የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 12/95 ገጽ 3-4
  • ብርሃናችን ሳያቋርጥ እንዲበራ ማድረግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብርሃናችን ሳያቋርጥ እንዲበራ ማድረግ
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ብርሃናችሁ ይብራ’
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2011
  • “ብርሃናችሁ ይብራ”
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2001
  • ይሖዋ እንዲከበር ‘ብርሃናችሁ ይብራ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2018
  • የዓለምን ብርሃን ተከተሉ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
km 12/95 ገጽ 3-4

ብርሃናችን ሳያቋርጥ እንዲበራ ማድረግ

1 ብርሃን ምንድን ነው? መዝገበ ቃላት “ለማየት የሚያስችል ነገር” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። ሰዎች በቴክኖሎጂ ረገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርሱም እንኳ በኢዮብ 38:24 ላይ ተመዝግቦ ለሚገኘው ይሖዋ ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን የተሟላ መልስ አላገኙም። ያለ ብርሃን መኖር እንችላለንን? አንችልም። ብርሃን ለማየት አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊ ሁኔታ “እግዚአብሔር ብርሃን” እንደሆነ ይነግረናል። (1 ዮሐ. 1:5) ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ የተመካው “ብርሃን በሚሰጠን” አምላክ ላይ ነው።— መዝ. 118:27 አዓት

2 ይህ ሐቅ በሰብዓዊ ሁኔታ የሚሠራ ቢሆንም በመንፈሳዊ ረገድ ያለው ተፈጻሚነት ይበልጥ የጎላ ነው። የሐሰት ሃይማኖት ብዙ ሰዎችን መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ከትቶ ‘እንደ እውር እንዲደናበሩ’ በማድረግ በተሳሳተ አቅጣጫ መርቷቸዋል። (ኢሳ. 59:9, 10 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ ተወዳዳሪ በሌለው ፍቅሩና ርኅራኄው ተገፋፍቶ ‘ብርሃኑንና እውነቱን ይልካል።’ (መዝ. 43:3) ለዚህ ብርሃን አድናቆት ያላቸው ቃል በቃል በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ” በመምጣት ምላሽ ሰጥተዋል።— 1 ጴጥ. 2:9

3 ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ብርሃን ወደ ዓለም በማምጣት በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል። “በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 12:46) ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ያለውን ጥሪት የእውነት ብርሃን ለሁሉ እንዲበራ በማድረጉ ሥራ ላይ አውሎት ነበር። በእያንዳንዱ ከተማና መንደር ውስጥ ያሉ ሰዎችን በማስተማር ትውልድ አገሩን ከጫፍ እስከ ጫፍ አዳርሷል። ከሁሉም አቅጣጫ የማያባራ ስደት ቢደርስበትም የእውነትን ብርሃን የማብራት ተልዕኮውን ከማከናወን ወደ ኋላ አላለም።

4 ኢየሱስ በአእምሮው አንድ ልዩ ግብ ይዞ ደቀ መዛሙርት በመምረጥ፣ በማሠልጠንና በማደራጀት ሥራ ላይ አተኩሮ ነበር። በማቴዎስ 5:14-16 ላይ ኢየሱስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን መመሪያ እናነባለን። የእውነትን ብርሃን በስፋት በማብራት ልክ እንደ ኢየሱስ “በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች መሆን” ነበረባቸው። (ፊልጵ. 2:15 አዓት) ደቀ መዛሙርቱ ይህንን ኃላፊነት የሕይወታቸው ዋንኛ ዓላማ አድርገው በመመልከት በደስታ ተቀብለውት ነበር። ጳውሎስ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ምሥራቹ ‘ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኳል’ ብሎ ለመናገር ችሏል። (ቆላ. 1:23) ይህን ታላቅ ሥራ ለማከናወን መላው የክርስቲያን ጉባኤ አንድ ላይ ተባብሮ ነበር።

