ከ1999 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ተጠቀሙ
1 ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ‘በትምህርቱ ይገረሙ’ ነበር። (ማር. 1:22) ማናችንም ብንሆን የኢየሱስን ያህል የመናገርና የማስተማር ችሎታ ሊኖረን ባይችልም እርሱን ለመኮረጅ መጣር እንችላለን። (ሥራ 4:13) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም መሳተፋችን የመናገርና የማስተማር ችሎታችንን በማሻሻል እዚህ ግብ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል።
2 በ1999 የሚቀርበው ንግግር ቁ. 1 በአመዛኙ በ1997 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ላይ በወጡ ርዕሶች ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ጽሑፉን አስቀድመን ካነበብንና በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ ሲቀርብ ከተከታተልን ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ያለን ግንዛቤ በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል። እነዚህን የማስተማሪያ ንግግሮች እንዲያቀርቡ የሚመደቡት ወንድሞች ጽሑፉ የትምህርቱን ተግባራዊ ጠቀሜታ በማጉላት ትምህርቱን ማራኪና ሕያው በሆነ መንገድ ማቅረብ አለባቸው። ንግግር ቁ. 3 የቤተሰብ ደስታ በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ንግግር ቁ. 4 ደግሞ ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ክፍሎቹን ከመመደቡ በፊት ትምህርቱን በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል። የቤተሰብ ደስታ ከተባለው መጽሐፍ ክፍል እንዲያቀርቡ የሚመደቡት ተማሪዎች በሙሉ በቤተሰብ ሕይወታቸው ምሳሌ የሚሆኑ መሆን ይኖርባቸዋል።
3 የሚሰጣችሁን ምክር በሥራ አውሉ፤ በአግባቡም ተዘጋጁ፦ እያንዳንዱ ሰው በንግግርና በማስተማር ችሎታው ረገድ ተጨማሪ እድገት ማድረግ ይችላል። (1 ጢሞ. 4:13) በመሆኑም ምክር ለማግኘት መጣር ይኖርብናል እንጂ ከምክር ለመሸሽ መፈለግ የለብንም። (ምሳሌ 12:15፤ 19:20) በጉባኤም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ እውነትን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንዲሁ በዘልማድ ማስረጃዎችን ከመዘርዘርና ጥቅሶችን ከማንበብ የበለጠ ነገር ይጠይቃል። የአድማጮቻችንን ልብ መንካትና ለሥራ ማነሳሳት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እውነትን ከልባችን አሳማኝ በሆነ መንገድ በመናገር ነው። (ከሥራ 2:37 ጋር አወዳድር።) በትምህርት ቤቱ የምናገኘው ምክር ይህን ለማድረግ ይረዳናል።
4 ንግግር እንደተሰጣችሁ ወዲያውኑ በትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ላይ በተብራራው መሠረት እንድትሠሩባቸው ስለተሰጧችሁ የንግግር ባሕርያት አስቡ። ከዚህ ቀደም የተሰጣችሁን ምክር በሥራ ለማዋል ምን ማድረግ እንዳለባችሁ አስቡ። በጭብጡ ላይ፣ አስፈላጊ ከሆነ በምትመርጡት መቼት ላይ እንዲሁም በክፍሉ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች እንዴት እንደምትጠቀሙባቸው አሰላስሉ። የምታቀርቡትን ክፍል ሌሎችን ለማስተማርና ለሥራ ለማነሳሳት እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀሙበት እንደምትችሉ አስቡ።—1 ጢሞ. 4:15, 16
5 በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለመመዝገብ እያመነታችሁ ከሆነ ጉዳዩን ከጸለያችሁበት በኋላ የሚሰማችሁን ነገር ለትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች አወያዩት። በ1999 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚቀርበው ፕሮግራም ሁላችንም ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንችላለን።