዶኝ ነበር” በማለት ያስታውሳል። “ካሰብኩት በላይ በእነዚህ ጨዋታዎች ተጠምጄ ነበር። ሆኖም ይህንን እርምጃ መውሰዴ እንደሚጠቅመኝ ስለተገነዘብኩ የድል አድራጊነት ስሜት አደረብኝ።”—ማቴ. 5:29, 30
5. ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ መዋጀት የምንችለው እንዴት ነው? እንደዚህ በማድረጋችንስ ምን ጥቅም እናገኛለን?
5 ማስተካከያ ልታደርግባቸው የሚገቡ ነገሮች ካሉ ልክ እንደዚህ ወጣት እርምጃ መውሰድ ያስፈልግህ ይሆናል። አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዳዮችን በመተው በየቀኑ ግማሽ ሰዓት ያህል መዋጀት ትችላለህ? በየዕለቱ ይህን ያህል ሰዓት ማግኘት ከቻልክ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ዓመት ውስጥ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ። ይህ በመንፈሳዊ እንዴት የሚክስ ነው! (መዝ. 19:7-11፤ 119:97-100) መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፣ ለስብሰባዎች ለመዘጋጀትና ለመስክ አገልግሎት የተወሰነ ጊዜ መድብ። (1 ቆሮ. 15:58) እንደዚህ ማድረግህ ጊዜህን የሚያባክኑብህን ልማዶች ለመቆጣጠርና ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል’ ያስችልሃል።—ኤፌ. 5:17