አዘውታሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁን?
1 በነሐሴ 1999 ኢትዮጵያ 6,118 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ማግኘቷን ስንሰማ ሁላችንም እጅግ ተደስተናል። እንዴት ያለ ቁርጠኝነት የታከለበት የጋራ ጥረት ነበር! ሆኖም በቀጣዮቹ ወራት የነበረው የአስፋፊዎች አማካይ ቁጥር ወደ 5,791 ዝቅ ማለቱ ከእነዚህ አስፋፊዎች መካከል ጥቂቶቹ አዘውታሪ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን ረገድ ችግር እንደነበረባቸው የሚያሳይ ነው። የተወሰኑ አስፋፊዎች በእያንዳንዱ ወር አገልግሎታቸውን ሪፖርት አላደረጉም ማለት ነው። ቀጥሎ የቀረበው ማበረታቻ ለዚህ ችግር መፍትሄ ያስገኛል ብለን እናምናለን።
2 ያገኛችሁትን መብት አድንቁ:- ላገኘነው የመንግሥቱን ምሥራች ለሌሎች የማካፈል መብት ጥልቅ የሆነ አድናቆት ሊኖረን ይገባል። ይህ ሥራ የይሖዋን ልብ ደስ ከማሰኘቱም በላይ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሕይወትን መንገድ እንዲማሩ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 27:11፤ 1 ጢሞ. 4:16) አዘውትረን ለሌሎች መመሥከራችን በአገልግሎቱ ያለንን ተሞክሮ ከማዳበሩም በተጨማሪ የደስታና የእርካታ ስሜት ያስገኝልናል።
3 አገልግሎታችሁን ሪፖርት አድርጉ:- አንዳንዶች በአገልግሎት ተሳትፎ ቢያደርጉም በጊዜው ሪፖርት ማድረግን ቸል ይላሉ። ያደረግሁት ጥረት በጣም አነስተኛ ስለሆነ ሪፖርት ተብሎ የሚመለስ አይደለም የሚል ስሜት በፍጹም ሊያድርብን አይገባም። (ከማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።) ምንም ይሁን ምን ያከናወንነውን አገልግሎት ሪፖርት ማድረግ አለብን! ሪፖርታችንን በሰዓቱ ለመመለስ የተለያዩ ዘዴዎች መጠቀም እንችላለን። በአገልግሎት ያሳለፍነውን ሰዓት ቤታችን ውስጥ ለመመዝገብ እንደ ቀን መቁጠሪያ ያሉትን ነገሮች መጠቀማችን በየወሩ መጨረሻ ላይ ሳንዘገይ ትክክለኛ የአገልግሎት ሪፖርታችንን እንድንመልስ ዘወትር የሚያስታውሰን ይሆናል።
4 አስፈላጊውን እርዳታ ስጡ:- አንዳንድ አስፋፊዎች በአገልግሎቱ ቋሚ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለመርዳት ታስበው በጉባኤው ውስጥ የተደረጉት ዝግጅቶች መሻሻል ያስፈልጋቸው ይሆናል። የጉባኤው ጸሐፊና የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች ልምድ ያላቸው አስፋፊዎች እርዳታ እንዲያበረክቱ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ያልተጠመቁ አስፋፊዎች የሆኑ ልጆች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ካሏችሁ የአገልግሎት ሪፖርታቸውን በየወሩ እንዲመልሱ አሰልጥኗቸው።
5 “በይሖዋ አገልግሎት ረጅም ዘመን በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ” በሚል ርዕስ ጥቅምት 1, 1997 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን የሕይወት ታሪክ አስታውሱ። የኖርዌይ ተወላጅ የሆነችው እህት ኦቲሊ ሚድለን በ1921 ከመጠመቋ በፊት አዘውታሪ የምሥራቹ አስፋፊ ሆነች። ሰባ ስድስት ዓመታት ካለፉ በኋላ ማለትም በ99 ዓመቷ “አሁንም አዘውታሪ አስፋፊ መሆን መቻሌ ያስደስተኛል” በማለት ተናግራለች። ይህ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ሊኮርጁት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ዝንባሌ ነው!