የቤተሰብ ፕሮግራም ይኑራችሁ—የዕለቱን ጥቅስ ለመመርመር
1 አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በየዕለቱ ለልጆቻቸው ጥሩ ምግብ ለማቅረብ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ከአምላክ ቃል የሚገኘውን መንፈሳዊ ምግብ ለልጆቻቸው ማቅረብ ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። (ማቴ. 4:4) ልጆቻችሁ ጥሩ መንፈሳዊ ፍላጎት ኖሯቸው ‘ወደ ድነት እንዲያድጉ’ መርዳት የምትችሉበት አንዱ መንገድ የዕለቱን ጥቅስ በቤተሰብ ደረጃ በየቀኑ ለማንበብና በቀረበው ሐሳብ ላይ ለመወያየት ጊዜ በመመደብ ነው። (1 ጴጥ. 2:2) ታዲያ የዕለቱን ጥቅስ በቤተሰብ ደረጃ መቼ መወያየት ትችላላችሁ?
2 በምግብ ሰዓት:- በማለዳ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ውይይት ማድረጋችሁ ቤተሰባችሁ ቀኑን ሙሉ ይሖዋን እንዲያስብ ለማድረግ ይረዳል። (መዝ. 16:8) አንዲት እናት ልጇ ቁርስ በሚበላበት ወቅት የዕለቱን ጥቅስና ሐሳብ በማንበብ እንዲወያዩበትና ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዱ በፊት አብረው እንዲጸልዩ ለማድረግ ወሰነች። ይህም ከብሔራዊ ስሜት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲያጋጥመው በአቋሙ እንዲጸና፣ በጾታ ማባበያዎች እንዳይሸነፍ እንዲሁም ለተማሪዎችም ሆነ ለአስተማሪዎች በድፍረት እንዲመሰክር አስችሎታል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለው የይሖዋ ምሥክር እርሱ ብቻ ቢሆንም ፈጽሞ ብቸኝነት ተሰምቶት አያውቅም።
3 በዕለቱ ጥቅስ ላይ ለመወያየት የጠዋቱ ጊዜ አመቺ ካልሆነ በቀኑ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ላይ ወይም ደግሞ ማታ በእራት ሰዓት መላው ቤተሰብ በተገኘበት ማድረግ ትችሉ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንዶች በመስክ ላይ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች እንዲሁም በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸው ያጋጠሟቸውን ትኩረት የሚስቡ ነጥቦች በማንሳት ይወያያሉ። ብዙዎች በእራት ሰዓት ላይ ሰብሰብ ብለው ያሳለፏቸውን እነዚህን አስደሳች ጊዜያት ፈጽሞ አይረሷቸውም።
4 ምሽት ላይ:- አንዳንድ ቤተሰቦች ማታ ከመተኛታቸው በፊት በዕለቱ ጥቅስ ላይ ውይይት ማድረጉን የተሻለ ሆኖ አግኝተውታል። ይህ ጊዜ አንድ ላይ ለመጸለይም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ልጆቻችሁ በየቀኑ ስለ ይሖዋ ስትናገሩና ስትጸልዩ ሲሰሙ ይሖዋ እውን ይሆንላቸዋል።
5 ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር የተባለውን ቡክሌት በመጠቀም እውነትን በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ለመትከል የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንዲባርክላችሁ እንመኛለን።