5 እኛም በዛሬው ጊዜ ‘የጨለማውን ሥራ አውጥተው ከጣሉት’ ጋር መቀላቀል በመቻላችን አመስጋኞች መሆን አለብን። (ሮሜ 13:12, 13) ኢየሱስና በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ትተው ያለፉትን ምሳሌ በመከተል አድናቆታችንን ልናሳይ እንችላለን። ሰዎች እውነትን የመስማታቸው አስፈላጊነት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የአሁኑን ያህል አጣዳፊና አሳሳቢ ሆኖ አያውቅም። በአጣዳፊነቱና በሚያስገኛቸው ብዙ ጥቅሞች ረገድ ከዚህ ሥራ ጋር የሚወዳደር ሌላ ሥራ የለም።

6 ብርሃን አብሪዎች በመሆን ልናበራ የምንችለው እንዴት ነው? ብርሃናችንን የምናበራበት ዋንኛው መንገድ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መካፈል ነው። እያንዳንዱ ጉባኤ በተሰጠው ክልል ውስጥ ለመስበክ የሚያስችሉ መደበኛና የተደራጁ ዝግጅቶች አሉት። ከፍተኛ መጠን ያላቸው የተለያዩ ጽሑፎች በብዙ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። በስብሰባዎች አማካኝነት ሰፊ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ሌሎችን በግል በማሰልጠን እገዛ ያደርጋሉ። ወንዶች፣ ሴቶች፣ በእድሜ የገፉና ሌላው ቀርቶ ልጆች እንኳ በዚህ ሥራ መካፈል የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ችሎታዎቹና ሁኔታዎቹ በፈቀዱለት መጠን በዚህ ሥራ እንዲካፈል ተጋብዟል። የጉባኤው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ያተኮሩት በስብከቱ ላይ ሲሆን እያንዳንዱ አባል በሆነ መንገድ በዚህ ሥራ ላይ እንዲካፈል የሚረዱ ዝግጅቶች አሉት። ዘወትር ከጉባኤው ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረጉ ብርሃናችን እየበራ እንዲቀጥል የሚያደርግ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው።

7 የቃል ምስክርነት ሳንሰጥ በሌሎች መንገዶች ብርሃናችንን ማብራት እንችላለን። በጠባያችን ብቻ የሌሎችን ትኩረት መሳብ እንችላለን። ጴጥሮስ “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ . . . እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” ብሎ ሲያሳስብ በአእምሮው ይዞት የነበረው ይህንን ነው። (1 ጴጥ. 2:12) ብዙ ሰዎች ስለ አንድ መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት አንድ መደምደሚያ ላይ የሚደርሱት አባላቱ ባላቸው ጠባይ ተመርኩዘው ነው። ሰዎች በሥነ ምግባር ንጹሕ፣ ሐቀኛ፣ ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ሰዎችን ሲመለከቱ የተለዩ እንደሆኑ አድርገው ከማየታቸውም በተጨማሪ እነዚህ ሰዎች ብዙሃኑ ከሚከተሏቸው የአቋም ደረጃዎች በጣም ከፍ ያሉ የአቋም ደረጃዎች አሏቸው የሚል እምነት ያድርባቸዋል። ስለዚህ አንድ ባል ሚስቱን ፍቅር በተሞላበት መንገድ ሲያከብራትና ሲንከባከባት ብርሃኑን እያበራ ነው ማለት ነው። ሚስትም የባሏን የራስነት ሥልጣን በማክበር እንዲሁ ታደርጋለች። ልጆች ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ እንዲሁም ከጾታ ብልግናና ዕፅ ከመውሰድ ሲርቁ ከሌሎች ለየት ብለው ይታያሉ። በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ ለሥራው ጠንቃቃ የሆነ፣ ሐቀኛና ለሌሎች የሚያስብ ሰው ከሌሎች ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል። እነዚህን ክርስቲያናዊ ጠባዮች ስናሳይ ሌሎች እኛ ሕይወታችንን በምንመራበት መንገድ ሕይወታቸውን እንዲመሩ እየጋበዝን ስለሆነ ብርሃናችንን እያበራን ነው ማለት ነው።

