ነሐሴ ልዩ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ታሪካዊ ወር እንደሚሆን ይጠበቃል!
በዓለም ዙሪያ አዲስ ትራክት ይሰራጫል
1. የአምላክ መንግሥት የተቋቋመበት 100ኛ ዓመት እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት በዓለም ዙሪያ ምን ልዩ ዘመቻ ይካሄዳል?
1 የአምላክ መንግሥት የተቋቋመበት 100ኛ ዓመት እየተቃረበ ነው። በዚህ ወቅት ይሖዋን ለማክበር የሚያስችል ልዩ ዘመቻ መዘጋጀቱ ምንኛ የተገባ ነው! በነሐሴ ወር በአእምሯችን ለሚጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ትራክት በዓለም ዙሪያ እናሰራጫለን። ይህ ትራክት ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር እንዲሉ የሚያበረታታ ሲሆን በዚህ ረገድ jw.org የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነም ያብራራል።
2. “በታላቅ ድምፅ” ለይሖዋ ምስጋና በሚቀርብበት በነሐሴ ወር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
2 ታላቅ የምስጋና ድምፅ፦ በነሐሴ ወር ረዳት አቅኚ በመሆን አገልግሎታቸውን ማስፋት ለሚፈልጉ አስፋፊዎች ልዩ ዝግጅት ተደርጓል። በዚህ ወር፣ የተጠመቁ አስፋፊዎች 30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ መሆን ይችላሉ። ነሐሴ አምስት ዓርብ፣ አምስት ቅዳሜ እና አምስት እሁድ ስላለው በርካታ ሠራተኞችና ተማሪዎች ረዳት አቅኚ ሆነው ለማገልገል አመቺ ይሆንላቸዋል። አስፋፊ መሆን የሚፈልግ እድገት እያደረገ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አሊያም ልጅ ካላችሁ አሁኑኑ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪውን አነጋግሩት። በዚህ ታሪካዊ ወር አዳዲሶች አብረውን በአገልግሎት መካፈል ቢጀምሩ ምንኛ የሚያበረታታ ይሆናል! የነሐሴ ወር በርካታ የዘወትር አቅኚዎች የሰዓት ግባቸው ላይ ከደረሱ በኋላ እረፍት የሚያደርጉበት ወቅት ቢሆንም በዚህ ልዩ ዘመቻ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ሲሉ በፕሮግራማቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይችላሉ። “በታላቅ ድምፅ” ለይሖዋ ምስጋና በሚቀርብበት በነሐሴ ወር ቤተሰቦች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ከአሁኑ መወያየታቸው አስፈላጊ ነው።—ዕዝራ 3:11፤ ምሳሌ 15:22
3. ከዚህ ልዩ ዘመቻ ምን እንጠብቃለን?
3 ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የሆኑ ዘመቻዎችን ያደረግን ቢሆንም ይህ ዘመቻ ታሪካዊ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። በነሐሴ ወር በሰዓት እንዲሁም በአስፋፊና በረዳት አቅኚ ቁጥር ረገድ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ማስመዝገብ እንችል ይሆን? የ2014 የአገልግሎት ዓመት መጨረሻ በሆነው በነሐሴ ወር ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ በዓለም ዙሪያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲባርከውና ይህ ወር እስከ ዛሬ ምሥክርነት ከተሰጠባቸው ወራት ሁሉ የላቀ እንዲሆን ምኞታችን ነው!—ማቴ. 24:14