ሰዎችን ለመርዳት የተደረገ ዝግጅት
እውነተኛ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በማወጅ ሕዝባዊ አገልግሎት ያከናውናሉ። (ፊልጵ. 2:17) ይህንን ግብ ዳር ለማድረስ በ20 ቋንቋዎች የተዘጋጁና መሠረታዊ እውቀት ለማግኘት የሚረዱ አንዳንድ ብሮሹሮችን፣ ትራክቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን www.watchtower.org በሚለው አድራሻ በኢንተርኔት ማግኘት የሚቻልበት ዝግጅት ተደርጓል። ይህ ድኅረ ገጽ (web site) የተዘጋጀው አዲስ የሚወጡ ጽሑፎችን ለይሖዋ ምሥክሮች ለማሰራጨት አይደለም። ዓላማው የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጡት ትምህርት ለሰዎች ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ ነው።
በቅርቡ በዚህ ድኅረ ገጽ ላይ አንድ ጠቃሚ መረጃ ተጨምሯል። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ከ220 በሚበልጡ ቋንቋዎች በዚህ ድኅረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል። ከዚህም በላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በሚታተሙባቸው ቋንቋዎች በሙሉ ከጥር 1 እና ከጥር 8, 2004 እትም ጀምሮ በጀርባ ሽፋናቸው ላይ የኢንተርኔት አድራሻችንን ይዘው ይወጣሉ።
በዚህ ዝግጅት ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? ምሥራቹን ለመስማት ፍላጎት ቢኖረውም አንተ የማትችለውን ቋንቋ የሚናገር ሰው ታገኝ ይሆናል። ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል ከሆነ በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት የጀርባ ሽፋን ላይ ያለውን አድራሻ ልታሳየው ትችላለህ። ይህም እርሱ በሚናገረው ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ እስክታመጣለት ድረስ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር በቋንቋው ለማንበብ ያስችለዋል። ወይም ደግሞ እርሱ በሚናገረው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ወይም ቡድን ልታስተላልፈው ትችል ይሆናል።