jw.orgን በአገልግሎታችሁ ላይ ተጠቀሙበት
ድረ ገጻችን ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ለማሰራጨት የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። (ሥራ 1:8) ብዙ ሰዎች jw.org የተባለውን ድረ ገጽ በራሳቸው ሊደርሱበት አይችሉም። ከዚህ ይልቅ ስለ ድረ ገጹ ሊያውቁ የሚችሉት አስፋፊዎች ሲጠቁሟቸው ነው።
አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ አውርዶ የሞባይል ስልኩ ላይ ከጫነ በኋላ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን ቪዲዮ ለሰዎች ማሳየት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤት ወደ ቤት ሲሄድ ለቤቱ ባለቤት እንዲህ ይላል፦ “አስፈላጊ ለሆኑ ሦስት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለሰዎች እያሳየሁ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ፣ ‘ዓለም በችግር የተሞላው ለምንድን ነው? አምላክ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጠው እንዴት ነው? እስከዚያው ድረስ ችግሮቹን መቋቋም የምንችለውስ እንዴት ነው?’ ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።” ከዚያም ቪዲዮውን ማጫወት ይጀምርና የቤቱን ባለቤት ስሜት ለማስተዋል ይሞክራል። ይህ ቪዲዮ በጣም ትኩረት የሚስብ በመሆኑ ብዙዎች ዓይናቸውን ከቪዲዮው ላይ ሳይነቅሉ እስከ መጨረሻው ያዩታል። በመቀጠል ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ ይላል፦ “ቪዲዮው ላይ እንደተመለከቱት መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለመማር በኢንተርኔት አማካኝነት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል። ግን ይህ ትምህርት እንዴት እንደሚካሄድ እኔው ራሴ በአጭሩ ላሳይዎት እችላለሁ።” የቤቱ ባለቤት በዚህ ከተስማማ ጥናቱ የሚካሄደው እንዴት እንደሆነ ምሥራች የተባለውን ብሮሹር ተጠቅሞ ያሳየዋል። የቤቱ ባለቤት ጊዜ ከሌለው ጥናቱ የሚካሄድበትን መንገድ በሌላ ጊዜ ለማሳየት ቀጠሮ ይይዛል። አረፍ ለማለት ወደ ሻይ ቤት ሲገባ ደግሞ አጠገቡ ከተቀመጠው ሰው ጋር ጨዋታ ከጀመረ በኋላ ቪዲዮውን ለማስተዋወቅ ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል። እናንተስ jw.orgን በአገልግሎታችሁ ላይ እየተጠቀማችሁበት ነው?