የጥያቄ ሣጥን
◼ የመንግሥት አዳራሹን ማጽዳት የማን ኃላፊነት ነው?
ንጹሕና ማራኪ የሆነ የመንግሥት አዳራሽ በምንሰብከው መልእክት ላይ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል። (ከ1 ጴጥሮስ 2:12 ጋር አወዳድር።) አዳራሹን ንጹሕና ሥርዓታማ ማድረጉ አስፈላጊ ሲሆን በዚህ ረገድ ሁሉም ሰው ድርሻ ሊኖረው ይችላል። ጥቂት ሰዎች ብቻ ሸክሙን ሁሉ እንዲሸከሙ መጠበቅ የለብንም። በአብዛኛው የጽዳት ፕሮግራም የሚወጣው በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ቡድኖች መልክ ሲሆን መጽሐፍ ጥናቱን የሚመራው ወንድም ወይም የእርሱ ረዳት ግንባር ቀደም ሆነው ይገኛሉ። ከአንድ በላይ ጉባኤዎች በሚሰበሰቡባቸው አዳራሾች ሁሉም ጉባኤዎች በጽዳት ሥራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሽማግሌዎች ሁኔታዎችን ያደራጃሉ።
ይህን ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? የመንግሥት አዳራሹ ቋሚ የሆነ ፕሮግራም ተይዞለት መጽዳት አለበት። ለጽዳት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችና መሣሪያዎች መዘጋጀት አለባቸው። በሥራው የሚሳተፉት ወንድሞች መመሪያ ማግኘት እንዲችሉ መሠራት ያለባቸውን ነገሮች የያዘ ዝርዝር አመቺ በሆነ ቦታ መለጠፍ አለበት። ሁለት ዓይነት ዝርዝሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ ለሚደረግ ቀለል ያለ ጽዳት ሲሆን ሌላው ደግሞ የተሟላ ለሆነ ሳምንታዊ ጽዳት ነው። የመጽሐፍ ጥናት መሪው የተሟላ ጽዳት የሚደረግበትን ፕሮግራም ሲያወጣ በቡድኑ ውስጥ ላሉት ሁሉ አመቺ በሆነው ቀንና ሰዓት ላይ ማድረግ አለበት። እንዲሁም ለግቢው ሣር፣ ለአበባዎቹና ለአትክልቶቹ ዘወትር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። የእግር መንገዱና የመኪና ማቆሚያው ቦታ ከወዳደቁ ቆሻሻዎች የጸዳ መሆን ይገባዋል። በየዓመቱ የተሟላ ጽዳት መደረግ ያለበት ሲሆን ምናልባትም ይህ ከመታሰቢያው በዓል በፊት ሊደረግ ይችላል። ይህ ጽዳት መስተዋቶቹንና ግድግዳውን ማጠብ፣ ምንጣፉንና መጋረጃዎቹን ማጠብን ሊያጠቃልል ይችላል።
እርግጥ ሁላችንም አዳራሹ ውስጥም ሆነ ውጪ ማስቲካና ሌሎች ቆሻሻዎች ባለመጣል ሥራውን ማቅለል እንችላለን። መጸዳጃ ቤቱን ከተጠቀምን በኋላ ከእኛ ቀጥሎ ለሚገባው ሰው አጽድተን ልንተውለት እንችላለን። ዕቃ ላለመስበር ወይም ላለማበላሸት ጥንቃቄ አድርጉ። ምንጣፍ ላይ የቀሩ ምልክቶችን፣ የተበላሹ ወንበሮችን፣ የቧንቧ ብልሽቶችን፣ የተቃጠሉ አንፑሎችን እና ወዘተ ተመልክታችሁ የመንግሥት አዳራሽ ጥገናን በተመለከተ ኃላፊነት ላለው ወንድም ወዲያውኑ አሳውቁ።
ሁላችንም ድርሻችንን ለመወጣት ፈቃደኞች እንሁን። እንዲህ ማድረጋችን ማራኪ የአምልኮ ቤት ያስገኛል፤ እንዲሁም ይሖዋ አምላክን የሚያስከብር ንጹሕ ሕዝብ በመሆናችን ተለይተን እንድንታወቅ ያደርገናል።—1 ጴጥ. 1:16