ወንጌል በኢንተርኔት
በዛሬው የቴክኖሎጂ ዘመን አንዳንድ ሰዎች መረጃዎችን የሚያገኙት ኢንተርኔትን ጨምሮ በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ ውጤቶች አማካኝነት ነው። በመሆኑም ማኅበሩ የይሖዋ ምሥክሮችን እምነትና እንቅስቃሴ የሚመለከቱ አንዳንድ ትክክለኛ መረጃዎችን ኢንተርኔት ውስጥ አስገብቷል።
የኢንተርኔት ዌብ ሳይት አድራሻችን http://www.watchtower.org ሲሆን በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ (ቀለል ባለው)፣ በጀርመንኛ በሩስያኛ እና በስፓንኛ እንዲሁም በሌሎች ቋንቋዎች የሚገኙ አንዳንድ የተመረጡ ትራክቶችን፣ ብሮሹሮችን እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ርዕሶችን አካትቶ ይዟል። በዚህ ዌብ ሳይት ውስጥ ያሉት ጽሑፎች በጉባኤያችን የሚገኙና በአገልግሎት የምንጠቀምባቸው ናቸው። የዌብ ሳይቱ ዓላማ አዲስ የሚወጡ ጽሑፎችን ማስተዋወቅ ሳይሆን ብዙ ሰዎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት መረጃዎችን እንዲያገኙ መርዳት ነው። ማንኛውም ግለሰብ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ወይም እምነት ለመግለጽ በማሰብ በኢንተርኔት ውስጥ የመረጃ መስክ መክፈት አያስፈልገውም። ኦፊሴላዊ ሳይታችን ፍላጎት ላላቸው ሁሉ ትክክለኛውን መረጃ ይሰጣል።
ሳይታችን የኤሌክትሮኒክ መልእክት (ኢ ሜይል) መላላክ የሚያስችል ዝግጅት ባይኖረውም በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የቅርንጫፍ ቢሮዎች የፖስታ አድራሻ ይዘረዝራል። ስለሆነም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወይም በአካባቢያቸው የሚገኙ ምሥክሮች በአካል ተገናኝተው እንዲረዷቸው የሚፈልጉ በዚህ መንገድ መጻፍ ይችላሉ። በዚህ ዝግጅት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመማር ዝንባሌ ያድርበታል ብላችሁ ላሰባችሁት ለማንኛውም ግለሰብ ከላይ ያለውን አድራሻ ለመስጠት ነፃነት ይሰማችሁ።