በነሐሴ ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ማድረግ ይቻል ይሆን?
1 በመላው ምድር ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ከፍተኛ የሥራ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ይህ የያዝነው የአገልግሎት ዓመት በነሐሴ ወር ይጠናቀቃል። በመካከላችን የሚገኙ ብዙዎች በቅዱስ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እንዲችሉ የነሐሴ ወር ልዩ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። በዚህ ወር በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዕረፍት ጊዜያቸውን እንዲሁም ሌሎች በወሩ ውስጥ ያሉትን አምስት ሳምንታት ጥሩ አድርገው እንደሚጠቀሙበት የተረጋገጠ ነው። ማራኪ የሆኑ ብሮሹሮቻችንን በማበርከቱ ሥራ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። በመስኩ የምናገኛቸው ሰዎች የሰላም ጉዳይ ትኩረታቸውን ስለሚስበው የአምላክ መንግሥት ለምድራችን ዘላቂ የሆነ ሰላምና ደስታ የሚያመጣ መሆኑን ልንነግራቸው እንችላለን። የዚህን ወር ሪፖርት ለመስማት ሁላችንም በጉጉት እንጠብቃለን።
2 ባለፈው ነሐሴ 5,649 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት ተደርጎ ነበር። በዚያን ጊዜ የተደረገ ቆጠራ በመላው አገሪቷ 5,733 የሚያክሉ አስፋፊዎች እንደነበሩ ያሳይ ነበር። ሆኖም በነሐሴ ወር ሪፖርት ያደረጉት ሁሉም አልነበሩም። አንዳንዶቹ አገልግለው ሊሆን ይችላል ሆኖም ሪፖርታቸውን በጊዜው የመመለሱን ጉዳይ በቁም ነገር አልተመለከቱትም። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ብዙ ሰዎች ይሖዋን ማገልገል የጀመሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል። እንዲያውም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከ6,000 በላይ ወደሚሆኑ አስፋፊዎች ደርሰን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አሁን ትልቁ ጥያቄ በነሐሴ ወር ሁሉም በንቃት በአገልግሎት ተካፍለው ሪፖርታቸውን በታማኝነት ይመልሳሉ ወይ? የሚለው ነው። እንዲህ ከተደረገ በእርግጥም ነሐሴን ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወር ማድረግ ይቻላል!
3 ውጤቱ በአብዛኛው እኛ በምናደርገው ጥረት ላይ የተመካ ነው። ሆኖም የይሖዋ በረከት እንዲታከልበት መጸለይ ይኖርብናል። በቅርቡ ከዓለም የተለዩ ስለመሆን፣ በፍቅር እርስ በእርስ ስለመተሳሰር፣ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የአገልግሎት ክልሎችን ስለመሸፈን፣ የመንገድ ላይ ምሥክርነት በሚሰጥበት ጊዜ በሰዎች ላይ ትኩረት ስለማድረግና በማንኛውም ጊዜና ቦታ ብርሃናችንን ስለማብራት ወቅታዊ የሆነ ምክር ተሰጥቶናል። እነዚህን ምክሮች ይበልጥ ተግባራዊ ባደረግን መጠን ይሖዋም አብዝቶ ይባርከናል። ነሐሴን ልዩ የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወር ለማድረግ እንዲቻል ቀደም ብላችሁ ወሩ እንደገባ ባለው በመጀመሪያው ሳምንት በአገልግሎት ለመካፈል እቅድ አውጡ! ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን በምሥክርነቱ ያሳለፍነውን ጊዜ ለመመዝገብ የሚያስችል ማስታወሻ ደብተር ማዘጋጀቱ ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው። በወሩ መጨረሻ ላይ እነዚህ ትንሽ የሚመስሉ ደቂቃዎች ከፍ ያለ ሰዓት ሊያስገኙ ይችላሉ።
4 በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች የእያንዳንዱን አስፋፊ ሪፖርት በማሰባሰብ ጸሐፊውን ሊያግዙት ይችላሉ። ባለፉት ወራት ያልተመለሱ የዘገዩ ሪፖርቶችንም መሰብሰብ ይቻላል። ከጉባኤው ሪፖርት ትንሽ ዝቅ ብሎ ካለፉት ወራት የተሰበሰቡት የሪፖርቶች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ መጥቀሱ ጥሩ ነው። ሆኖም ሁሉም አስፋፊዎች የነሐሴ ወር የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሳይዘነጉ ቢመልሱ ምንኛ አበረታች ይሆናል! ስንት የአስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር እናስመዘግብ ይሆን? ወደ 6,000 ምን ያህል እንቃረብ ይሆን? ወይስ ይህን ቁጥር እናልፍ ይሆን?
5 በነሐሴ ወር እንደ አንድ አስፋፊ መቆጠር ትችሉ ዘንድ በወሩ መጨረሻ ላይ የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችሁን ሳትዘገዩ መመለሳችሁን ፈጽሞ አትዘንጉ።
6 መብቱን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት፦ አገልግሎት “መልካም ዐደራ” ነው። (2 ጢሞ. 1:14 የ1980 ትርጉም) ምሥራቹን እንድንሰብክ የተሰጠንን መብት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (1 ተሰ. 2:4) ይሖዋ ያደረገልንን ነገሮች መለስ ብለን ስናስብ ዓመቱን በሙሉ በዚህ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ሥራ መካፈላችንን እንድንቀጥል ልንገፋፋ ይገባል። አዘውትረን እንዳንሰብክ ምንም ነገር እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። ነሐሴን በይሖዋ አገልግሎት ልዩ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ወር ለማድረግና ከዚያ በኋላ ባሉት ወራትም ስለ እርሱ መመሥከራችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን! በይሖዋ አገልግሎት አዘውትረን መካፈላችን በመንፈሳዊ ጤናሞች እንድንሆንና ደስታችን የበለጠ ከፍ እንዲል ያደርግልናል። በተጨማሪም የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል።—መዝ. 34:1፤ ምሳሌ 27:11