በሰው ልጆች ፈጣሪ ላይ ያላቸውን እምነት መገንባት
1 አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ሕይወት አጀማመር ወደ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ደርሰዋል። ብዙዎች ዝግመተ ለውጥን እንደ መፍትሔ አድርገው እንዲቀበሉ በስህተት የተማሩ መሆናቸው የሚያሳዝን ነው። ፍጥረት የተባለው መጽሐፍ ፍጥረትንም ሆነ ዝግመተ ለውጥን በጥልቀት ይመለከትና መጽሐፍ ቅዱስን የሚደግፉ ብዙ ማስረጃዎችን ያቀርባል። ለመስማት ፍላጎት ያላቸውን ልበ ቅን ሰዎች ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ነው። ተመልሰን በምንሄድበት ጊዜ በፈጣሪያችን በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያዳብር አንድ የተወሰነ ነጥብ ለመናገር አስበን መሄዱ ጥሩ ነው።
2 ሰውዬው በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምን መሆኑን ከገለጸ ይህ አቀራረብ ንግግር ለመጀመር ውጤታማ መግቢያ ሊሆንልህ ይችላል፦
◼ “ኢሳይያስ 45:18 ስለ አጽናፈ ዓለም አጀማመር አሳማኝ በሆነ መንገድ ይናገራል። ስለ ጉዳዩ ያለዎትን ሐሳብ ባውቅ ደስ ይለኛል። [አንብብለትና ሐሳብ እንዲሰጥ አድርግ።] ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ መሆኑን እዚህ ላይ ተናግሯል። በዚህች ምድር ላይ ስላለው ሕይወትስ ምን ሊባል ይቻላል? ኢሳይያስ 42:5 በምድር ላይ ሕይወት እንዲገኝ ያደረገም ይሖዋ ነው ይላል። [አንብብ።] መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው እውነት ከሆነ ዝግመተ ለውጥ ሐሰት መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉ ሆኖ ይሰማዎታል? ” ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 አውጣና ይሖዋ ፈጣሪ መሆኑን ለማመን የሚያስችሉንን ተጨማሪ ነጥቦች ጥቀስ።
3 እንዲህ ባለ አቀራረብ ንግግር ልትጀምር ትችላለህ፦
◼ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳለ የሰው ልጅና የምድር የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ አንሥተን ነበር። የሰጠሁዎት መጽሐፍ ይህን ጥያቄ እንዴት እንደሚመልስ ይመልከቱ።” ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 234–5 አውጣና አንቀጽ 6 እና 7ን እንዲያነብ ጋብዘው። ተጨማሪ ፍላጎት ካሳየ እንዲህ ብለህ ጠይቀው:- “በምድር ላይ ምን ዓይነት አስደናቂ ለውጥ ይፈጸማል ብለው ያስባሉ?” አስፈላጊ ከሆነ ይህን ነጥብ በዚያው ወቅት አለዚያም በሚቀጥለው ጉብኝት ጊዜ ፍጥረት ከሚለው መጽሐፍ በዚያው ምዕራፍ ላይ ቀጥሎ ባሉት አንቀጾች ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ይቻላል።
4 ሰውዬው ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያለው ከመሰለህ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦
◼ “በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ተፈጥሮን ልክ እንደ ፈጣሪ አድርገው ሲናገሩ ሰምተው ያውቃሉን? [ሐሳብ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው ፈጣሪ ማን መሆኑን ለማወቅ እንድንቸገር ወይም እንዲሁ በጨለማ እንድንደናበር አይተወንም።” ራእይ 4:11ን አንብብ። ጥቅሱ ከተነበበ በኋላ ሰውዬው ስሜቱን ይገልጽ ይሆናል። ከዚያም ፍጥረት ከተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ 11 ላይ በአንድ ወይም በሁለት ነጥቦች ላይ እንዲያተኩር አድርግ፤ በተጨማሪም በክርስቶስ በሚተዳደረው ንጉሣዊ መንግሥት አማካኝነት መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ ያለውን ዓላማ ጎላ አድርገህ ልትገልጽለት ትችላለህ።
5 ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ውይይቱን እንዲህ በማለት መጀመር ትችላለህ፦
◼ “በተንኮልና በክፋት ምክንያት የሰው ልጅ ብዙ ሥቃይና መከራ ሲደርስበት ኖሯል። የዚህች ምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች እንደሚያቆሙ ተስፋ ሰጥቷል። [ገጽ 196ን አውጣና ምሳሌ 2:21, 22ን አንብብለት።] ይሖዋ ፈጣሪያቸው መሆኑን አምነው የሚቀበሉና ፈቃዱን የሚፈጽሙ አስደናቂ በረከቶችን እንደሚያገኙ ሊጠባበቁ ይችላሉ።” ለዚያ ወቅት ተስማሚ ከሆነ ከገጽ 197–8 በራእይ 21:4, 5 ላይ ውይይቱን ልትቀጥሉ ትችላላችሁ።
6 ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የተወሰነ ቀጠሮ መያዝ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ለዚህ ሥራ ግልጽ ዝግጅት ማድረጉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ወዲያውኑ ተከታትለን እንድንረዳ ያስችለናል። ለአንተም ሆነ በአገልግሎት ክልሉ ለሚኖሩት ሰዎች ይበልጥ ተስማሚ የሆነውን ጊዜ ምረጥ። በዚህ ሥራ አዘውትረህ ስትሳተፍ “ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ትእዛዝ በመፈጸምህ ደስታ ታገኛለህ። — ማቴ. 28:19, 20