ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት የበላይ ተመልካች
1 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች በንግግርና በማስተማሩ ሥራ የሚተጋ እንዲሁም አክብሮትና ድጋፍ ልንሰጠው የሚገባ መንፈሳዊ ሽማግሌ ነው። (1 ጢሞ. 5:17) ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው?
2 በመንግሥት አዳራሹ የሚገኘው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ቤተ መጻሕፍት በእርሱ የበላይ ጥበቃ ሥር ነው። ብቃቱን የሚያሟሉ ሁሉ በትምህርት ቤቱ እንዲመዘገቡ ለማበረታታት ይጥራል። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ክፍል ለሚያቀርቡ ሁሉ ሥርዓት ባለው መንገድ ቢያንስ ቢያንስ ከሦስት ሳምንታት በፊት ክፍላቸው ይሰጣቸው ዘንድ ትክክለኛ መዝገብ እንዲኖር ያደርጋል። እያንዳንዱን ተማሪና ችሎታቸውን ከግምት ውስጥ ለማስገባት ጉባኤውን በሚገባ ማወቅ ይኖርበታል። የትምህርት ቤቱን ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚረዳው ሌላ ወንድም ሊኖር ቢችልም ክፍሎቹን በአግባቡ መመደብ ግን የራሱን የበላይ ተመልካቹን ትኩረት የሚሻ ነው።
3 የበላይ ተመልካቹ በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ወቅት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር ይችል ዘንድ የተመደቡትን ክፍሎች በጠቅላላ ጥሩ አድርጎ በማጥናት በየሳምንቱ ትጋት የተሞላበት ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል። እንዲህ ማድረጉ ጉባኤው ትምህርቱን በጉጉት እንዲከታተል ለማድረግ፣ የቀረበው ክፍል በትክክል መሸፈን አለመሸፈኑን ለማረጋገጥና በክለሳ ጥያቄው ውስጥ የሚካተቱትን ነጥቦች ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ያስችለዋል።
4 እያንዳንዱ ተማሪ ክፍሉን ካቀረበ በኋላ የበላይ ተመልካቹ ተማሪውን ያመሰግንና ተማሪው የሠራበት የንግግር ባሕርይ ለምን ጥሩ እንደነበር ወይም ለምን መሻሻል እንደሚያስፈልገው ያብራራል። አንድ ግለሰብ የተሰጠውን ክፍል በመዘጋጀት ረገድ ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነ የበላይ ተመልካቹ ወይም እርሱ የወከለው ሌላ ሰው በግል እርዳታ ሊሰጡት ይችላሉ።
5 ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካቹም ሆነ በእርሱ አመራር ሥር ሆነው ከሚያገለግሉ ሌሎች ምክር ሰጪዎች ትጋት የተሞላበት ሥራ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት እንድንችል አዘውትረን በትምህርት ቤቱ መገኘት ይኖርብናል። በተጨማሪም የሚሰጠንን ክፍል በሚገባ መዘጋጀትና በቀጥታ ለእኛ የሚሰጠንንም ሆነ ለሌሎች የሚሰጣቸውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። በዚህ መንገድ በሕዝብ ፊትም ሆነ ከቤት ወደ ቤት ምሥራቹን የምናቀርብበት ችሎታችን ደረጃ በደረጃ እየተሻሻለ ይሄዳል።—ሥራ 20:20፤ 1 ጢሞ. 4:13, 15