“ብርሃናችሁ ይብራ”
1 በዙሪያችን ያለው ዓለም በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ይገኛል። የእውነት ብርሃን ‘ፍሬ የሌላቸው የጨለማ ሥራዎች’ እንዲጋለጡ ስለሚያደርግ ከእነዚህ አደገኛ እንቅፋቶች መሸሽ ይቻላል። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” በማለት አጥብቆ አሳስቧል።—ኤፌ. 5:8-11
2 “የብርሃኑ ፍሬ” ከዚህ ዓለም ጨለማ ጋር ፈጽሞ የሚገጥም አይደለም። (ኤፌ. 5:9) ይህንን ፍሬ ለማፍራት በክርስቲያናዊ አኗኗር ግሩም ምሳሌዎች በመሆን የኢየሱስን ሞገስ የምናገኝ ዓይነት ሰዎች መሆን አለብን። በተጨማሪም በሙሉ ልብ፣ በቅንነትና በጋለ ስሜት ከእውነት ጎን እንደተሰለፍን ማሳየትም ይገባናል። ይህ ፍሬ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንና በአገልግሎታችን በግልጥ መታየት አለበት።
3 በማንኛውም አጋጣሚ ብርሃናችሁ ይብራ:- ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 5:16) የኢየሱስን አርዓያ በመከተል ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ዓላማው በመስበክ የይሖዋን ብርሃን እናንጸባርቃለን። ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ እንዲሁም በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ ለጎረቤቶቻችን ወይም አጋጣሚ በምናገኝበት በማንኛውም ስፍራ እውነትን ስናሰራጭ ብርሃን አብሪዎች እንሆናለን።—ፊልጵ. 2:15
4 ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች ይህን ብርሃን እንደሚጠሉ ተናግሯል። (ዮሐ. 3:20) ስለዚህ አብዛኞቹ ሰዎች “የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን” እንዲያበራላቸው አለመፈለጋቸው ተስፋ አያስቆርጠንም። (2 ቆሮ. 4:4) ይሖዋ የሰዎችን ልብ ስለሚያነብ ክፉ አድራጊዎች በሕዝቡ መካከል እንዲኖሩ አይፈልግም።
5 የይሖዋን መንገድ ስንከተልና በመንፈሳዊው ብርሃን መመላለሳችንን ስንቀጥል ብርሃኑን ለሌሎች ማንጸባረቅ እንችላለን። አኗኗራችንን በማየት ‘የሕይወት ብርሃን እንዳለን’ ከተገነዘቡ እነሱም ብርሃን አብሪዎች ለመሆን አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ይነሳሱ ይሆናል።—ዮሐ. 8:12
6 ብርሃናችንን በማብራት ለፈጣሪያችን ውዳሴ እናመጣለን፤ እንዲሁም ልበ ቅን ሰዎች እሱን እንዲያውቁና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው እንረዳቸዋለን። (1 ጴጥ. 2:12) ብርሃናችንን ሌሎች ሰዎች ከመንፈሳዊ ጨለማ ወጥተው የብርሃን ሥራዎች እንዲያደርጉ ለመርዳት እንጠቀምበት።