8 ስብከት ከአምላክ ቃል የተማርነውን ነገር ለሌሎች የምንነግርበት መንገድ ነው። ይህን የምናደርገው መድረክ ላይ ሆነን ወይም ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ቢሆንም ስብከታችን በእነዚህ አጋጣሚዎች ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም። ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ከብዙ ሰዎች ጋር ያገናኙናል። በአንድ ቀን ውስጥ ከቅርብ ጎረቤቶችህ ጋር ምን ያህል ጊዜ ትነጋገራለህ? ሰዎች ምን ያህል ጊዜ ወደ ቤትህ ይመጣሉ? ዕቃ ስትገዛ፣ በአውቶቡስ ስትጓዝ ወይም ሰብዓዊ ሥራህን ስትሠራ ምን ያህል ሰዎች ታገኛለህ? ትምህርትህን በመከታተል ላይ ያለህ ወጣት ከሆንክ በእያንዳንዱ ቀን የምታነጋግራቸውን ሰዎች መቁጠር ትችላለህን? ሌሎችን ለማነጋገር ያሉት አጋጣሚዎች ወሰን የላቸውም ለማለት ይቻላል። ማድረግ የሚያስፈልግህ ነገር ቢኖር ጥቂት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን በአእምሮህ መያዝ፣ መጽሐፍ ቅዱስና ጥቂት ትራክቶች ቶሎ ማግኘት በምትችልበት ቦታ ማስቀመጥና አጋጣሚውን ስታገኝ ቅድሚያውን ወስደህ መናገር ነው።

9 መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምስክርነት መስጠት ቀላል ቢሆንም ብዙዎች በዚህ መስክ ለመሳተፍ ያመነታሉ። የማያውቋቸውን ሰዎች ለማናገር በጣም ዓይነ አፋሮች ወይም እጅግ ፈሪዎች እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ዝምተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። የሰዎችን ትኩረት ወደ እነርሱ መሳብ ወይም ሰዎች የሚሰጡት የተቃውሞ ምላሽ ሊያስፈራቸው ይችላል። መደበኛ ባልሆነ ምስክርነት ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎች ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለ ሊነግሩህ ይችላሉ። ሌሎች ሰዎች ልክ እንደኛው ናቸው። እኛ የሚያስፈልገን ነገር ያስፈልጋቸዋል፣ የሚያሳስበን ነገር ያሳስባቸዋል እንዲሁም እኛ ለራሳችንና ለቤተሰባችን የምንፈልገውን ነገር እነርሱም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ይፈልጉታል። ብዙዎቹ ለሚቀርብላቸው ደስ የሚል ፈገግታና ወዳጃዊ ሰላምታ ቀና ምላሽ ይሰጣሉ። ውይይት ለመጀመር ‘ደፋር’ መሆን ይኖርብሃል። (1 ተሰ. 2:2) አንዴ ከጀመርከው ግን አስገራሚና አስደሳች ውጤቶች ልታገኝ ትችላለህ።

10 ብርሃናችንን ስናበራ እንባረካለን፦ መደበኛ ባልሆነ ምስክርነት አማካኝነት ከተገኙ የሚያነቃቁ ተሞክሮች መካከል ጥቂት ምሳሌዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል:- አንዲት የ55 ዓመት ሴት መንገድ እያቋረጡ ነበር። አንድ መኪና ሊገጫቸው ሲል አንዲት እህት እጃቸውን ያዝ አድርጋ ወደ ዳር አወጣቻቸውና “እባክዎትን ለራስዎ ይጠንቀቁ። የምንኖረው አደገኛ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው!” አለቻቸው። ከዚያም ያለንበት ጊዜ በጣም አደገኛ የሆነበትን ምክንያት ነገረቻቸው። ሴትየዋም “የይሖዋ ምሥክር ነሽ?” ብለው ጠየቋት። ሴትየዋ ከመጽሐፎቻችን መካከል አንዱን ከእህታቸው አግኝተው ነበር፤ በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት ይፈልጉ ስለነበር ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሆነላቸው።

