ድረ ገጻችንን ለአገልግሎት ተጠቀሙበት—“የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው”
jw.org ላይ በሚገኘው “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች” በሚለው ክፍል ሥር “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” የሚል ዓምድ ይገኛል። በዚህ ዓምድ ሥር የሚገኙትን በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች በሚገባ የምናውቃቸው ከሆነ የምናነጋግረው ሰው ጥያቄ በሚያነሳበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ እንዲያገኝ ወደ ድረ ገጻችን ልንመራው እንችላለን። እነዚህ ጥያቄዎች በአገልግሎት ላይ ውይይት ለመጀመርም ሊረዱን ይችላሉ። በክልላችን ያሉ ሰዎችን ትኩረት የሚስብ አንድ ጥያቄ ከመረጥን በኋላ የምናነጋግረው ሰው በጥያቄው ላይ ሐሳብ እንዲሰጥ መጋበዝ ይቻላል፤ ከዚያም ከjw.org ላይ ያገኘነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ልንነግረው እንችላለን። በመቀጠል ይህን ሐሳብ ያገኘነው ከየት እንደሆነ መንገር ወይም ድረ ገጹ ላይ ማሳየት እንችላለን። ሌላው አማራጭ ደግሞ ግለሰቡ መልሱን ከድረ ገጹ ላይ በቀጥታ እንዲያነብብ ማድረግ ነው። አንዲት የተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚስት በዚህ ረገድ ስኬታማ እንድትሆን የረዳት አንድ አቀራረብ አለ፤ ይህች እህት እንዲህ ትላለች፦ “ብዙ ሰዎች ‘ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መልስ ማወቅ ይፈልጋሉ። የዚህን ጥያቄ መልስ በ51 ሴኮንድ ውስጥ ማወቅ ይፈልጋሉ?” ከዚያም ከድረ ገጹ ላይ ያወረደችውን በድምፅ የተቀዳውን የዚህን ርዕስ ንባብ በስልኳ ታስደምጣቸዋለች። በመጨረሻም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 11ን በማስተዋወቅ ውይይቷን ትደመድማለች።