እድገት የሚያደርጉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት
1 በታንዛኒያ የምትኖረውን አንዲት ነርስ፣ በአርጀንቲና የምትኖረውን አንዲት ወጣትና በላትቪያ የምትኖረውን አንዲት እናት የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? በእያንዳንዱ ሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ለማጥናት ፈቃደኛ በመሆናቸው ሦስቱም በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ፈጣን እድገት እንዳደረጉ የ1997 የዓመት መጽሐፍ (ገጽ 8, 46 እና 56) ሪፖርት አድርጓል። አስፋፊዎች በተቻለ መጠን በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ የመጽሐፉን አንድ ምዕራፍ ለመሸፈን እንዲጥሩ ሐሳብ ቀርቦላቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንዲህ ማድረግ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ምንም እንኳን በአብዛኛው የሚመካው እያንዳንዱ ተማሪ ባለው ሁኔታና የመማር ችሎታ ላይ ቢሆንም ተሞክሮ ያካበቱ አስተማሪዎች ከዚህ በታች የሰፈሩትን ሐሳቦች ሥራ ላይ በማዋል ውጤት አግኝተዋል።
2 በሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ በተብራራው መሠረት ተማሪያችሁ ለጥናቱ እንዲዘጋጅ ማሰልጠኑ አስፈላጊ ነው። ገና ከመጀመሪያው ዝግጅት ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ማሳየት ጥሩ ይሆናል። የምታስጠኑበትን እውቀት የተሰኘውን መጽሐፍ የራሳችሁን የግል ቅጂ አሳዩአቸው። የመጀመሪያውን ትምህርት አብራችሁ ተዘጋጁ። ተማሪው መጽሐፉ ላይ ለሰፈረው ጥያቄ በቀጥታ መልስ የሚሆኑትን ቁልፍ ቃላት ወይም ሐረግ ፈልጎ እንዲያገኝ እርዱት፤ ከዚያም መልሱ ላይ አስምሩበት ወይም ምልክት አድርጉበት። አንዳንድ አስፋፊዎች ደመቅ አድርጎ የሚያሰምር እርሳስ ለተማሪዎቻቸው ሰጥተዋቸዋል። ለጥናት በሚዘጋጁበት ጊዜ ሁሉንም ጥቅሶች አውጥተው እንዲያነቡ አበረታቷቸው። እንዲህ በማድረግ ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናትና ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንዲዘጋጁ ታሰለጥኗቸዋላችሁ።— ሉቃስ 6:40
3 ጥሩ አስተማሪ ተማሪው እንዲናገር ያደርጋል እንጂ እርሱ ብዙ አይናገርም። ጥቃቅን ነጥቦችን ለማብራራት ወደ ሌላ ርዕስ ከመሄድ ይታቀባል። አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከመጽሐፉ ውጪ ተጨማሪ ሐሳቦችን አያመጣም። ከዚህ ይልቅ የትምህርቱን ዋና ዋና ነጥቦች ያጎላል። አንዳንዶች ተማሪዎቻቸው ላሏቸው ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ተጨማሪ ጽሑፍ ይሰጧቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ተጨማሪ ጥልቅ ማብራሪያዎችን ያገኛሉ።
4 በትምህርቱ ውስጥ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የሰፈሩትን ጥቅሶች በሙሉ ማንበቡ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ዋና ዋና ነጥቦች አንቀጾቹ ውስጥ ሐሳባቸው ከሰፈረው ጥቅሶች ሊብራሩ ይችላሉ። ክለሳ በምታደርጉበት ጊዜ ውይይት ያደረጋችሁበትን ቁልፍ ጥቅስ ጎላ አድርጉ፤ እነዚህንም ጥቅሶች እንዲያስታውሳቸው ተማሪውን አበረታቱት።
5 እያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል ሰዓት መፍጀት ይኖርበታል?:- ጥናቱ ለአንድ ሰዓት ብቻ መገደብ አይኖርበትም። አንዳንዶች በቂ ጊዜ ስላላቸው ረዘም ላለ ጊዜ ማጥናት ይፈልጉ ይሆናል። ወይም ተማሪው በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ማጥናት ይፈልግ ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ለሚችሉ ይህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
6 በኢሳይያስ 60:8 ላይ እንደተገለጸው “ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፣ እንደ ደመና የሚበርሩ” በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ይሖዋን የሚያወድሱ አዳዲስ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ ወደሚገኙበት ጉባኤ በመጉረፍ ላይ ናቸው። ይሖዋ በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን የመሰብሰቡን ሥራ በሚያፋጥንበት ጊዜ ከእርሱ ጋር ጎን ለጎን በመሥራት ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ እናከናውን።— ኢሳ. 60:22