‘ብርሃናችሁ ይብራ’
1. ለሰዎች ምን ነገር የማካፈል መብት አግኝተናል?
1 ጎህ ከሚቀድበት ጊዜ አንስቶ ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ የሚታየው ደስ የሚል ብርሃን ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣል። ይሁንና ኢየሱስ ሌላ ዓይነት ብርሃን ይኸውም “የሕይወት ብርሃን” እንዲኖራቸው ለደቀ መዛሙርቱ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር። (ዮሐ. 8:12) እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ብርሃን ማግኘት ልዩ መብት ሲሆን ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። ኢየሱስ “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል፤ ይህን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ ሌሎችም ከብርሃኑ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል። (ማቴ. 5:16) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም ድቅድቅ በሆነ መንፈሳዊ ጨለማ ስለተዋጠ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይህን ብርሃን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል! ታዲያ እኛም እንደ ክርስቶስ ብርሃናችንን ማብራት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ኢየሱስ መንፈሳዊ ብርሃንን ለሰዎች ማካፈል አስፈላጊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
2 ምሥራቹን በመስበክ፦ ኢየሱስ ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ጥሪቱን ተጠቅሞ ሰዎች ሊገኙበት በሚችሉበት ቦታ ሁሉ ማለትም በቤታቸው፣ በአደባባይና በተራሮች ላይ በማስተማር የእውነትን ብርሃን እንዲያገኙ አድርጓል። ኢየሱስ እውነተኛውን መንፈሳዊ ብርሃን ለሰዎች ማዳረስ ዘላቂ ጠቀሜታ እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 12:46) እንዲያውም ብዙ ሰዎች ይህን ብርሃን እንዲያገኙ ሲል ደቀ መዛሙርቱ “የዓለም ብርሃን” እንዲሆኑ አሠልጥኗቸዋል። (ማቴ. 5:14) በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ለሰዎች መልካም በማድረግና መንፈሳዊ እውነቶችን በማካፈል ብርሃናቸውን ፈንጥቀዋል።
3. ለእውነት ብርሃን ልባዊ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
3 የአምላክ ሕዝቦች ‘የብርሃን ልጆች ሆነው የመመላለስ’ ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ስለሚመለከቱት ሰዎች ሊገኙበት በሚችሉበት ቦታ ሁሉ ይሰብካሉ። (ኤፌ. 5:8) በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ውስጥ በእረፍት ሰዓት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ሰዎች ሊያዩን በሚችሉበት ቦታ ሆኖ ማንበብ እንኳ መንፈሳዊ ውይይት ለማድረግ በር ሊከፍት ይችላል። አንዲት ወጣት እህት በዚህ ዘዴ በመጠቀም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ብሎም ለ12 የክፍሏ ተማሪዎች መጻሕፍትን ማበርከት ችላለች!
4. ‘ብርሃናችንን ለማብራት’ የሚረዳን ሌላው መንገድ መልካም ምግባር ማሳየት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 መልካም ሥራዎችን በመሥራት፦ ብርሃናችንን ማብራት የምንችልበት ሌላው መንገድ በዕለታዊ እንቅስቃሴያችን ጥሩ ምግባር ማሳየት ነው። (ኤፌ. 5:9) በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች ክርስቲያናዊ ምግባር የምናሳይ ከሆነ ሰዎች በቀላሉ ያስተውሉታል፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለእነሱ ለማካፈል አጋጣሚ ይከፍትልናል። (1 ጴጥ. 2:12) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የአምስት ዓመት ልጅ ጥሩ ጠባይ በማሳየቱ አስተማሪዋ ለወላጆቹ ስልክ በመደወል አድናቆቷን ገልጻለች። “እንዲህ ያለ ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ያለው ልጅ ፈጽሞ አይቼ አላውቅም!” በማለት ተናግራለች። በእርግጥም አገልግሎታችንና መልካም ምግባራችን ሰዎችን ወደ “ሕይወት ብርሃን” እንዲሳቡ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ለአምላካችን ክብር ያመጣል።