ቀኑን ሙሉ ይሖዋን ፍሩ
1 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” (መዝ. 111:10) ይሖዋን መፍራት ጥሩ ሥራዎችን እንድንሠራ ያነሳሳናል፤ እንዲሁም ከክፋት እንድንርቅ ይረዳናል። (ምሳሌ 16:6) ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ፈጣሪያችንን እንዳናሳዝን እንዲሁም ትእዛዙን እንዳንጥስ የሚገፋፋ ሲሆን ለእሱ ጥልቅ አክብሮት እንዳለን የሚያሳይ ነው። ይህ ልናዳብረውና ቀኑን ሙሉ እንዲታይ ልናደርገው የሚገባ ባሕርይ ነው።—ምሳሌ 8:13
2 የሰይጣን ዓለም መንፈስ የክፋት መንገዶቹን እንድንከተል በየዕለቱ ከፍተኛ ግፊት ያሳድርብናል። (ኤፌ. 6:11, 12) ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ለኃጢአት ተገዢ ስለሆነ ክፉ ወደ መሥራት ማዘንበል ይቀናዋል። (ገላ. 5:17) ስለዚህ የይሖዋን ትእዛዛት ማክበር፣ ደስተኛ መሆንና ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ቀኑን ሙሉ ይሖዋን መፍራት ይኖርብናል።—ዘዳ. 10:12, 13
3 በዚህ በምንኖርበት ዘመን እርስ በርስ ለመበረታታት ‘ከበፊቱ አብልጠን’ መሰብሰብ እንዳለብን በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ በጥብቅ ተመክረናል። እነዚህን የመጨረሻ ቀናት በሕይወት ማለፍ የምንፈልግ ከሆነ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን ወሳኝ ነው። አምላክን እንዳናሳዝን መፍራታችን በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝና ስብሰባዎች ያላቸውን ጠቀሜታ ከፍ አድርገን እንድንመለከት ይገፋፋናል። አምላክን የሚፈሩ ሰዎች በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መካፈልን ቅዱስ መብት አድርገው ይመለከቱታል።
4 አምላክን እንደምንፈራ የምናሳይበት ሌላው መንገድ የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ መፈጸም ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሥራ 10:42) የስብከቱ ሥራችን ዋነኛ ዓላማ ሌሎች ሰዎች ይሖዋን መፍራት እንዲማሩና ለፈቃዱ እንዲገዙ መርዳት ነው። ይህን ከግብ የምናደርሰው ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር በመጣጣርና ከዚያም ሌሎች የአምላክን ትእዛዛት በሙሉ እንዲያውቁ በማስተማር ነው። እንዲህ በማድረግ ይሖዋን እንደምንፈራና ጎረቤቶቻችንን እንደምናፈቅር እናሳያለን።—ማቴ. 22:37-39
5 አምላካዊ ፍርሃት የሌላቸው ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ተገቢውን አድናቆት ለማዳበር ፈቃደኛ የማይሆኑ ሲሆን ለዓለም መርዘኛ አየር ወይም የአእምሮ ዝንባሌ ተጋልጠዋል። (ኤፌ. 2:2) ቁርጥ ውሳኔያችን ‘በአምላካዊ አክብሮትና ፍርሃት እሱን ደስ ማሰኘት’ ይሁን። (ዕብ. 12:28) እንዲህ በማድረግ ቀኑን ሙሉ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች ከሚያጭዱት በረከት ተካፋይ እንሆናለን።