የምታዩት ውጫዊውን ሁኔታ ብቻ ነውን?
1 ሕዝባዊ አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ወቅት ለአንዳንድ ሰዎች ያለን የመጀመሪያ ግምት ምሥራቹን ለእነሱ ለማካፈል እንድናመነታ ሊያደርገን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ለእውነት ፍላጎት ያሳየ ሰው ለማነጋገር ስትሄዱ ሁልጊዜ በጥርጣሬ ዓይን የሚያያችሁ የሚያስፈራ ጎረቤት ቢኖረው ምን ታደርጋላችሁ? እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማት አንዲት አቅኚ እህት ሰውዬውን ቀርባ ለማነጋገር ወሰነች። ሰላምታ የሰጣት አክብሮት በጎደለው መንገድ ነበር። የሚያስደንቀው ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አዳመጠና በደስታ ለማጥናት ተስማማ። እህት ውጫዊውን ሁኔታ አይታ ባለመፍረዷ ይህ ሰውና ባለቤቱ እውነትን የሚማሩበት መንገድ ተከፍቶላቸዋል።
2 አንዲት ሌላ እህት እርሷ ወደምትሠራበት ሱቅ የሚመጣ ረጅም ፀጉር ያለው ወጣት ውጫዊ ሁኔታ መጀመሪያ ላይ ቢያስፈራትም በመጣ ቁጥር በአጭሩ ትመሠክርለት ነበር። ጥረቷ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ይህ ወጣት የተጠመቀ ምሥክር ሆኗል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ምላሽ አይሰጡም ብለን በችኮላ እንዳንደመድም ምን ሊጠብቀን ይችላል?
3 የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ፦ ኢየሱስ ሕይወቱን ለሁሉም ሰው እንደሚሰጥ ያውቅ ነበር። ስለሆነም የሌሎች ውጫዊ ሁኔታ ወደኋላ እንዲል አላደረገውም። በሥነ ምግባር ረገድ መጥፎ ስም ያተረፉ ሰዎችም ቢሆኑ ተገቢው እርዳታና ማበረታቻ ከተሰጣቸው ሊለወጡ እንደሚችሉ ተገንዝቦ ነበር። (ማቴ. 9:9-13) ሀብታም ድሀ ሳይል ሁሉንም ለመርዳት ሞክሯል። (ማቴ. 11:5፤ ማር. 10:17-22) በአገልግሎት የምናገኛቸው ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን ጥሩ የልብ ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳናስገባ በውጫዊ ሁኔታቸው የምንፈርድ አንሁን። (ማቴ. 7:1፤ ዮሐ. 7:24) የኢየሱስን የላቀ ምሳሌ ለመኮረጅ ምን ሊረዳን ይችላል?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አማካኝነት የአምላክ ቃል የአንድን ሰው አስተሳሰብ፣ አኗኗርና አጠቃላይ ባህርይ የመለወጥ ኃይል እንዳለው ተገንዝበናል። (ኤፌ. 4:22-24፤ ዕብ. 4:12) ስለዚህ እኛ አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ የቀረውን ነገር የሰውን ልብ ለሚያነበው ለይሖዋ ልንተወው ይገባናል።—1 ሳሙ. 16:7፤ ሥራ 10:34, 35
5 ውጫዊው ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን፣ የምሥራቹን ሳናዳላ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ማካፈላችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በሚከናወነው ታላቅ የመከር ሥራ አስተዋፅኦ የሚያበረክት እንዲሆን ምኞታችን ነው።—1 ጢሞ. 2:3, 4