ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀትና ከስብሰባዎቹ መጠቀም
1 የወንድማማች ማኅበር አባል እንደመሆናችን መጠን በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ዘወትር መገኘታችን ጥሩ ነው። (1 ጢሞ. 4:15, 16) በስብሰባዎች መደሰትና የተሻለ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ለስብሰባዎች የምንዘጋጅበት ቋሚ ጊዜ መመደብ አለብን። አንዳንዶች ለስብሰባዎች ዝግጅት ለማድረግ ከሌሎች የበለጠ ሰፋ ያለ ጊዜ መመደብ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ምንም ያህል በሥራ ብንዋከብም የተወሰነ ጊዜ ወስዶ ለስብሰባዎች መዘጋጀት አስፈላጊ ነው። በተለይ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው።— ኤፌ. 5:15, 16
3 ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት፦ ከሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ጋር እኩል ለመራመድ ጥረት አድርግ። (ኢያሱ 1:8) በስብሰባው ላይ የሚቀርቡትን ክፍሎች አስቀድመህ ከልስ፤ እንዲሁም ተናጋሪዎቹን መከታተል እንድትችል የሚያስፈልጉ ጽሑፎችን ይዘህ ሂድ። የሚሰጠውን ትምህርት በአገልግሎትህ መጠቀም የምትችልባቸውን መንገዶች አስብ።
4 ለአገልግሎት ስብሰባ፦ በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን ፕሮግራም ተመልከት። በስብሰባው ላይ የሚቀርቡትን ርዕሶች አንብብ። በአንድ መጠበቂያ ግንብ ወይም በሌሎች ጽሑፎች ላይ የሚገኝ ትምህርት የሚቀርብ ከሆነ ይህንንም ጽሑፍ አውጥተህ አንብበው። በመስክ አገልግሎት የምንጠቀምባቸውን አቀራረቦች በሠርቶ ማሳያዎች የሚቀርቡ ከሆነ በአገልግሎትህ ለመጠቀም ዝግጁ እንድትሆን አስቀድመህ ከልሳቸው።
5 ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት፦ የሚጠናውን ርዕስ ቀደም ብለህ በማንበብ ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሆኑትን አስምርባቸው። የተጠቀሱትን ጥቅሶች እያወጣህ ማንበብህ ሐሳቡን ይበልጥ እንድትረዳው ያስችልሃል። ትምህርቱ አስቀድሞ ከምታውቀው ነገር ጋር እንዴት እንደሚስማማ ማሰላሰልህ እውቀትህን ያሰፋልሃል። ቢያንስ በአንድ ወይም በሁለት አንቀጾች ላይ አጠር ያለ ሐሳብ ለመስጠት በመዘጋጀት በጥናቱ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዕቅድ አውጣ። ተሳትፎ ማድረጉ “ተስፋችንን በሰው ፊት የምንገልጽበት” ዋንኛ መንገድ ነው።— ዕብ. 10:23 አዓት
6 ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናት፦ በመጀመሪያ የሚጠናውን ክፍል አጠቃላይ ይዘት ተመልከት። የምዕራፉን ርዕስና ንዑስ ርዕሶቹን ተመልከት። ስታነብ ቁልፍ ሐሳቦችን ልብ በል። ለድጋፍ የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተመልከት። መልሶቹን በራስህ አባባል ለመመለስ ሞክር። ተዘጋጅተህ ስትጨርስ በአእምሮህ ከልሰው። ዋና ዋና ነጥቦቹንና ሐሳቦቹን ለማስታወስ ሞክር።— 2 ጢሞ. 2:15
7 ከስብሰባዎች መጠቀም፦ ከስብሰባዎች ሙሉ ጥቅም ለማግኘት በሰዓቱ መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው። በሰዓቱ ከደረስን ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን በሚቀርበው የመክፈቻ ጸሎት ላይ መገኘት እንችላለን። በተጨማሪም መንፈስን ከሚያድሱት የመንግሥቱ መዝሙሮች ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። ትንንሽ ልጆች ከሌሉህ ወይም በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከኋላ እንድትቀመጥ የሚያስገድዱህ ሌሎች ምክንያቶች ከሌሉ ፊት ብትቀመጥ ብዙም ሐሳብን የሚከፋፍል ነገር ሳያጋጥምህ ከስብሰባው ብዙ ጥቅም ታገኛለህ። ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ ወደ ውጪ መውጣት ሊያስፈልጋቸው ስለሚችል በመተላለፊያው አቅራቢያ ወደ ኋላ በመቀመጥ የአድማጮችን ሐሳብ እንዳይከፋፈል ሊያደርጉ ይችላሉ።
8 የሚነበቡትን ጥቅሶች አውጥተህ ለመከታተል ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ የምትሰማውን ነገር ለማስታወስ ይረዳሃል። የተማርከውን ነገር ለቤተሰብህና ለጓደኞችህ መንገርህ ትምህርቱ ጭንቅላትህ ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ብናውል ስብሰባዎች ይበልጥ ትርጉም ያላቸውና አስደሳች ይሆኑልናል፤ በተጨማሪም ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ያነቃቁናል።’— ዕብ. 10:24, 25