ሕጋዊ ድረ ገጻችን—እኛንም ሆነ ሌሎችን ለመጥቀም የተዘጋጀ
ኢየሱስ “ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ አዞናል። (ማቴ. 24:14) ‘አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም እንድንችል’ እኛን ለመርዳት watchtower.org፣ jw-media.org እና jw.org የተባሉት ድረ ገጾች አንድ ላይ ተዋህደው jw.org የሚለው ድረ ገጽ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶልናል።—2 ጢሞ. 4:5
“በመላው ምድር”፦ ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ኢንተርኔት ይጠቀማል። ኢንተርኔት ለብዙዎች በተለይም ለወጣቶች ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል። በድረ ገጻችን ላይ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት ይቻላል። በመሆኑም ድረ ገጻችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ከይሖዋ ድርጅት ጋር የሚያስተዋውቃቸው ከመሆኑም በላይ በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በቀላሉ ጥያቄ ማቅረብ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በሆነባቸው የምድር ክፍሎች ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው ያስችላል።
“ለሕዝቦች ሁሉ”፦ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት “ለሕዝቦች ሁሉ” ለመመሥከር ምሥራቹን በተለያዩ ቋንቋዎች መስበክ ይኖርብናል። በመሆኑም jw.org የተባለውን ድረ ገጽ የሚጎበኙ ሰዎች ወደ 400 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች በቀላሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ በሌላ ድረ ገጽ ላይ ከሚያገኙት በእጅጉ የላቀ ነው።
በሚገባ ተጠቀሙበት፦ በአዲስ መልክ የተዘጋጀው jw.org የተባለው ድረ ገጽ ዓላማው ለአዲስ ሰዎች መመሥከር ብቻ አይደለም። የተዘጋጀው የይሖዋ ምሥክሮች እንዲጠቀሙበትም ታስቦ ነው። የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የምትችሉ ከሆነ jw.org ከተባለው ድረ ገጽ ጋር በሚገባ እንድትተዋወቁ እናበረታታችኋለን። ድረ ገጹን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በመቀጠል ቀርበዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሞክሩት
1 የኢንተርኔት ማሰሻውን ከፍተህ አድራሻ በሚጻፍበት ቦታ ላይ www.jw.org ብለህ ጻፍ።
2 በድረ ገጹ አናት ላይ፣ በስተ ግራና በሌሎች ቦታዎች ላይ የሚገኙትን ዋና ዋና ርዕሶችና ሊንኮች በመጫን ከድረ ገጹ ጋር ለመተዋወቅ ሞክር።
3 jw.org የተባለውን ድረ ገጽ እንደ ሞባይል ስልክ ባሉ ኢንተርኔት ለመጠቀም በሚያስችሉ ተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ለመክፈት ሞክር። ገጾቹ በትንሽ ስክሪን መታየት እንዲችሉ ተደርገው ቢዘጋጁም የሚጎድል መረጃ የለም።