ማዘናጊያዎችን በማስወገድ ነቅተን እየኖርን ነውን?
1 ኢየሱስ ከሚመጣው ጥፋት “ለማምለጥ እንድትችሉ . . . ነቅታችሁ ኑሩ” በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ሉቃስ 21:36 አዓት) በሰው ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ አደገኛ ጊዜ ውስጥ እንኖራለን። ለመንፈሳዊ ድብታ እጃቸውን የሚሰጡ ሰዎች ጥፋት ይጠብቃቸዋል። ይህም በእያንዳንዳችን ፊት አደጋ እንዲደቀን ያደርጋል። ኢየሱስ ስለ መብላት፣ ስለ መጠጣትና ስለ ዕለት ተዕለት ኑሮ መጨነቅን አስመልክቶ ተናግሯል። ስለ እነዚህ ነገሮች የተናገረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩት፣ ሊያዘናጉንና አደገኛ መንፈሳዊ ድብታ ሊያስከትሉብን ስለሚችሉ ነው።
2 የተለመዱ ማዘናጊያዎች፦ አንዳንዶች በተንዛዙ ወይም አጠያያቂ በሆኑ መዝናኛዎች ጊዜያቸው ተይዟል። አልፎ ተርፎም የቴሌቪዥን ሱሰኞች ሆነዋል። እርግጥ ነው፣ መንግሥቱን ማስቀደም ማለት ከማንኛውም ዓይነት መዝናኛ መራቅ አለብን ማለት አይደለም። መዝናኛን ምክንያታዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስንጠቀምበት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ከ1 ጢሞቴዎስ 4:8 ጋር አወዳድር።) አብዛኛውን ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን ወይም በመንግሥቱ ስብከት የምናደርገውን ተሳትፎ በመንካት በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ሲይዝ ግን ማዘናጊያ ይሆናል።
3 ሌላው መንፈሳዊ ድብታ የሚያስከትል የተለመደ ማዘናጊያ አላስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን የማግኘት ፍላጎት ነው። ይህም አንድ ሰው በሰብዓዊ ሥራው ብዙ ሰዓት እንዲያሳልፍና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ያለው ጊዜ እንዲጣበብ ያደርገዋል። አንዳንዶች ይበልጥ የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ሲሉ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት በመሯሯጥ ስለተዋጡ ዓይናቸውን ከመንፈሳዊ ግቦቻቸው ላይ ነቅለዋል። “ምግብና ልብስ” የሚያስፈልገን ቢሆንም ከእምነት ሊያባዝነን የሚችለው የገንዘብ ፍቅር በውስጣችን እንዳያድግ መጠንቀቅ አለብን። (1 ጢሞ. 6:8–10) ዓይናችንን ከመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ ከነቀልን የቤተሰባችንን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ግድ የለሽ ልንሆንና አገልግሎታችንን ማከናወን ሊያቅተን ይችላል።— 1 ጢሞ. 5:8፤ 2 ጢሞ. 4:5
4 አንዳንዶች መንፈሳዊ እንቅልፍ እስኪወስዳቸው ድረስ ‘ልባቸው በሕይወት ውጣ ውረዶች አንዲከብድ’ ፈቅደዋል። (ሉቃስ 21:34 አዓት) አንዳንድ ጊዜ የጤንነት እክል ወይም ቤተሰብ ውስጥ የሚከሰቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጭንቀት ይፈጥራሉ። ቢሆንም እንደነዚህ ያሉ በግለሰብ ደረጃ የሚያስጨንቁን ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቃረበ ስላለው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ያለንን ግንዛቤ እንዲያደበዝዙብን ልንፈቅድላቸው አይገባም።— ማር. 13:33
5 ዲያብሎስ እኛን በማይጨበጥ ዓለም ውስጥ በመክተት አንድ ዓይነት ዓለማዊ ቅዠት እንድናሳድድ ከማድረግ የበለጠ የሚያስደስተው ነገር የለም። በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን ለመኖር መጋደል አለብን። ‘የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ እንደሚመጣ’ ስለምናውቅ ‘ንቁ ሆኖ መኖርና የማስተዋል ስሜቶቻችንን መጠበቅ’ አስፈላጊ ነው። (1 ተሰ. 5:2, 6 አዓት) መንፈሳዊ ድብታ እንደያዘን የሚጠቁሙ ምልክቶች በራሳችን ላይ ማስተዋል ከጀመርን ‘የጨለማ ሥራዎችን አውጥቶ መጣሉ’ አጣዳፊ ነው።— ሮሜ 13:11–13
6 ንቁ ሆነን ለመኖር የሚረዱን ነገሮች፦ እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው? ጸሎት ወሳኝነት አለው። ሳናቋርጥ መጸለይ አለብን። (1 ተሰ. 5:17) ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መቀራረባችን ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ያነቃቃናል።’ (ዕብ. 10:24) ዘወትር በሐቀኝነት ራሳችንን መመርመራችን ድክመቶቻችንን ለመቋቋም በሚያስችል ሁኔታ ንቁዎች ሆነን ለመኖር ሊረዳን ይችላል። (2 ቆሮ. 13:5) ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ‘የእምነትን ቃል እየተመገብን’ እንድንቀጥል ያስችለናል። (1 ጢሞ. 4:6) ትጉዎች ከሆንን የሚያዘናጉ ነገሮችን ለማስወገድ፣ ‘ንቁዎች ለመሆንና በእምነት ጸንተን ለመቆም’ እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።— 1 ቆሮ. 16:13