የይሖዋን ቃል በየዕለቱ መርምሩ!
1 በእያንዳንዱ ዕለት አዳዲስ የእምነት ፈተና ይገጥማችኋል። ምናልባት አንድ የምታውቁት ዓለማዊ ሰው በፆታ ስሜት አጉል ይቀራረባችሁ ይሆናል። አስተማሪያችሁ የሕይወት ግባችሁ ትምህርት ብቻ እንዲሆን ወይም አሠሪያችሁ ተጨማሪ ረጅም ሰዓት እንድትሠሩ ይፈልግ ይሆናል። ጤንነታችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ይሄድ ይሆናል። ይሖዋ እነዚህን የመሰሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስፈልጋችሁን ጥበብ ሊሰጣችሁ ዝግጁ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስና ለጥቅሱ የተሰጠውን ሃሳብ መመርመር የይሖዋን ቃል አዘውትራችሁ የምትመገቡበት አንዱ መንገድ ነው። በዚህ ዝግጅት እየተጠቀማችሁ ነውን?
2 አስፈላጊው እርዳታ አለላችሁ፦ ኢሳይያስ 30:20 [NW ] ይሖዋ “ታላቅ አስተማሪ” እንደሆነና የአምላክ ሕዝቦች ለእርዳታ ፊታቸውን ወደ እርሱ እንደሚያዞሩ ይገልጻል። እምነታችሁን የሚፈታተኑትን ነገሮች ለመጋፈጥ እንድትችሉ የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ይሰጣችኋል። እንዴት? ከዚያ ቀጥሎ ያለው ቁጥር “ጆሮዎችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ” ይላል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ‘ቃሉን’ የሚያሰማው በቅዱሳን ጽሑፎችና “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) ባለፉት ዓመታት የወጡት የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ብቻ እንኳን ሁሉንም የክርስቲያናዊ ኑሮ ዘርፍ የሚዳስሱና ጥበብ የሞላባቸው ናቸው። ቅዱሳን ጽሑፎችን መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ የተጠቀሱትን መከለስ ማንኛውንም ዓይነት ፈተና በመቋቋም ረገድ ጠቀሜታ ያለው እውቀት ለማካበት ይረዳችኋል።—ኢሳ. 48:17
3 ጊዜ መድቡለት:- አንዲት እናት ጧት ጧት ሥራ የሚበዛባት ቢሆንም ወንድ ልጅዋ ቁርሱን በሚበላበት ጊዜ ሥራዬ ብላ ሁልጊዜ የዕለቱን ጥቅስና ሐሳቡን እያነበበች ውይይት ያደርጋሉ። ልጁ ሁልጊዜ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊት የሚሰማቸው የመጨረሻ ቃላት የዕለት ጥቅሱና የእናቱ ጸሎቶች ናቸው። ይህም የፆታ ማባበያዎችን እንዲቋቋም፣ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነቱን እንዲጠብቅ፣ ለተማሪዎችም ሆነ ለአስተማሪዎች በድፍረት እንዲመሰክር አጠንክሮታል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለው ምስክር እርሱ ብቻ ቢሆንም ፈጽሞ ብቸኝነት ተሰምቶት አያውቅም።
4 መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ቃሉ ዘወር በሉ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ይሖዋ እንደምትተማመኑበት ወዳጅ ዕውን ይሆንላችኋል። በእያንዳንዱ ዕለት የእርሱን እርዳታ ለማግኘት ጣሩ! በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ የአምላክን ቃል ከሚመረምሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር የእናንተም ‘ዓይኖች ታላቁን አስተማሪያችሁን እንዲያዩ’ ምኞታችን ነው።