11 አንዲት እህት ሐኪም ቤት ወረፋ እየጠበቀች ከሌላ ሴት ጋር መነጋገር ጀመረች። ሴትየዋ በትኩረት ካዳመጠች በኋላ እንዲህ አለች:- “እርግጥ የይሖዋ ምሥክሮችን መንገድ ላይ አገኛቸው ነበር፤ ነገር ግን እኔ ራሴ ወደፊት የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ መቼም ለዚህ ዋንኛ ምክንያት የሚሆነው አሁን አንቺ የነገርሽኝ ነገር ነው። የነገርሽኝ ነገር በጨለማ ውስጥ የፈነጠቀ ብርሃን ሆኖልኛል።”

12 ለሰዎች ደግነት ማሳየት እውነትን እንዲያውቁ መርዳት የምንችልበት መንገድ ሊከፍትልን ይችላል። ሁለት እህቶች ከመስክ አገልግሎት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አንዲት በዕድሜ የገፉ ሴት ከአውቶቡስ ሲወርዱ ተመለከቱ፤ ሴትየዋ ትንሽ ያመማቸው ይመስሉ ነበር። ቆም አሉና ሴትየዋ እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቋቸው። ሴትየዋ ፈጽሞ የማያውቋቸው ሁለት ሰዎች አሳቢነት ስላሳዩአቸው በጣም በመደነቅ እንዲህ ያለ ደግነት እንዲያሳዩ የገፋፋቸው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈለጉ። ይህም ምስክርነት ለመስጠት የሚያስችል በር ከፈተ። ሴትየዋ ወዲያውኑ አድራሻቸውን ሰጧቸውና መጥተው እንዲያነጋግሯቸው ሞቅ ያለ ግብዣ አቀረቡላቸው። ከዚያም ጥናት ተጀመረ። ብዙም ሳይቆዩ ሴትየዋ ስብሰባ ላይ መገኘት የጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እርሳቸውም እውነትን ለሌሎች በመናገር ላይ ይገኛሉ።

13 አንዲት በዕድሜ የገፉ እህት በጠዋት ተነስተው በአካባቢው በሚገኝ የባሕር ዳርቻ ይሰብካሉ። ከቤት ሠራተኞች፣ ከሞግዚቶች፣ ከባንክ ጸሐፊዎችና ጠዋት ተነስተው በባሕሩ ዳርቻ በእግራቸው ከሚንሸራሸሩ ሌሎች ሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር። በባሕሩ ዳርቻ ባሉ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመሩ ነበር። ብዙ ሰዎች በእርሳቸው አማካኝነት እውነትን ሰምተው በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።

14 አንዲት እህት መሥሪያ ቤቷ ውስጥ አንዲት የሥራ ባልደረባዋ የዓለምን ችግሮች ይፈታል ብላ ስለምታምንበት የፖለቲካ ፓርቲ ስትናገር ሰማች። እህት የአምላክ መንግሥት ወደፊት ምን እንደምታከናውን የተሰጠውን ተስፋ ነገረቻት። ይህ በሥራ ቦታ ያደረጉት ውይይት ቤት ተገናኝተው ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ መንገድ ከፈተላቸው፤ በመጨረሻም ሴትየዋና ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

15 የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ፈጽሞ አትርሳ! ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የዓለም ብርሃን” ብሎ ሲጠራቸው ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ካለው መንፈሳዊ ብርሃን እንዲጠቀሙ ሊረዷቸው እንደሚገባ ነግሯቸዋል። የኢየሱስን ምክር በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ አገልግሎታችንን እንዴት አድርገን እንመለከተዋለን?

