ትንንሽ ልጆች መልካም ምሳሌ ያስፈልጋቸዋል
1 ‘የይሖዋን ስም የሚያወድሱ’ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ወጣቶች በመካከላችን በመኖራቸው ደስ ይለናል። (መዝ. 148:12, 13 አዓት) ብዙዎቹ ገና ልጆች ናቸው። እድገታቸው ከወላጆቻቸውና በጉባኤ ውስጥ ባሉ ሌሎች አዋቂዎች በሚያገኙት ሥልጠናና አርዓያነት ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተመካ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች ወጣቶች በተለይም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ከፍ ያሉ ወጣቶችና ጎልማሶች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ከሆነ እዚህ ላይ የቀረቡት ሐሳቦች ይጠቅሙህ ይሆናል።
2 ከአሥራዎቹ ዕድሜ በታች ያሉ ልጆች በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ ያሉ ታላላቆቻቸውን መምሰል ይወዳሉ። በተፈጥሯቸው፣ አንድን በጣም የሚያደንቁትንና የሚቀርቡትን ሰው የመምሰል ፍላጎት አላቸው። ከነሱ የበለጠ እውቀትና እድገት ያላቸው የሚመስሉትን በዕድሜ የሚበልጧቸውን ሌሎች ወጣቶች ከፍ አድርገው ወደ መመልከት ያዘነብላሉ። በዚህም ምክንያት ያንተንም አነጋገርና ጠባይ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለህን አድናቆትና በጉባኤ የምታደርገውን ተሳትፎ ሊቀዱ ይችሉ ይሆናል።
3 በዕድሜ ከፍ ያልክ ወጣት በመሆንህ አንዳንድ መብቶች እንዳሉህ ሁሉ ከባድ ኃላፊነትም አለብህ። አሁን በዚህች ጊዜ የምታሳየው ምሳሌ እንኳን ታናናሽ ጓደኞችህ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ሊሆን ይችላል። እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በታናናሾቼ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እያሳደርኩ ነኝ? ቁም ነገረኛ የሆንኩ እንዲሁም ከሞኝነትና “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት” የራቅሁ ነኝን? ወላጆቼን፣ ሽማግሌዎችንና ሌሎች በዕድሜ የገፉ ሰዎችን የምታዘዝና የማከብር ነኝን?’ (2 ጢሞ. 2:22፤ ቆላ. 3:20) የምትናገረውና የምታደርገው ነገር እንቅስቃሴዎችህን ለሚከታተሉ ታናናሾችህ መንፈሳዊ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል።
4 የመንግሥቱን መልእክት መስበክ የጉባኤው ተቀዳሚ ሥራ ነው። በዚህ ሥራ ለመካፈል ያለህ ፈቃደኝነትና አዘውትረህ በሥራው የምትካፈል መሆንህ ጓደኞችህ ይበልጥ ትጉዎች እንዲሆኑ ሊያበረታታቸው ይችላል። የአቅኚነት አገልግሎት ልትጀምር ብትችል ጓደኞችህም እንዲሁ ለማድረግ ይገፋፋሉ። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ብትሰጥና በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለሚሠሩ አስፈላጊ ሥራዎች በፈቃደኝነት እርዳታ ብታበረክት ጥሩ አርዓያ ትሆናቸዋለህ።
5 ምንም እንኳን ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሚከተለውን ምክር በሰጠው ጊዜ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያልነበረ ቢሆንም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኙት እናንተ ግን ተግባራዊ ልታደርጉት ትችላላችሁ፦ “በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን።” (1 ጢሞ. 4:12) በይሖዋ አገልግሎት በሙሉ ነፍስህ በግለት ብትሳተፍ ብዙ ጊዜ የሚቀራረቡህና የምታደርገውን የሚከታተሉ ታናናሾችህ እድገት በማሳየት በመንፈሳዊ ረገድ አዋቂዎች እንዲሆኑ በመርዳት ገንቢ ግፊት ልታሳድርባቸው ትችላለህ። (ኤፌ. 4:13) በቅርቡ ማጥናት በጀመሩ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ ወጣቶች ከሚያዩብህ ነገር የተነሣ ወደ እውነት ሊሳቡ ይችላሉ።
6 ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አምላካዊ የሆነ ጠባይ ለማሳየት የምታደርገው ትጋት ይሖዋንና ድርጅቱን ያስከብራቸዋል። (ምሳሌ 27:11) እውነተኛ ታዛቢዎች በአንተና በዓለም ውስጥ ባሉ ወጣቶች መካከል በሚያዩት አስደናቂ ልዩነት መገረማቸው አይቀርም። ስለዚህ ይሖዋን ለማወደስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረግህ ታናናሾችህንም ለመርዳት የምትችልበት ልዩ አጋጣሚ አለህ።—መዝ. 71:17