16 አንዳንድ ሰዎች የትርፍ ጊዜ ሥራ ቢያገኙ ይመርጣሉ። አብዛኛውን ጊዜያቸውን ይበልጥ ዋጋማ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ማሳለፍ ስለሚፈልጉ በሰብዓዊ ሥራ በሚያሳልፉት ጊዜና ጉልበት ረገድ ገደብ ያበጃሉ። እኛስ ለአገልግሎታችን እንዲህ ያለ አመለካከት አለንን? ማድረግ እንዳለብን ተሰምቶን ለአገልግሎት ጊዜ ብንመድብም እንኳ ዋናው ግባችን ሌላ ነገር መሆን አለበትን?

17 የከፊል ጊዜ ክርስቲያን የሚባል ነገር እንደሌለ ተገንዝበን ‘ራሳችንን በመካድ’ ኢየሱስን “ያለማቋረጥ” ለመከተል ቆርጠን ራሳችንን ለአምላክ ወስነናል። (ማቴ. 16:24 አዓት) ፍላጎታችን በየትም ቦታ ያሉ ሰዎች ብርሃናችን እንዲታያቸው ለማድረግ ሁሉንም አጋጣሚዎች በመጠቀም “በሙሉ ነፍሳችን” እያገለገልን መቀጠል ነው። (ቆላ. 3:23, 24) ከዓለማዊ አስተሳሰብ መራቅ፣ መጀመሪያ ላይ የነበረን ቅንዓት እንዳይጠፋ ማድረግና ብርሃናችን ዘወትር ቦግ ብሎ እንዲበራ ማድረግ አለብን። አንዳንዶች ቅንዓታቸው እንዲቀዘቅዝና ብርሃናቸው ከቅርብ ርቀት እንኳ ማየት እስኪያስቸግራቸው ድረስ እንዲደበዝዝ ፈቅደው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል የነበራቸውን ዓይነት የአገልግሎት ቅንዓት እንዲኖራቸው እርዳታ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል።

18 ብዙ ሰዎች በመልእክታችን ስለማይደሰቱ አንዳንድ አስፋፊዎች ከመናገር ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ የሚነገረው መልእክት “ለሚጠፉት ሞኝነት ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 1:18) ሆኖም ሌሎች ያሉትን ቢሉ “በወንጌል አላፍርም” በማለት ጠንከር አድርጎ ገልጿል። (ሮሜ 1:16) የሚያፍር ሰው የበታችነት ስሜት ወይም ዋጋ ቢስነት ይሰማዋል። ስለ አጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታና ዘላለማዊ ደስታ እንድናገኝ ብሎ ስላዘጋጃቸው አስደናቂ ዝግጅቶች ስንናገር እንዴት እፍረት ሊሰማን ይችላል? እነዚህን እውነቶች ለሌሎች ስንናገር ፈጽሞ የበታችነት ስሜት ወይም ዋጋ ቢስ እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ ‘ምንም የምናፍርበት ነገር እንደሌለ’ ያለንን ጠንካራ እምነት በግልጽ በማሳየት የቻልነውን ያህል ለማድረግ መትጋት እንዳለብን ሊሰማን ይገባል።— 2 ጢሞ. 2:15 የ1980 ትርጉም

19 በአሁኑ ጊዜ በመላው ምድር ላይ እየበራ ያለው የእውነት ብርሃን በገነቲቱ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ዘርግቷል። ብርሃናችን ሳያቋርጥ እንዲበራ የተሰጠንን ምክር ልብ እንዳልነው እናሳይ! እንዲህ ማድረጉ በየቀኑ “ያለማቋረጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራች ያስተምሩና ያውጁ” እንደነበሩት ደቀ መዛሙርት ደስታ ያስገኝልናል።— ሥራ 5:42 አዓት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